ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም፦ ዮሐንስ ታደሰ አካ የሚባል ወጣት ስደተኛ የተስፋው ነጸብራቅ የሚል መጽሐፍ እአአ በ2013 በጀርመን አገር አሳትሞአል፤ ሳይፈራ ሀሳቡን የሚገልጽ በመሆኑ ሳይሆን አይቀርም በታወቀው ሦስተኛ ፖሊስ ጣቢያና በቃሊቲም ታስሮ ነበር፤ እሱ እንደሚለው ‹‹በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት የመሬት አስተዳደር ባለሥልጣን ውስጥ … የመሬት መሀንዲስ›› ተብሎ በ2000 ዓ.ም. ተቀጠረ፤ ከተቀጠረ በኋላ በቦዘኔነት ደመወዝ እየበላ ቆየ፤ ቀይቶ እንደተገነዘበው ‹‹… ለካስ እንኳንስ የእያንዳንዱ ሠራተኛ የሥራ ድርሻ ተለይቶ ሊታወቅ የመሥሪያ ቤቱም ሥራ አይታወቅም፤ መሥሪያ ቤቱም ሥራውን አያውቅም፤ የመሥሪያ ቤቱም ሃላፊዎች መሥሪያ ቤቱን አያውቁትም፤ ጉድ በል አዲስ አበባ! የምናወራው ስለዝነኛው አዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ነው።›› (ገ. 19)
ስለፋይሎች ስቃይ፣ ውጣ-ውረድ፣ መተሻሸት፣ መጎሳቆል ዮሐንስ ያለርኅራኄ ይተርካል፤ የእነዚህ ፋይሎች መሰቃየትና መጎሳቆል በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ላይ የሚደርሰውን ሥርዓት የያዘ ግፍ የሚያንጸባርቅ ነው፤ በግፍ ሲሰቃዩ ያየው ፋይሎችን ብቻ ሳይሆን ሰዎችንም ነው፤ በሦስተኛ ፖሊስ ጣቢያና በቃሊቲ ያየውን በብዙ ሰዎች ላይ የተፈጸመውን መከራና ስቃይ ይናገራል፤ ኢትዮጵያን ‹‹ባለማጥፋት ከጥፋተኛነት የማይድኑበት አገር›› ያደርጋታል፤ ኢሕአዴግንም ውሸታም ከማለት ይልቅ ‹‹የሌለ ማንነት አላብሶ ይሾምሃል፤ የሌለ ማንነት አላብሶ ይሽርሃል፤›› በማለት ይገልጸዋል።
ለእኔ መጽሐፉ የያዘው ሌላ ጥሩ መረጃ ስለአዲስ አበባ የቅርጫ መሬት ሰንጠረዥ ነው፤ ብዙ ሰው መሬት እንደተነጠቀ፣ ብዙ ሰው በድንገት የሰፋፊ መሬት ባለቤት እንደሆነ፣ ብዙ ሰው ቤቱ እየፈረሰበት ከነበረበት ደሀነት የባሰ ደሀነት ውስጥ እንደገባ፣ ብዙ ሰው ከመናጢ ደሀነት ተነሥቶ መሬት አልበቃ ብሎት ወደሰማይ ወደመንጠራራት እንደደረሰ እናያለን፤ እንሰማለን፤ ነገር ግን ይህንን የአዲስ አበባን ሕዝብና መሬት እየቆፈረ ግልብጥብጥ እያደረገ፣ የነበረውን የሚያጠፋና የሚጠፋውን የሚክብ ሁነት መጠኑን አናውቅም፤ መጽሐፉ ውስጥ ባለው ሰንጠረዥ ላይ የሚታየው በቅርጫ የተደለደለው መሬት ‹‹ለመኖሪያ ግንባታዎች ብቻ›› የተሰጠውን እንጂ ‹‹ለሆቴልና ለቅይጥ አገልግሎቶች›› የተሰጡትን አይጨምርም፤ አንዱ ሲከዳ ደግሞ ያንን መረጃም እናገኘዋለን።
