Friday, July 25, 2014

ኢትዮጵያ በፍርሀት የሞት እና ሽረት ትግል መካከል የምትንጠራወዝ ምስኪን አገር


ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም

ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ



በሞት ሽረት ትግል ውስጥ የሚገኙት የዞን 9 ትንታግ ወጣት ጦማርያን

የኔ ጥያቄ እውን በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ያለው ስርዓት “የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ መንግስት ሬፐብሊክ መንግስት” ነው ወይስ በሽብር ተግባር ላይ ተዘፍቆ የሚገኝ “የፖሊስ መንግስት”? ኢትዮጵያ በሌላ ጠፈር (ህዋ) የምትገኝ አገር ናትን? እነዚህን ጥያቄዎች በጥሞና የማነሳቸው ጥያቄዎች ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ “የፖሊስ ሬፐብሊክ መንግስት” ተብላ ልትጠራ ትችላለች፡፡ በ20ዎቹ አካባቢ የዕድሜ ጣሪያ ላይ የሚገኙ ወጣት ወንዶች እና ሴቶች በፌስቡክ እና በሌሎች የማህበረሰብ ድረገጾች ያለምንም ፍርሀት በመጻፋቸው እና ሀሳባቸውን በነጻ በመግለጻቸው ምክንያት ብቻ በገዥው አካል ሽብርተኛ በሚል የሸፍጥ ፍረጃ እና ክስ በቁጥጥር ስር ውለው በእስር ቤት በመማቀቀቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ ያለው ገዥ አካል 6 ጦማሪያንን እና 3 ጋዜጠኞችን (የዞን 9 ጦማርያን እየተባሉ የሚጠሩትን) በተለምዶ ቃሊቲ እየተባለ በሚጠራው በአስፈሪው የመለስ ዜናዊ የማሰቃያ እስር ቤት ከሚማቅቁት የፖለቲካ እስረኞች የእስር ቤት ቁጥር 8 ቀጥሎ በተሰየመው የማጎሪያ እስር ቤት ለ80 ቀናት ያህል ሲያማቅቅ ከቆየ በኋላ ህገወጥ በሆነ መልኩ ሽብርተኛ የሚል ታፔላ በመለጠፍ መሰረተቢስ የሆነ የሸፍጥ ውንጀላ ክስ መስርቶባቸዋል፡፡



ሀሳባቸውን ያለምንም ፍርሀት በፌስቡክ እና በማህበረሰብ ድረገጽ ነጻ በሆነ መልኩ ከገለጹት ውሰጥ የሚከተሉት ትንታግ ወጣት ጦማሪያን ይገኙበታል፤ አቤል ዋቤላ(በኢትዮጵያ አየር መንገድ በመሀንዲስነት ተቀጥሮ የሚሰራ)፣ አጥናፍ ብርሀኔ(በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሙያ በክፍለ ከተማ ተቀጥሮ የሚሰራ)፣ ማህሌትፋንታሁን (በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በስታቲስቲክስ ባለሙያነት ተቀጥራ የምትሰራ)፣ናትናኤል ፈለቀ (በኮንስትራክሽን እና ቢዝነስ ባንክ በማኔጀርነት ተቀጥሮ የሚሰራ የኢኮኖሚክስ ባለሙያ)፣ ሲሆን ከዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከሆኑት ጆን ኬሪ ጋር ከዚህ በታች የተነሳውን ፍቶግራፍ ማየት ይቻላል፣ዘላለምክብረት (በአምቦ ዩኒቨርስቲ የህግ ትምህርት መምህር)፣ እና በፈቃዱ ኃይሉ(በቅድስት ማሪያም ዩኒቨርስቲ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያ እና በቅርብ ጊዜ ደግሞ የዕንቁ መፅሔት አርታኢ በመሆን ሲያገለግል የነበረ)፡፡ ሌሎቹ በገዥው አካል ህገወጥ ውሳኔ እስረኛ ጦማሪያን የሚከተሉትን ያካትታል፤ ጋዜጠኛ አስማማው ኃ/ጊዮርጊስ (ከአዲስ ጉዳይ ጋዜጣ)፣ እና ፍሪላንሰሮች ተስፋሁንወልደየስ (ከአዲስ ስታንዳርድ መጽሔት) እና ኤዶም ካሳዬ (የቀድሞ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ሰራተኛ የነበረች) ናቸው፡፡ ኢትዮጵያውያን/ት ጋዜጠኞች እና ጦማርያንን (ከዚህ በላይ የተጠቀሱትን ጥቂቶችን ጨምሮ) በተጨባጭ እውነታ ላይ በመመስረት የሰጡትን ቃለ መጠይቅ በሚመለከት መሰረቱን በእንግሊዝ አገር ያደረገ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ቡድን አንቀጽ 19 በሚል ርዕስ በድረገጽ ላይ ያደረገውን ቃለመጠይቅ ከእዚህ ጋ በመጫን ማዳመጥ ይቻላል)፡፡

የሽብርተኝነት ክሱ ዋና ጭብጥ ጦማሪያኑ “በውጭ ከሚንቀሳቀሱ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ነን ከሚሉ ድርጅቶች ጋር ህብረት በመፍጠር በአገር ውስጥ ሁከት እና እረብሻ ለመፍጠር“ እና “ከውጭ የእርዳታ ገንዘብ በመቀበል ህዝባዊ አመጽ ለመቀስቀስ የማህበረሰብ ድረገጾችን ይጠቀማሉ“ የሚል ነው፡፡

በአማርኛ ተዘጋጅቶ ይፋ የሆነውን የክስ ሰነድ ለማየት ከእዚህ ጋ ይጫኑ፡፡ (በባለአርማ የተጻፈው የመጻጻፊያ ቋሚ ወረቀት ላይ “ኢትዮጵያ” የሚለው የንግሊዘኛ ቃል ቃል በስህተት “ኢትዮያ” ተብሎ መጻፉን ልብ ይሏል)፡፡ አገሪቱ በይፋ በምትጠቀምበት በባለአርማ ወረቀት በታተመው የመጻጻፊያ ደብዳቤ ላይ የአገሪቱን ስም በትክክል መጻፍ ያቃተው ገዥ አካል በጦማሪያኑ ላይ የመሰረተው ክስ ትክክል ይሆናል ብሎ መውሰድ እንደምን ይቻላል? ምን ዓይነት አሳፋሪ ሁኔታ ነው!!!

በሽብርተኝነት ስም የተመሰረተው የውንጀላ ክስ በርካታ ዝርዝር ጉዳዮችን የሚያካትት ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ ሽብርተኝነትን ለመፈጸም ከሌሎች ጋር አብሮ መዶለት፣ የማህበረሰብ መገናኛ ድረገጾችን በመጠቀም የአመጽ ቅስቀሳ ማካሄድ፣ ለኢትዮጵያ ሳቴላይት ቴሌቪዥን/ኢሳት እና ሬዲዮ ዘገባዎችን ማቅረብ፣ ለግንቦት ሰባት የሚሆኑ አባላትን በመመልመል የትብብር አገልግሎት መስጠት፣ በሰው እና በንብረት ላይ አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉ ፍንዳታዎችን ለማካሄድ የአሸባሪነት ስልጠናዎችን መውሰድ፣ ለአሸባሪ ኃይሎች ስልት መንደፍ እና የአሮሞ ነጻነት ግንባርን ፕሮፓጋንዳ መንዛት የሚሉት ናቸው፡፡ ለውንጀላው አስረጅ ይሆናሉ የተባሉ ዝርዝር ሰነዶች በዋናነት በተከላካዮች እጅ የሚገኙትን ብዙ ዲጂታል የኤሌክትሮኒክ መገናኛ ዘዴዎችን መሰረት ያደረገ ነው፡፡ የዩናይትድ ስቴትስ መንግስት መምሪያ በዞን 9 ጦማሪያን ላይ የቀረበውን የክስ ውንጀላ ያለውን ስጋት በመግለጽ ለገዥው አንዲህ ስል አስገንዝቧል፣ “ኢትዮጵያ ነጻ ሀሳብን ከመግለጽ የሚገድበውን የጸረ ሽብርተኝነት ህግ ከመተግበር እንድትቆጠብ“ በማለት መግለጫው የሚከተለውን አውጇል፣ “ሀሳብን በነጻ መግለጽ እና የነጻው ፕሬስ ነጻነት የዴሞክራሲያዊ ማህበረሰብ መሰረታዊ ምርጫዎች ናቸው፡፡ ነጻ ጋዜጠኞችን እና ጦማሪያንን በቁጥጥር ስር በማዋል በጸረ ሽብርተኝነት ህግ ወንጀል ክስ መስርቶ ዜጎችን በፍርድ ቤት ቀጠሮ ማንገላታት በመላ የኢትዮጵያ ህዝቦች ሰብአዊ መብት ጥበቃ እና በመገናኛ ብዙሀን ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል፡፡“ ከዚህም በተጨማሪ ሂዩማን ራይትስ ዎች፣ የጋዜጠኞች ጥበቃ ኮሚቴ እና ሌሎች የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የዞን 9 ጦማሪያን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ እንዲፈቱ መግለጫ በማውጣት ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

