Thursday, July 24, 2014

የገነት ዘውዴ “ጠባሳ”

ከኢየሩሳሌም አረአያ

እስክንድር አሰፋ ይባላል፤ አሜሪካ ለ22 አመት ከኖረ በኋላ አገር ቤት የገባው በዘመነ ኢህአዴግ ነበር። የት/ሚኒስትሯ ወ/ሮ ገነት ዘውዴ ታናሽ ወንድም ነው። እስክንድር የቅርብ ወዳጄና ብዙ ነገር ያስተማረኝ ሰው ነው። ..ሚያዚያ 1993ዓ.ም፤ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አድማ ይመታሉ። ወቅቱ ሕወሐት ለሁለት የተሰነጠቀበት ጊዜ ነበር። የትምህርት ሚ/ሯ ገነት ዘውዴ ለተማሪዎቹ ህጋዊና ሰላማዊ ጥያቄ በቲቪ የሰጡት ምላሽ የበለጠ ተማሪውን ቁጣ ውስጥ ከተተው።

እንዳውም ፈረንሳይ ለጋሲዮን ወደሚገኘው የገነት ወላጅ እናት መኖሪያ ቤት ተማሪዎቹ ይተማሉ። በሁኔታው የተደናገጠው እስክንድር ከግቢው ሾልኮ በመውጣት ወ/ሮ ገነት ወደሚኖሩበት የገርጂ ቤታቸው ያመራል። በጊዜው ገነት ከጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ አቶ ከበደ ታደሰ ጋር ተጋብተው ይኖሩ ነበር።..አመሻሽ ላይ አቶ ተፈራ ዋልዋና የወቅቱ የፖሊስ ኮሚሽነር ወርቅነህ ገበየሁ በወ/ሮ ገነት መኖሪያ ውስጥ ተገኝተዋል። 3ቱ በክብ ሶፋ ዙሪያ ተቀምጠው ይዶልታሉ።

እስክንድር ከአቶ ከበደ (አማቹ) ጋር ፈንጠር ብለው ውስኪ እየጠጡ ነበር። የት/ሚ/ር ገነት ለፖሊስ ኮሚሽነር ወርቅነህ እንዲህ አሉ፥ « በነገው እለት ስለት (ጩቤ) የያዙ ሲቪል ፖሊሶች ተማሪዎቹን ይቀላቀሉ። በምታሰማራቸው ፖሊሶች ላይ አደጋ እንዲያደርሱ ይነገራቸው። ከዛ የሃይል እርምጃው ይቀጥል..» ሲሉ አቶ ተፈራም ሴራውን በመደገፍ ተመሳሳይ የቤት ስራ ለወርቅነህ ነገሩ። እስክንድርና አቶ ከበደ በትዝብት ያዳምጡ ነበር። ..ሌሊቱን እንቅልፍ ያልወሰደው እስክንድር ሲነጋ ለእህቱ ገነት « ምን አይነት እርኩስ ነሽ!?..ንፁህ ተማሪዎች እንዲመቱ ሴራ ትሸርቢያለሽ!?..ለካ ሰው የጠላሽ ያለነገር አይደለም!?..አሁን ኢህአዴግ ገባኝ!..» ሲል ተናግሮ ወጣ። ለ7 አመት እስክንድርና ገነት ሰላምታ ሳይለዋወጡ ዘለቁ።

የገነት የሴራ እስትራቴጂ በማግስቱ ተግባራዊ ሆነ። ተማሪዎች ተደበደቡ፣ ቆሰሉ፣ ሞቱ፣ በጅምላ እስር ቤት ተጋዙ፣ ከአገር ተሰደዱ። ..ገዢውን ፓርቲ ይደግፍ የነበረው እስክንድር ከዛ በኋላ ተጠየፋቸው። ወዳጄ እስክንድር ስለዚህ አሳዛኝ ሴራ ባወራኝ ቁጥር እጅግ በሃዘን ስሜት ተውጦ ነበር።…ይህን እንዳስታውስ ያደረገኝ በትላንትናው እለት በአንዋር መስጊድ የተፈፀመው ተመሳሳይ ሴራና ድራማ ነው። ..በሌላ ጊዜ ስለፈንጂ ድራማዎችና አጥማጆቹ ማንነት እንዲሁም ቅንብር ሴራ ልመለስበት እሞክራለሁ። ..


No comments:

Post a Comment