ዮሐንስ ለመጽሐፉ የተስፋው ነጸብራቅ የሚል ስም የሰጠው ለምን እንደሆነ ግን በቅጡ አልገባኝም፤ በመጽሐፉ ውስጥ ከተገለጸው ግፍና መከራ ውስጥ ተስፋ የሚባል ነገር ጭላንጭሉም የለም፤ ጠንቋዩ እንዳለው ቢሆንምን ጨምረንበት የተስፋው ተካፋይ መሆን እንችላለን።
በአጠቃላይ ለመኖሪያ ቤት ቅርጫ ባለመብት ሆነው በሰንጠረዡ ውስጥ የገቡት አንድ መቶ ሠላሳ ስምንት ሰዎች/ኩባንያዎች ብቻ ናቸው፤ በአጠቃላይ ያገኙት መሬት ከስድስት ሚልዮን ካሬ ሜትር በላይ ነው፤ አንድ መቶ ሠላሳ ስምንቱ ተረካቢዎች ወይም ተጠቃሚዎች ያገኙት በአማካይ እያንዳንዳቸው 43748 (አርባ ሦስት ሺህ ሰባት መቶ አርባ ስምንት) ካሬ ሜትር መሬት ነው።
ያገኙት፣ ወይም ተረካቢዎቹ፣ ወይም ተጠቃሚዎቹ በአንድ በኩል፤ አስረካቢዎቹ ወይም ያጡት ወይም የተጎዱት በሌላ በኩል ስንት እንደሆኑ በእርግጠኛነት አናውቅም፤ ግን መገመት የምንችል ይመስለኛል፤ ለእያንዳንዱ ለተፈናቀለ ደሀ አንድ መቶ ካሬ ሜትር ለመኖሪያ ብናስብ እያንዳንዱ የቅርጫው ተሳታፊ 437 (አራት መቶ ሠላሳ ሰባት ያህል ደሀዎችን በአማካይ አስነቅሎአል ማለት ነው፤ ለቅርጫ የገባውን መሬት ለማግኘት ከስድሳ ሺህ በላይ ደሀዎች ከነቤተሰቦቻቸው ለባሰ ደሀነት ተዳርገዋል ማለት ነው፤ ስድሳ ሺህ ማለት ከሦስት መቶ ሺህ በላይ ግለሰቦችን ያካትታል፤ ደባሎችን ስንጨምርበት ቁጥሩ በጣም ከፍ ይላል፤ እንግዲህ 138 (አንድ መቶ ሠላሳ ስምንት) ቤተሰቦችን ወይም 690 (ስድስት መቶ ዘጠና) ግለሰቦችን ለመጥቀም ከሦስት መቶ ሺህ በላይ ሰዎች ተጎድተዋል ማለት ነው።
ይህ ሲሆን ስንት ቁም-ነገር ነው የተፋለሰው? የዜጎች ያለስጋት የመኖር ነጻነት፣ የዜጎች በአገራቸው ሀብት ላይ ያላቸው እኩልነት፣ ደሀዎችና ደካማዎች የሆኑ ዜጎች ሊኖራቸው የሚገባ የኑሮ ዋስትና፣ ይህ ሁሉ ነጻነትና መብት በግላጭ ሲገፈፍበትና ሲያለቅስ አቤት የሚልበት ዳኛ ማጣት ደግሞ ዋናው ግፍ ነው።
የአዲስ አበባ የመሬት ቅርጫ የተከናወነበት ጊዜም የመሬት አስረካቢዎችንና የመሬቱ ተረካቢዎችን ያልተፈጸመ ታሪክ ያመለክታል፤ ለመኖሪያ ተብሎ ለቅርጫ ከቀረበው መሬት 41.3 ከመቶ የሚሆነው በ1998 ዓ.ም. የተከናወነ ሲሆን 16.2 የሚሆነው በ1997 ዓ.ም. የሆነ ነው፤ የቀረው ከ1997 በፊትና ከ1988 በኋላ የተቀራመቱት ነው፤ ከዚህ በፊት አንዲህ ሰፊ የሆነ የብዙ ዜጎች መፈናቀልና የጥቂቶች ተጠቃሚ መሆን የታየው በኢጣልያ ወረራ ጊዜ ነው፤ አንዳጋጣሚ አንዳንድ ቤቶች በኢጣልያ ወረራ ጊዜና አሁንም ባለቤቶቻቸው መጎዳታቸው የሚያስደንቅ ነው።
የቅምያና የዝርፊያ ጊዜ እንዳለ ሁሉ የፍትሕና የማስተካከያ ጊዜ አለ፤ ደሀዎችን ለሚያደኸዩ ጊዜ እንዳለ ሁሉ ዘራፊዎችን ሙልጭ ለሚያወጡ ጊዜ አለ፤ ሰሎሞን ለሁሉም ጊዜ አለ ብሏልና
No comments:
Post a Comment