በሀሰተኛዋ ሬፐብሊካዊት ኢትዮጵያ…

በሀሰተኛዋ ሬፐብሊካዊት ኢትዮጵያ ጋዜጠኞች በእስር ቤት ታጉረው ይጠበቃሉ፣ እናም የሙያ ስነምግባራቸውን በመተግበራቸው ብቻ በእስር ቤት እንዲማቅቁ ይደረጋሉ፡፡ እ.ኤ.አ የ2014 ትልቅ ክብር ያለውን እና ዓመታዊ ለፕሬስ ነጻነት አሸናፊዎች የሚሰጠውን ወርቃማውን የብዕር ሽልማት ከዓለም ጋዜጦች እና ዜና አታሚዎች ማህበር (ሌሎች በርካታ ዓለም አቀፍ የፕሬስ ሽልማቶች አሸናፊ የሆነው) በቅርቡ የተሸለመው እስክንድር ነጋ በነጻ በመጻፉ ብቻ የ18 ዓመታት እስራት ተበይኖበታል፡፡ የ34 ዓመቷ ሴት ጀግና ወጣት እና የኢትዮጵያ ፕሬስ ነጻነት ቀንዲል የሆነችው እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅናን የተጎናጸፈችው “እውነት ተናጋሪዋ እስረኛ“ እየተባለች የምትጠራው እና የበርካታ ዓለም አቀፍ የፕሬስ ሽልማቶችን አሸናፊ የሆነችው ርዕዮት ዓለሙ የገዥውን የፖለቲካ ፓርቲ በአገር አቀፍ የግድብ ፕሮጀክት የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዘዴ ላይ የሰላ የጽሁፍ ትችት በማቅረቧ እና በሞት በተለዩት በመለስ ዜናዊ እና አሁን በህይወት በሌለው በሊቢያው አምባገነን መሪ በሞአማር ጋዳፊ መካከል ምንም ዓይነት ልዩነት የሌላቸው አምባገነኖች ናቸው በማለቷ ብቻ የ14 ዓመታት እስራት ተበይኖባታል፡፡ ሌላው የዓለም ዓቀፍ የፕሬስ ሽልማት አሸናፊ የሆነው ትንታግ ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ ሲያዘጋጀው በነበረው ጋዜጣ ላይ የገዥው አካል በሙስና የበከተ መሆኑን እና የያዘውን ስልጣንም ከህግ አግባብ ውጭ እየተጠቀመ መሆኑን በመግለጹ ብቻ የ14 ዓመታት እስራት ተፈርዶበታል፡፡ በዚህ ዓይነት ጉዳይ ላይ የሚጽፉ እና የዜግነት ግዴታቸውን ለመወጣት ሲሉ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የሚፋለሙ ሌሎች በርካታ የነጻው ፕሬስ ጋዜጠኞች አሉ፡፡

በሀሰተኛዋ ሬፐብሊካዊት ኢትዮጵያ ጋዜጠኞችን፣ ጦማሪያንን፣ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን እና ሰላማዊ አማጺያንን በመወንጀል፣ ስማቸውን ጥላሸት በመቀባት እና ኢሰብአዊ ድርጊትን በመፈጸም አሸባሪዎች፣ አመጸኞች እና ሌላ ሌላም በመሰየም ይፈርጇቸዋል፡፡ አሁን በህይወት የሌለው የገዥው አካል ቁንጮ መሪ እና ዘዋሪ፣ አድራጊ እና ፈጣሪ የነበረው አምባገነኑ መለስ ዜናዊ እ.ኤ.አ የ2005 አገር አቀፍ ምርጫን ተከትሎ በተፈጠረው ቀውስ የበርካታ ጋዜጦች አታሚዎችን በእስር ቤት ካጎረ በኋላ በነጻው ፕሬስ ላይ ጦርነት በማወጅ እንዲህ የሚል መግለጫ ሰጥቶ ነበር፣ “ለእኛ እነዚህ ጋዜጠኞች አይደሉም፣ የፕሬስ ህጉን ጥሰዋል ተብለው ክስ አይመሰረትባቸውም፡፡ እንደ ለቅንጅት ለአንድነት እና ለዴሞክራሲ አመራሮች በአገር ክህደት ወንጀል ይከሰሳሉ“ በማለት ሲሳለቅ የነበረ መሆኑ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ2011 ፈላጭ ቆራጩ መለስ ዜናዊ ጆን ፔርሰን እና ማርቲን ሽብዬ የተባሉትን ስዊድናዊ ጋዜጠኞች በቁጥጥር ስር በማዋል ወደ ዘብጥያ ከወረወረ በኋላ እንዲህ በማለት ፈርጇቸው ነበር፣ “የሽብርተኛ ድርጅት ተላላኪዎች“ እንዲህ ሲል ተሳልቋል፣“እነዚህ ወንጀለኞች አሁን እየሰሩት ያለው ጋዜጠኝነት የሚያሰኝ ከሆነ እኔ እራሴ ሽብርተኝነት ምን እንደሆነ አላውቅም ማለት ነው“ በማለት የተለመደውን የቅጥፍና ፍልስፍና አሰምቶ ነበር፡፡

በሀሰተኛዋ ሬፐብሊካዊት ኢትዮጵያ ጋዜጠኝነት ማለት አሸባሪነት ማለት ነው፡፡ ጋዜጠኞች ለመንግስት ጠላቶች ናቸው፡፡ መጦመር ወይም መጻፍ የሀገር ክህደት ወንጀል ነው፡፡ ጦማሪያን የመንግስት ደመኛ ጠላቶች ናቸው፡፡

በሀሰተኛዋ ሬፐብሊካዊት ኢትዮጵያ የእንግሊዝ ዜግነት ያለው የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አመራር በየመን በአውሮፕላን በትራንዚት ላይ እያለ አስነዋሪ እና አሳፋሪ የሆነ የጠለፋ ወንጀል ተፈጽሞበታል፣ እናም ከህግ አግባብ ውጭ በሆነ መልኩ ዓለም አቀፍ ህግን በመደፍጠጥ ወደ ዘብጥያ እንዲወረወር ተደርጓል፡፡

