አንድ ዓመት ከአንድ ወር ኾኖታል። እስክንድር ነጋ ከታሰረ ከዐስራ ስምንት ወራት በኋላ ከባለቤቱ ከጋዜጠኛ ሰርካለም ፋሲል እና ከልጁ ከናፍቆት በተጨማሪ ለመጀመሪያ ጊዜ ሌላ ሰው እንዲጠይቀው በሰኔ የመጀመሪያ ወር ላይ በ2005 ዓ.ም. እንደተፈቀደለት፤ እስክንድርን ልጠይቀው ቃሊቲ ወደሚገኘው እስር ቤት አምርቼ ነበር።
ተገናኝተን ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላም እንዲህ አለኝ፤ ”ሽብርተኛ አይደለኹም፤ ሀገሬ በማንም እንድትሸበር አልፈልግም አልፈቅድምም እኔ የምፈልገው የሀገሬ ሕዝቦች በነጻነት የሚያስቡባትና የሚንቀሳቀሱባት ሰላማዊ ሀገር እንድትኾን ነው”፤ እስክንድር ”ሽብርተኛ” አይደለምና ከእስሩም በላይ ያንገበገበው ”አሸባሪ” መባሉ ነበር።
እስክንድር ”ጋዜጠኛ” ነው። እስክንድር ሲጽፍ ሀገሪቱ ላወጣችው ሕግ ራሱን አስገዝቶ፣ በሀገሪቱ ሕግ ማዕቀፍ ሥር ራሱን ገድቦ ነው። ይህም ኾኖ ግን ሲጽፍ ሕግ ተጥሶ አደጋ ሊደርስበት እንደሚችል፣ ሲጽፍ ሕግ ተጥሶ ሊታሰር እንደሚችል ያውቃል። ግን ደግሞ ቢታሰር በቀጫጭን መስመርም ቢኾን በሀገሪቱ ሕግ ተዳኝቶ ከእስር ሊለቀቅ እንደሚችል ያምን ነበር። በዚህ እምነቱም የመጣበትን ለመቀበል ተዘጋጅቶ ሀገሩ ላይ ቁጭ ብሎ ይጽፋል።
ከመጻፍ እና ሐሳቡን በአደባባይ ከመግለጽ ውጭ ያሉት መንገዶች እስክንድርን አይመቹትም። እስክንድር ሐቀኛና ቀጥተኛ የኾነ አስተሳሰብ ያለው፤ ላመነበት ነገር የታመነ ንጹህ ኢትዮጵያዊ ነው። ምናልባት ይህን ”እስክንድርን” ለመረዳት እስክንድርን ማወቅ ሊጠይቅ ይችላል። እስክንድርን ያኔ ቃሊቲ ሳገኘው ሽብርተኛ አለመኾኑን ደጋግሞ ነገረኝ። ”እስክንድር ለማነው የምትነግረው ሽብርተኛ አለመኾንህን ከቀረበብህ ክስ ጋር አንዳችም ግንኙነት እንደሌለህ እኮ ዓለም ያውቃል፤ አሳሪዎችህም ይህን ጠንቅቀው ያውቃሉ” አልኩት። እርሱን ግን ያበሳጨው ከታሰረውም፣ ከተንገላታውና ከተፈረደበትም በላይ በውሸት የተወነጀለበት “ሽብርተኝነት’’ ነበር።
አሁንም ሽብርተኝነት
አሁን እስክንድር ከታሰረ ሁለት ዓመት ከሰባት ወር ኾኖታል በእርሱ የተጀመረው ጋዜጠኛን፣ ጸሐፊዎችንና መብቱን በአደባባይ የሚጠይቀውን ሁሉ ሰብስቦ ”ሽብርተኛ” ብሎ መክሰስ ዕለት በዕለት እየጨመረ የታሳሪዎቹን ቁጥር አበራክቷል። ላለፉት ሰማንያ ሦስት ቀናት በማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ታስረው የሚገኙትና በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አንደኛ ወንጀል ችሎት በጊዜ ቀጠሮ መዝገብ በቀጠሮ ሲመላለሱ የቆዩት ጋዜጠኛ ተስፋዓለም ወልደየስ፣ ጋዜጠኛ አስማማው ኃይለ ጊዮርጊስና፣ ጋዜጠኛ ኤዶም ካሳዬ፣ የሕግ መምሕርና የዞን ዘጠኝ ጦማሪ ዘለዓለም ክብረት፣ የዞን ጦማሪዎቹ ናትናኤል ፈለቀ እና አጥናፉ ብርሃኑ ለቅዳሜ ሐምሌ 5 ቀን የዞን ዘጠኝ ጦማሪዎቹ ማኅሌት ፋንታሁን፣ በፍቃዱ ኃይሉ እና አቤል ዋበላ በዚሁ በፈረደበት ”ሽብር” ተጠርጥረው የታሰሩ ናቸው።
የምርመራ መዝገቡ በሌሉበት መዝገቡ ተዘግቶ ከሕግ ውጪ በእስር የከረሙት እነዚህ እስረኞች ግንቦት ዘጠኝ በነበረው ቀጠሮ ቀን ፖሊስ ፍርድ ቤት ቀርቦ ተጠርጣሪዎችን በሽብር መጠርጠሩን ሲናገር ወጣቶቹ በድንጋጤ አንገታቸውን ሲሰብሩ ታይተው ነበር። የሚያስደነግጠው እስሩ አይደለም፤ ሕግን አስከብራለሁ የሚል አንድ ተቋም ወጣቶችን ሰብስቦ አስሮ ባልዋሉበት የሚያውል የፈጠራ ክስ ሲጭን መስማቱ ነው። ማንነቱን ጠንቅቆ የሚያውቅ ሰው እንዲህ ያለ የውሸት ክስ ሲቀርብበት የሚሰማውን ስሜት ለመገመት ያስቸግራል። እናም ወጣቶቹ በሽብር ተግባር አለመሳተፋቸውን ያውቃሉና የቱንም ያህል የኢሕአዴግን ባህሪ ጠንቅቀው ቢያውቁት ”በሽብር እንከሰሳለን” የሚል ቅንጣት ያህል ጥርጣሬ ሊኖራቸው አይችልም። ምናባት የመጨረሻውን ጣሪያ ቢገምቱ እነርሱን አስሮ ሌሎች ጸሐፊዎችን ለማስፈራራት የተነደፈ ስልት ይኾናል ከሚል ግምታዊ መላምት ”ምርጫው እስኪያልፍ ታስረን እንቆያለን” የሚለውን ነው።
ዛሬ ጠዋት ልደታ በሚገኘው ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛው ወንጀል ችሎት ሲቀርቡም፤ ከዚሁ ሐሳብ ሊኖራቸው እንደማይችል እገምታለሁ። ወጣቶቹ ከታሰሩ ጀምሮ ጉዳያቸውን ሲከታተሉ የቆዩት ጠበቃ፣ ቤተሰብና ሌሎች ሰዎች ከትናንት ጀምሮ ፍርድ ቤት ሊቀርቡ ይችላሉ በሚል ይቀርቡበታል በተባለው ፍርድ ቤት ግቢ ክትትል ሲያደርጉ ቢቆዩም ዛሬ ጠዋት ማንም ሰው ባልተገኘበት ዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ ከፍቶባቸዋል። ነገር ግን የክስ ቻርጁ እንዲሰጣቸውና መቃወሚያ ካላቸው እንዲናገሩ ተጠይቀው ዘጠኙም እስረኞች ጠበቆቻቸው ባልተገኙበት ክሱ እንዲነበብላቸው እንደማይፈልጉ ያቀረቡት አቤቱታ ተቀባይነትን አግኝቶ ጠበቆቻቸው በተገኙበት ነገ ጠዋት እንዲቀርቡ ታዟል።
