ኢሳት ዜና :-የብአዴን ወጣቶች ሊግ ጽ/ቤት በከተሞች የሚገኙ አውራጅና ጫኝ፤ሊስትሮ፤ሱቅ በደረቴ፤ተጽእኖ ፈጣሪ ወጣቶችን፤ በተለያዩ
አደረጃጀቶች የታቀፉ ወጣቶችን እና በአደረጃጀት ያልታቀፉ ሌሎች ወጣቶችን በወቅታዊ ጉዳዮች ዙርያ ግንዛቤ ለማስጨበጥ የተዘጋጀው ሰነድ ፣ “የጥፋት ፖለቲከኞች እንቅስቃሴ
በመላ የከተማችን ሰላም ወዳድ ወጣቶች የተደራጀና የነቃ ተሳትፎ እንዲከሽፍ ካልተደረገ በመላ ቀልቡ ወደ ልማቱ የገባው ህዝባችን በተለይ ደግሞ ተጠቃሚ እየሆነ የመጣው ወጣቱ
ከልማት ተግባሩ ሊስተጓጎል ይችላል” ሲል አስጠንቅቋል።
በብአዴን የተዘጋጀው ሰነድ ለኢሳት የደረሰ ሲሆን፣ በሰነዱ ላይ የጥፋት ሃይሎች የተባሉት አካላት በስርአቱ ላይ ከባድ ፈተና መደቀናቸውን አትቷል።
ሰነዱ የጥፋት ሃይሎቹ ” የመጀመርያው በአማራ ህዝብ ላይ የተለያየ የጀግንነት ስም እየሰጡ ከሌላው ብሄር ጋር ተቻችለን ተከባብረን በልዩነታችን ውስጥ አንድነትን እንዳንመሰርትና
ከሌሎች ብሄር ወንድሞቻችን ጋር ተቻችለን እንዳንኖር የትምክህትን እና ፀረ-ዲሞክራሲያዊ የሆነ ቅስቀሳቸውን በማራገፍ በተለይም ለዚህ ድብቅ አላማቸው ወጣቶችን መጠቀሚያ
መፈለጋቸውን፣ ይህም በቅርቡ በመላው ኢትዮጵያ ስፖርት ጨዋታ ላይ የታየው ምልክት የሚጠቀስ ነው” ብሎአል።
ይጥፋት ሃይሎች ” ከጦር የተመለሱ ታጋዮች ልዩ ድጋፍ አልተደረገላቸውም፣ ተማሪዎች ከዩኒቨርስቲ ከወጡ ድንጋይ ቀጥቃጭ ይሆናሉ፣ ድንበር ተገፋ፣ ለሱዳን መሬት ተቆርሶ ተሰጠ፣
አማራው በራሱ ብሄር ተወላጆች እተመራ አይደለም፣ የክልሉ አመራር አማራን ተሳደበ” የሚሉ ፕሮፓጋንዳዎችን በመንዛት ላይ ናቸው ሲል ሰነዱ ያትታል።
ሰነዱ ወጣቶች መውሰድ ስላለባቸው እርምጃዎችም ሲዘረዝር፣ የጥፋት ሃይሎች የሚሰሩትን የጥፋት ተግባር በዝርዝር ማጥናት፣ የትግል ስልቶቻቸውን ተከታትሎ በአግባቡ መረዳት፣
ይጥፋት ድርጊታቸውን ሁሉም እንዲያውቀው በርትቶ ማጋለጥ እና ሁሉም የተስተካከለ አቋም ይዞ እንዲታገላቸው መንቀሳቀስ፣ ወደ ህገወጥ ተግባር ሲሄዱም በማስረጃ አስደግፎ ለህግ
እንዲቀርቡ ማድረግ” የሚሉ ነጥቦች ተቀምጠዋል።
ሰነዱ በመጨረሻም “መላው የከተሞች ወጣት የጥፋት ሃይሎችን እና ጸረ-ሰላም፣ ጸረ ዲሞክራሲና ጸረ ልማት ተግባር ከመደበኛ ተግባራችን ጋር በማስተሳስር በቀጣይነት መፋለም
ይጠበቅብናል” ብሎአል።
ብአዴን እመራዋለሁ በሚለው ክልል የህዝቡ ብሶት እየጨመረ ድርጅቱም ህዝቡን ለመምራት በማይችልበት ደረጃ ላይ መድረሱን የብአዴን አባላት ለኢሳት ገልጸዋል።
በከተሞች የሚገኙ ወጣቶችን እየሰበሰቡ ” ስለ ጥፋት ሃይሎች” በየጊዜው የሚሰብኩ ቢሆንም፣ የክልሉ ወጣት ግን ብአዴንን እንደ ድርጅት እንደማይቆጥረውና አመራሩ
በወጣቱ ምላሽ ተስፋ እንደቆረጡ እንዲሁም ወጣቶችን የሚያሸፍቱ ጸረ ሰላም ሃይሎችን አጋልጡ በማለት በተቃዋሚነት የሚጠረጠሩ ወጣቶችን እየሰቃዩዋቸው ይገኛሉ።
No comments:
Post a Comment