በሀሰተኛዋ ሬፐብሊካዊት ኢትዮጵያ ሰዎች ኢሰብአዊነት ድርጊት ይፈጸምባቸዋል፣ ስልጣኔ ወደ ኋላቀርነት ይቀየራል፣ ፍትህ በሙስና ይጣመማል፣ የጎሳ ማጥራት ዘመቻ ይካሄዳል፣ ህዝቦች በድህነት እንዲማቅቁ እና የረሀብ ሰለባ እንዲሆኑ ይደረጋል፣ ወጣቶች በችግር እንዲጠረነፉ ይደረጋል፣ የግዳጅ ስራ እንዲሰሩ ይደረጋል፣ ሰካራም እንዲሆኑ እንዲሁም የጫት እና የሌሎች ሱሶች ተገዥዎች እንዲሆኑ ስልታዊ ስራ ይሰራል፣ ተፈጥሯዊ ከባቢያችን እንዲወድም ይደረጋል፣ ግድቦች በዘላቂነት በአንድ ቦታ አካባቢ የሚኖሩትን የወገኖቻችንን ህይወት በሚጎዳ መልኩ በመገደብ በህብረተሱ ዘንድ መቅሰፍታዊ አደጋ እንዲመጣ ይደረጋል፣

በሀሰተኛዋ ሬፐብሊካዊት ኢትዮጵያ ድህነት ሀብታምነት ማለት ነው፣ ረሀብ ማለት በጥጋብ መወጠር ማለት ነው፣ የመንግስት በስህተት መዘፈቅ የሰብአዊ መብት ማክበር ማለት ነው፡፡ ጭቆና ፍትሀዊነት ነው፣ እናም ወሮበልነት ዴሞክራሲያዊነት ማለት ነው፡፡

በሀሰተኛዋ ሬፐብሊካዊት ኢትዮጵያ ድንቁርና ምሁርነት ነው፡፡ የመንግስት ዋና ዓላማ ህዝቡን አደንቁሮ ለማቆየት እና በህገወጥነት መንገድ ለመግዛት እውነታውን ማጣመም፣ መወጠር እና እውነታውን ማፍተልተል፣ ጸጥ ማድረግ እና ምንም ሳያስቡ ባላወቁት እና ባላመኑበት ነገር ላይ ስምምነት እንዲያደርጉ ማስቻል ነው፡፡

በሀሰተኛዋ ሬፐብሊካዊት ኢትዮጵያ ወሮበሎች ይገዛሉ! ወሮበሎችን መፍራት የህግ የበላይነት ማለት ነው!

በዞን 9 ሰላማዊ እንቅስቃሴ ምክንያት የሚደረግ የፍርሀት የሞት ሽረት ትግል፣

በ196ዎቹ አመታት ሮድ ሴርሊንግ በተባለ በአንድ ታዋቂ እና ተወዳዳሪ በሌለው “የሞት ሽረት ትግል” በተሰኘ ተከታታይ የቴሌቪዥን የተውኔት ደራሲ አስፈሪ ተውኔቶችን፣ ጭንቀት የተሞላበት እና በጣም አስቸጋሪ የሆነ የአውዳሚነት ባህሪን የተላበሰ የሳይንስ ልብወለድ ድርሰት ተዘጋጅቶ ቀርቦ ነበር፡፡ በአንድ ትርኢት ያቀርበው ታሪክ የቤተመጽሐፍት ባለሙያ ሰው ላይ የተመሰረተ ነበር:: ይህ የቤተመጽሐፍት ባለሙያ “አታስፈለግም” የሚል ክስ ቀርቦበት ነበር:: በዚህ በቀረበበት ክስ ምክንያት የሞት ፍርድ ሊበየንበት እንደሚገባ የግዛቱ አስተዳዳሪ የሆነው ባለስልጣን በችሎት በተሰየመው የዳኞች ስብሰባ ፊት በመገኘት ችሎቱን ለማሳመን ሞከረ፡፡ በፍርድ አሰጣጥ ሂደቱ ወቅት ባለስልጣኑ ( ቻንስለሩ) እና የቤተመጽሐፍት ባለሙያው በሰው ልጅ ክብር ላይ በሚከተለው መልኩ ጠንካራ የሆነ ክርክር በማድረግ ስራ ላይ ተጠመዱ፣

ባለስልጣኑ (ቻንስለሩ) (ለቤተመጽሐፍት ባለሙያው)፡ “አንተ የማታስፈለግ ባለሙያ ነህ!

የቤተመጽሐፍት ባለሙያው፡ የመጽሐፍ ገጾችን በማቃጠል እውነታውን ልታወድም እንደማትችል ከማሳሰብ የዘለለ ሚና የለኝም!