በሌላም በኩል ዛሬ ጠዋት እስረኞቹን ለመጠየቅ ማዕከላዊ ሄደው የነበሩ ቤተሰቦችና ጠያቂ ወዳጆች መግባት እንደማይችሉ ተነግሯቸው ተመልሰው ነበር። ከሰዓት በኋላም ሊጠይቋቸው በሄዱ ጊዜ ስለተከሰሱት ክስ የሚያውቁት ነገር አልነበረም። አብዛኞቹም (አብዛኞቹ ስል ስለ አስተያየታቸው መረጃ ያገኘኹት ማለቴ ነው) በሽብርተኝነት እንከሰሳለን የሚል እምነት አልነበራቸውም። ነገ የሚኾነውን ለማየት በይደር አቆይተው ቤተሰቦቻቸውን ተሰናብተው ወደ ማደሪያቸው ወደ እስር ቤት ተመልሰዋል።
የሽብርተኝነት ክሱ
የሪፖርትር ጋዜጣ ዘጋቢ ታምሩ ጽጌ ደግሞ ሰበር ዜና በሚል በጋዜጣው ድረ ገጽ ላይ፤ ሶልያና ሽመልስ (በሌለችበት)፣ በፍቃዱ ኃይሉ፣ ናትናኤል ፈለቀ፣ ማህሌት ፋንታሁን፣ አጥናፉ ብርሃኔ፣ ዘለዓለም ክብረት፣ አቤል ዋበላ፣ እንዲሁም ጋዜጠኞቹ አስማማው ኃይለ ጊዮርጊስ፣ ኤዶም ካሣዬና ተስፋለም ወልደየስ ላይ ዐቃቤ ሕግ በሽብርተኝነት ክስ መመስረቱን አስነብቦናል።
ዜናው እንደሚለው፤ ተጠርጣሪዎቹ በሕቡዕ በመደራጀት፣ የአጭርና የቅርብ ጊዜ ግብ በማቀድና በመንደፍ ከግንቦት 2004 ዓ.ም. ጀምሮ እጃቸው እስከተያዘበት ጊዜ ድረስ በፓርላማ ሽብርተኛ ተብለው ከተሰየሙት የግንቦት 7 እና የኦነግ ድርጅቶች መመርያና ሐሳብ ሲቀበሉ መቆየታቸው ተገልጿል።
ከተጠርጣሪዎቹ አንዷ የሆነችው ሶሊያና ሽመልስ የቡድኑ መሥራችና አስተባባሪ በመሆን ከ2004 እስከ 2006 ዓ.ም. መቆየቷና ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ በውጭ አገር አስተባባሪና የውጭ ግንኙነት ሆና ከመሥራቷም በተጨማሪ፣ ከግንቦት 7 ጋር ግንኙነት ለመፍጠር ተልዕኮ በመቀበል፣ አባላትን በማደራጀትና በመመልመል ስትሠራ መቆየቷን ክሱ ያስረዳል። የህቡዕ ቡድኑ ከ2004 እስከ 2006 ዓ.ም. ”ሴኩሪቲ ኢን ቦክስ” የተባለ ሥልጠና እንዲሠለጥንና እንዲደራጅ ስትመራ መቆየቷም በክሱ ተካቷል።
ሌላኛው ተጠርጣሪ በፍቃዱ ኃይሉ የአገር ውስጥ የሽብር ቡድንን በመምራትና የሥራ ክፍፍል በማድረግ፣ እንዲሁም ግብ በማስቀመጥና ስትራቴጂ በመንደፍ ከሽብርተኛ ኃይሎች ጋር ግንኙነት ሲፈጥር መቆየቱ በክሱ ተጠቅሷል።
የዓቃቤ ሕግ ክስ እንደሚያስረዳው ከሆነ ተጠርጣሪ ናትናኤል ፈለቀ ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ ካልተያዙ ግብረ አበሮቹ ጋር በመሆን የህቡዕ ድርጅቱ የአገር ውስጥ አስተባባሪ በመሆን በሥሩ ላሉት አባላት የሥራ ክፍፍል መመርያ በመስጠት፣ ከግንቦት 7 ጋር ግንኙነት በመፍጠር መመርያ ከመቀበሉ በተጨማሪ፣ ለአመፅ ተግባር የሚውል የተላከለትን 48,000 ብር ማከፋፈሉንም ክሱ ያብራራል።