ባለስልጣኑ፡ አንተ ትኋን ነህ፡፡ በመሬት ላይ የምትሳብ ነብሳት፡፡ አስቀያሚ እና ምንም ዓይነት ቅርጽ የሌለህ ዓላማ ቢስ አናሳ ፍጡር ነህ! ምንም ዓይነት ስራ የለህም…“

የቤተመጽሐፍት ባለሙያ፡ “እኔ ሰብአዊ ፍጡር ነኝ…”

ባለስልጣኑ፡ “አንተ የመጽሐፍት አከፋፋይ ነህ፣ በመጽሐፍት ማውጫ መደርደሪያው መስመር ላይ ትርጉም የለሽ የሆኑ ቃላትን በኃይል በማውጣት በተዘጋጀው የመጽሐፍት መደርደሪያ ላይ ሁለት ሳንቲም የሚያወጡ ጥራዞችን እያወጣህ የምትደርድር ከንቱ ፍጡር ነህ፡፡ ምንም ዓይነት ዋጋ የሌላቸው ቃላት፣ እንደ ነፋስ፣ ምንም ዓይነት አቅጣጫ የሌላቸው ናቸው፡፡ እንደ ባዶ ህዋ በትንሽ ካርድ ላይ አመልካች ቁጥሮችን በመደርደር ትርጉም የለሽ ምልክት በማድረግ ህልውና እንዳለህ በመቁጠር እምነት እንዲያድርብህ ታደርጋለህ፡፡“

የቤተመጽሐፍት ባለሙያው፡ “እኔ ደንታዬ አይደለም፡፡ ነግሬሀለሁ፣ ደንታዬ አይደለም፡፡ ሰብአዊ ፍጡር ነኝ፣ እኖራለሁ… እናም አንድን ሀሳብ ከፍ በማድረግ በተናገርሁ ጊዜ ያ ሀሳብ በዘላቂነት ይኖራል ወደ መቃብር ከተወረወርኩ በኋላም ቢሆን እንኳ፡፡“

ባለስልጣኑ፡ እነዚህ ሁሉ ከንቱ የውሸት እምነቶች ናቸው!! የማተሚያ ቀለሙን በደምህ ውስጥ በማዋሀድ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ግጥም፣ ድርሰት እና ሌላም ነገር ሁሉ ስነጽሁፍ እያልክ የምትጠራውን አደንዛዥ ዕጽ በመውሰድ ምንም ዓይነት ኃይል ሳይኖርህ ኃይል እንዳለህ አድርገህ እራስህን ትቆጥራለህ!!! አንተ ምንም ማለት አይደለህም፣ ሆኖም ግን አንተ ማለት የሚንቀሳቀሱ የእጆች እና እግሮች ቅርጽ አንዲሁም ህልም ብቻ ያሉህ ፍጡር ነህ፡፡ እናም መንግስት አንተ የዋህ በመሆንህ የሚያገኘው አንዳችም ጥቅም የለም!!! ጊዚያችንን አቃጥለሀል፣ እናም ያቃጠልከውን ጊዜ ያህል ጠቀሜታ የሌለህ ከንቱ ፍጡር ነህ፡፡

ፍርድ ቤቱ የሞት ቅጣቱን ውሳኔ የቤተመጽሐፍት ባለሙያ ላይ ተግባራዊ አደረገ፡፡

የቤተመጽሐፍት ባለሙያው ድፍረት በተመላበት መልኩ የሞት ቅጣቱን ዕጣ ፈንታ በጸጋ ተቀበለ፡፡ ጨካኝ አረመኔዎቹ ምህረትን እንዲያደርጉለት ከመጠየቅ ይልቅ የእራሱን ሰብአዊ ክብር እና ነጻነት ለማስጠበቅ ሲል ከኃይለኞቹ ጉልበተኞች ፊት በጽናት ቆመ፡፡ ሁለት ልዩ የሆኑ ጥያቄዎችን አቀረበ፣ 1ኛ) በምን ዓይነት መንገድ የሞት ቅጣቱ ሊፈጸምበት እንደሚገባ እንዲመርጥ የሞት ቅጣቱን የወሰኑበት እብሪተኞች ዕድል እንዲሰጡት ጠየቀ፣ 2ኛ) የሚፈጸምበት የሞት ቅጣት እና በመሬት ላይ በህይወት የሚቆይባቸው የመጨረሻዎቹ ጥቂት ሰዓታት በቴሌቪዥን ለህዝብ ይፋ እንዲደረግ ጠየቀ፡፡ ሁሉም ዝግጅት ከተጠናቀቀ በኋላ የቤተመጽሐፍት ባለሙያው የሞት ቅጣቱን የሚያስፈጽመውን ባለስልጣን ወደ ማቆያ ክፍሉ ለመጨረሻ ጊዜ እንዲመጣ ጋበዘው፡፡ ባለስልጣኑ/ቻንስለሩ የሞት ቅጣቱ ከሚፈጸምበት ጊዜ ጥቂት ደቂቃዎች ቀደም በማለት ደረሰ፡፡ ለጥቂት ደቂቃዎች ተወያዩ፡፡ የውይይታቸው ዳህራ እንደሚከተለው ቀርቧል፣

የቤተመጽሐፍት ባለሙያ፡ እዚህ ድረስ ጥያቄዬን አክብረው በመምጣትዎ አመሰግናለሁ፡፡

ባለስልጣን፡ ለመሆኑ ለምን እንደመጣሁ ታውቃለህ?

የቤተመጽሐፍት ባለሙያ፡ አዎ እንዲመጡ ስለጋበዝኩዎ ነው፡፡

ባለስልጣን፡ እዚህ አንተ ጋ ለምን እምደመጣሁ ልነግርህ እፈልጋለሁ፡፡ ምናልባት ስለአንተ ጉዳይ አንድ ነገር ለማረጋገጥ ነው፡፡

የቤተመጽሐፍት ባለሙያ፡ እና ያ….?

ባለስልጣን፡ መንግስቱ ምንም ዓይነት ፍርሀት የለውም፣ ይህንን ላረጋግጥልህ ነው የመጣሁት፡፡ በምንም ዓይነት መልኩ ቢሆን ምንም ፍርሀት የሚባል ነገር የለም፣ ምንም…

የቤተመጽሐፍት ባለሙያ፡ ክቡር ባለስልጣን እንደዚህ ላለ የተለቀቀ ፌዝ ይቅርታ እንዲያደርጉልኝ እጠይቃለሁ…ማለቴ ወደ እኔ ማቆያ ክፍል የመጡት መንግስት… እኔን የማይፈራኝ መሆኑን ለመግለጽ ነውን!? እኔ ለምንድን እንደዚህ ያለ የማይታመን ሸክም ለመሆን እንደቻልኩ የሚገርም ጉዳይ ነው! መንግስት አንድ እንደ እኔ ያለውን ያረጀ የቤተመጽሐፍት ባለሙያ የማይፈራ መሆኑን ለማረጋገጥ እዚህ ድረስ መምጣቱ የሚያስደንቅ ነው፡፡ ኦ! አይደለም፡፡ እዚህ ድረስ የመጡበትን ምክንያ በግልጽ ልነግርዎት እፈልጋለሁ… እርስዎ ለእራስዎ ለመቀበል ፈቃደኛ ባይሆኑም እንኳ ምክንያቱን እንግረወታለሁ፡፡

ባለስልጣን፡ ያ ለምን መሆን እንዳለበት አሁን ጥያቄ የማቅረብ ተራው የእኔ መሆን የለበትምን?

የቤተመጽሐፍት ባለሙያ፡ የእርስዎን መስፈርት አላሟላም፡፡ የእርስዎ መንግስት ሁሉንም ነገር ፈርጆ አስቀምጧል…መለያ ቁጥር እና ኮድ ሰጥቷል፣ እንደዚሁም የመለያ ተለጣፊ ጸሑፍ/ታግ ሰጥቷል፡፡ እንደ እርስዎ ያሉ ሰዎች ኃያል ናቸው፡፡ እንደ እኔ ያሉ ሰዎች ደግሞ ደካሞች ናቸው፡፡ እርስዎ ስርዓትን ይቆጣጠራሉ፤ እናም ያስገድዳሉ… እኔ እና መሰል ደካሞች ፍጡራን ደግሞ እርስዎን መከተል እና መታዘዝ ነው፡፡ ሆኖም ግን አንድ ነገር ስህተት ተሰርቷል፣ አይደለምን? ለዚህ ጉዳይ ተስማሚ አይደለሁም፣ ነኝ እንዴ?

የቤተመጽሐፍት ባለሙያው ለባለስልጣኑ ማሳየት የፈለገው ህዝቦች በምን ዓይነት መንገድ ክብራቸው እና ሰብዕናቸው መጠበቅ እንዳለበት መከራከር እና መብትን መጠየቅ ለሞት ቅጣት እንደሚያደርስ አየተከራከረ ከዳዊት መዝሙር ምዕራፍ 23 እና 53ን ማንበብ ጀመረ ፡፡ በቴሌቪዥን ህዝቡ የቤተመጽሐፍት ባለሙያው እና ባለስልጣኑ ክርክር ሲያደርጉ ይመለከታል፡፡ የሞት ቅጣት የሚፈጸምበት ጊዜ እየተቃረበ ሲመጣ ባለስልጣኑ የቤተመጽሐፍት ባለሙያውን ክፍል ለቅቆ ለመውጣት ሞከረ፡፡ ሆኖም ግን የክፍሉ በር ተዘግቶ አገኘው፡፡ የሞት ቅጣቱ ሰዓት እኩለ ሌሊት መሆኑን ከማመልከቱ በፊት ባለስልጣኑ በጭንቀት ማዕበል ውስጥ ሰምጦ የሚይዝ የሚጨብጠውን አጣ፡፡ የቤተመጽሐፍት ባለሙያው ግን በተረጋጋ መንፈስ እና ከፍርሀት በጸዳ መልኩ ይመለከት ነበር፡፡ ባለስልጣኑ የቤተመጽሐፍት ባለሙያው የተቆለፈውን በር እንዲከፍትለት እና መውጣት እንዲችል እንዲህ በማለት ለመነው፣ “በእግዚአብሔር ስም ይዠሀለሁ ከዚህ ክፍል ውስጥ ልውጣ!“ የቤተመጽሐፍት ባለሙያው ደስታ በተቀላቀለበት ሁኔታ ሆኖም ግን መንግስት “እግዚአብሔር እንደማይኖር ያረጋገጠውን” ቃል ሳይደግም ባለስልጣኑ እንዲወጣ በሩን ከፈተለት፡፡ ከዚያ በኋላ ባለስልጣኑ በደረጃው ላይ አድርጎ ከክፍሏ በመውጣት ቁልቁል እየወረደ ከውስጥ ባለው የቤተመጽሐፍት ባለሙያ ክፍል ላይ የእሳት ቃጠሎ ተነሳ፡፡ በመጨረሻው ሁኔታ ባለስልጣኑ እንደ ወንጀለኛ የተፈረጀ እና አስፈላጊ አንዳልሆነ ወደ ፍርድ ሰጭ ጉባኤው ተመለሰ፡፡ የምክንያቱም ፍርሃት በማሳየት ያለዉን መንግስት መሳቂያ ስላደረገ:: ፈራጆቹ ባለስልጣኑን በጠረጴዛ ላይ በመጎተት እስከሚሞት ድረስ ጨፈጨፉት፡፡