ሌሎቹ ተጠርጣሪዎች በህቡዕ ድርጅቱ ውስጥ ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ መሥራችና አባል በመሆን የግንቦት 7 እና የኦነግን ስትራቴጂና ዕቅድ በመቀበል በውጭና በአገር ውስጥ ባሉ የቡድኑ አባላት ጋር ግንኙነት በመፍጠር፣ በውጭና በአገር ውስጥ ሥልጠና በመውሰድ፣ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን የሽብርተኝነት ድርጊት ለመፈጸም በማቀድ፣ በመዘጋጀት፣ በማሰርና በማነሳሳት ወንጀል መከሰሳቸውን ዓቃቤ ሕግ ያቀረበው ክስ ያስረዳል።
በሁሉም ተጠርጣሪዎች ላይ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበው ሁለተኛ ክስ እንደሚያስረዳው ተጠርጣሪዎቹ በወንጀሉና በሚያስገኘው ውጤት ተስማምተው በሕገ መንግሥት ሥርዓት የተቋቋመን መንግሥት በአመፅ፣ በሁከትና በብጥብጥ ለመለወጥ በማሰብ ከግንቦት 2004 ዓ.ም. እስከተያዙበት ዕለት ድረስ በህቡዕ ተደራጅተው፣ የሥራ ክፍፍል በመፍጠር፣ ሥልጠናዎችን በመውሰድ፣ አመፅ የሚቀሰቅሱ ጽሑፎችን በመበተን፣ የአመፅ ቡድኖችን በማደራጀት ሕገ መንግሥቱና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በአመፅና በሁከት ለመለወጥ በመሞከር ወንጀል መከሰሳቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል።
በመጨረሻ
ይህን ክስ የሰማ ማንም ሰው እነዚህ ወጣቶች ሽብርተኛ አለመኾናቸውን እንደሚረዳው ኹሉ፤ ከሳሻቸው ዐቃቤ ሕግም የውሸት ክስ እንደመሰረተባቸው ልቦናው ያውቀዋል። በተለይ ደግሞ ወጣቶቹን በቅርበት ለሚያውቃቸው ሰው በእነሱ ላይ እንዲህ ያለ ክስ ሲመሰረትባቸው ምን ዐይነት ስሜት እንደሚፈጥር ለመግለጽ ያስቸግራል። ጠንካራና ሀገር ወዳድ ወጣቶች በሽብርተኝነት ሲከሰሱ መስማት የሚፈጥረውን ቁጭት ከቃላትም በላይ ነው። ይህ ስሜት እነርሱ ላይ ሲደርስ ምን ሊኾን እንደሚችልም መገመት ያስቸግራል። እስክንድርን ከመታሰሩም በላይ ያስከፋው እንኳን ክፉ ሊያደርስባት ክፉ እንዳይነካት ቀን ከሌሊት የሚጸልይላትን የሚወዳትን ሀገሩን ገንዘብ ተቀብለህ ልትበጠብጣት ነው መባሉ ነበር።
”ዴሞክራሲያዊነቷ” የታወጀላት ሀገር ስትበደል ሕግ በሚፈቅድላቸው መሰረት ተቃውሟቸውን በጹሑፍ ያሰሙ፣ ለሀገሪቱ ሕግ ራሳቸውን አስገዝተው የጋዜጠኝነት ሥራን የሠሩ በሽብርተኞች እጅ የወደቁ እንጂ ”ሽብርተኛ” ያልኾኑት ወጣቶች ነገ ጠዋት በሽብርተኝነት መከሰሳቸውን ሲሰሙ ምን ይሉ ይኾን?
No comments:
Post a Comment