በኢትዮጵያ ያለው ገዥ አካል ጋዜጠኞችን እና ጦማሪያንን አሸባሪ ብሎ በመፈረጅ ጭካኔ በተመላበት ሁኔታ እያሰቃዬ በተጨባጭ እነርሱ “የማያስፈለጉ” ናቸው በማለት በመዘባበት ላይ ይገኛል፡፡ እንዲሁም “ትኋኖች እና የሚሳቡ ነብሳት ናቸው” ይላል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ “እነርሱ መጥፎዎች፣ የተበላሸ ቅርጽ ያላቸው፣ ምንም ዓይነት ዓላማ የሌላቸው እና ትርጉምየለሽ ፍጡሮች ናቸው!” ይላል፡፡ ገዥው አካል እንዲህ በማለት ይነግራቸዋል፣ “በሳንቲም የሚሸጡ ጋዜጦች፣ መጽሔቶች እና በድረገጽ የሚለቀቁ ኃይል ያዘሉ ትርጉም የለሽ ጽሑፎች አከፋፋዮች ናቸው፡፡“ “ምንም ዓይነት ጥራት የሌላቸው እንደ ነፋስ እና እንደ አየር ምንም ዓይነት ቅርጽ የሌላቸው፣ እንደ ህዋ ባዶ የሆኑ፣ ጋዜጠኞች እና ጦማሪያን ቃላትን በጋዜጦች፣ በድረገጾች እና በብሎጎች ላይ በመሞነጫጨር የሚኖሩ ትርጉመ ቢስ ፍጡሮች ናቸው” በማለት በህዝቡ ዘንድ እምነት እንዳይጣልባቸው ይዘባበታሉ፡፡

በሴርሊንግ ታሪክ እንደ የቤተመጽሐፍት ባለሙያው ሁሉ በእስር ላይ የሚገኙት የዞን 9 ጦማሪያን እና የነጻው ፕሬስ ጋዜጠኞች ጸጥታ በተላበሰ መልኩ እንዲህ በማለት ሀሳባቸውን ይገልጻሉ፣ “እኛ ሰብአዊ ፍጡሮች ነን… ገዥው አካል ስለሚናገራቸውም ሆነ ስለማይናገራቸው ነገሮች ደንታ የለንም፡፡ አለን፣ እንኖራለን… እናም አንድ ነገር ድምጻችንን ከፍ አድርገን በተናገርን ቁጥር ያ ሀሳብ ለዘለቄታው ይኖራል፣ እኛ ወደ መቃብር ከተወረወርን በኋላ እንኳ ቀጣይነት ይኖረዋል፡፡“ ገዥው አካል “ስርዓትን መቆጣጠር እና ማስገደድ” ይችላል፣ ሆኖም ግን የዞን 9 ጦማሪያን እና ጋዜጠኞች “እንደ ቀላል ነገር በዘፈቀደ የሚከተሉ እና የሚታዘዙ አይደሉም” በውሸታሟ ሬፐብሊካዊት ኢትዮጵያ ላይ አንድ መሰረታዊ የሆነ ስህተት ተከስቷል! በእስር ላይ የሚገኙት ጋዜጠኞች እና ጦማሪያን መስፈርቱን አያሟሉም፡፡

“የማያስፈለጉት” የውሸታሟ ሬፐብሊካዊት ኢትዮጵያ ወንዶች እና ሴቶች ወይስ የማያስፈለጉት የውሸታሟ ሬፐብሊካዊት ኢትዮጵያ መሪዎች?

ሮድ ሴርሊንግ አሁን ቢኖር ኖሮ የውሸታሟ ሬፐብሊካዊት ኢትዮጵያ የጽሑፉ ትረካ መግቢያ በሚከተለው መልክ ይናገር ነበር:

(የተራኪው ድምጽ፡፡) በአሁኑ ጊዜ የአፍሪካ የፖሊስ መንግስት ገዥ የወሮበላ ስብስብ በብረት ጡንቻቸው ህዝብን ቀጥቅጠው በመግዛት ላይ ይገኛሉ፡፡ በግልጽ ለመናገር “የአፍሪካ የወሮበላ አገዛዝ” ነው በአህጉሪቱ ተንሰራፍቶ ያለው፡፡ ዋናው ዓላማቸው፣ “የተቃዋሚ ቡድኖች ምርጫችንን ዋጋ የሚያሳጣ የኃይል እርምጃ የሚወስዱ ከሆነ በሙሉ ኃይላችን እንደመስሳቸዋለን፡፡ ለዘላለም በእስር ቤት ውስጥ ሆነው ይበሰብሳሉ፡፡“ በዚህ የወሮበላ አገዛዝ ስርዓት ውስጥ በህሊና መኖር እና ማሰብ ወንጀል ነው፡፡ በስልጣን ላይ ላሉት ሸፍጠኞች እውነቱን መናገር ወንጀል ነው፡፡ ሰላማዊ ተቃውሞ ወንጀል ነው፡፡ የአንድን ሰው ህይወት ለመሸጥ ተቃውሞ ማሰማት ወንጀል ነው፡፡ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ እና ለሰብአዊ መብት ጥበቃ መከበር መቆም ወንጀል ነው፡፡ የህግ የበላይነት እንዲጠበቅ መሟገት እና መከራከር ወንጀል ነው፡፡ ሰላማዊ በሆነ መልክ መንግስታዊ ሽብርተኝነትን ለማስቆም መታገል ወንጀል ነው፡፡

በዚህ የአፍሪካ የወሮበላ አገዛዝ ጋዜጠኝነት በሞት የሚያስቀጣ ወንጀል ነው፡፡ ጦማሪነት ወይም ጸሐፊ መሆን በሞት የሚያስቀጥ ወንጀል ነው፡፡ ማንም ቢሆን በዥው አካል ላይ ትችት ካቀረበ በጆሮ ጠቢ ደህንነት ወይም በጦር ኃይል ይታፈናል፣ ይታሰራል፣ ይሰቃያል፣ እንዲሁም ይሰወራል፣ ይገደላል፡፡ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ባመጹ ጊዜ በአነጠጥሮ ተኳሾች በጥይት ይደበደባሉ፡፡ ሰላማዊ አመጸኞች በተጭበረበረ የምርጫ ውጤት ምክንያት ተቃዎሟቸውን ለማሰማት ወደ አደባባይ በወጡ ጊዜ በይፋ በጥይት በመንገዶች ላይ ይደበደባሉ፡፡ የወሮበላ አገዛዝ ስርዓት እድሜውን ለማራዘም እና በስልጣን ላይ እንደ መዥገር ተጣብቆ ለመቆየት ሲል ከውጭ የሚገኝ የገንዘብ እና የማቴሪያል እርዳታ ይጠቀማል፡፡

(ተራኪው የካሜራ እይታ፡፡) በእራስህ ኃላፊነት አዝሂች የውሸታሟ ሬፐብሊካዊት አገር ትገባለህ ፡፡ ይህ አዲስ አገዛዝ አይደለም፡፡ ይልቁንም ከዚህ በፊት የነበረው የቀድሞው ያፍዝ ያደንግዝ አገዛዝ ስርዓት ቅጥያ ነው፡፡ ከእያንዳንዱ አምባገነን መሪ በኋላ በታሪክ ሂደት ውስጥ የእራሱን አምባገነናዊ ስርዓት እና ባህል ጥሎ ካለፈው አምባገንን የሚመነጭ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ የሰብአዊ መብትን እና ነጻነትን ለማፈን የቴክኖሎጂ መስፋፋትን እና ምጥቀትን በመሳሪያነት ይጠቀማሉ፡፡ ሆኖም ግን ከእነርሱ በፊት እንደነበሩት አገዛዞች ሁሉ እነዚህም አንድ ዓይነት የመቀጥቀጫ የብረት ጡንቻ አላቸው፡፡ ምክንያታዊነት ጠላት ነው እናም እውነት አደጋ ላይ ወድቋል፡፡ (ካሜራ ወደ ተከሰሱት ተከላካዮች ፊቱን ያዞራል፡፡) እነዚህም የዞን 9 ጦማሪያን፣ ጋዜጠኞች፣ ዜና ዘጋቢዎች፣ አታሚዎች እና አርታዒኦች በወሮበላው አገዛዝ በአሸባሪነት ተከስሰው በእስር ቤት በመማቀቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊወገዱ የሚችሉ የአንድ መንግስት ዜጎች ናቸው ምክንያቱም ከስጋ የተሰሩ ፍጡሮች እና የሚያስቡበት አእምሮ እና ስቃይን የሚመለከቱበት ልብ አላቸው፡፡

“ባላስፈላጊ ሰው” ተራኪው እንዲህ በማለት ማጠቃለያ ሰጠ፣ “ባለስልጣኑ/ቻንስለሩ አሁን በህይወት የሌለው ባለስልጣን ብቻ ነበር ትክክለኛው ሰው፡፡ እርሱ አስፈላጊ ሰው አይደለም፣ እንዲሁም ያመልክበት የነበረው አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስትም አስፈላጊ አይደለም፡፡“ በስልጣን ላይ ያለ ማንም መንግስት፣ የትኛውም አካል ቢሆን እና የትኛውም የአመለካከት ፍልስፍና ጠቃሚነትን፣ ክብርን፣ የሰውን ልጅ መብት መጠበቅ ከግምት የማሰያስገባ ወዳቂ ከሆነ ያ መንግስት አስፈላጊ አይደለም፡፡

በህይወት የተለየው የውሸታሟ ሬፐብሊካዊት ኢትዮጵያ ባለስልጣን/ቻንስለር እና የመሰረተው መንግስት እና አምልኮ አስፈላጊ አይደለም!

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!

ሀምሌ 17 ቀን 2006 ዓ.ም


No comments:

Post a Comment