ሰው በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረ ነው፤ ሕይወቱ ክቡር ነው፤ ክቡር ሕይወቱን ለመጠበቅ ብዙ ፍላጎቶቹን ማሟላት አለበት፤ አንዳንዶቹ ፍላጎቶች በየዕለቱ የሚከሰቱና የሚጎተጉቱ ናቸው፤ ስለዚህም ወዲያው ካልተስተናገዱ በጤንነት ላይ መጥፎ ውጤትን ያስከትላሉ፤ምግብና መጠጥ ግዴታዎች ናቸው፤ ልብስና መጠለያም ግዴታዎች ናቸው፤ ሰው ሁሉም ነገር ከተሟላበት ከገነት ከተባረረ በኋላ በግንባርህ ላብ ብላ ተብሎ ተረግሟል፤ በሰላም በሕግ ጥላ ስር የመተዳደር ፍላጎትም አለ፤ በአለው አቅምና ችሎታ አነዚህን ፍላጎቶች ለማሟላት ይጥራል፤ ይህ ቀላል አይደለም፤ ቀላል የማያደርጉት ብዙ ምክንያቶች አሉ።አንደኛ፣ የሰውም፣ የእንስሳም፣ የእጸዋትም ሁሉ መኖሪያና መመገቢያ ምድር አንድ ነች፤ ስለዚህ ውድድሩ ከባድ ነው፤ በዚች ምድር ላይ እየኖሩ፣ ምድር የምታፈራውን እየተመገቡ፣ ውሀዋን እየጠጡ በሰላም መኖር አይቻልም፤ የሰው ልጅ ከቢምቢ ጋር ብቻ ሳይሆን ከሰው ቢምቢ ጋርም መታገል አለበት፣ ከዱር አንበሳ ጋር ብቻ ሳይሆን ከሰው አንበሳ ጋርም ነው።
ሁለተኛ፣ ፍላጎቶች የሥራ ሁሉ ምንጭ ስለሆኑ በጣም ይራባሉ፤ የመራባት አቅማቸው ከሰው ልጅ መራባትና የመፍጠር ችሎታ ጋር የተያያዘ ነው፤ በተጨማሪም ለተመቸው ሁሉ አምሮቶች ፍላጎቶች ይሆናሉ፤ ደሀዎችንና ሀብታሞችን የሚለየው አንዱ ዋና ነገር የፍላጎቶች ብዛት ነው፤ የደሀ ፍላጎቶች ከመሠረታዊ ፍላጎቶች አይርቁም፤ የሀብታሙ ፍላጎቶች ከትልቅ ቤት ወጥተው በትልቅ መኪና አድርገው በአውሮጵላን ሰማይ ይወጣሉ፤ ከዚያም አልፈው ይቧጭራሉ።
ሦስተኛ፣ በፍላጎቶች መራባት ላይ አምሮት ታክሎበት፣ እነዚህን ፍላጎቶችና አምሮቶች ማስተናገድና ማርካት ከባድ ፉክክርን ይፈጥራል፤ አብዛኛውን ጊዜ በፉክክር ላይ የሚታየው የተሠራው ቤት ትልቅነትና ውበት፣ የታረደው ሙክት ትልቅነትና ስብነት፣ የሚለብሰው ልብስ ስፌትና ውበት፣ የሚነዳው መኪና ዓይነት የሰዎቹን የኑሮ ደረጃ ያሳያል፤ በግለሰብ ደረጃ ይህ ከፍተኛ የልማት ደረጃን ያመለክታል፤ የግለሰቦችን እድገት የሚጠላ የለም፤ ጥያቄው የግለሰቦች አድገት በምን ዓይነት መንገድ ተገኘ ነው፤ ግለሰቦች በሕገ-ወጥ መንገድ ደሀውን እያሠሩና እያፈናቀሉ መሬቱን በዝርፊያና በቅሚያ ሌሎቹን እያደኸዩ ራሳቸውን የሚያበለጽጉ ነገን የማያስቡ ዕለትዋን ዘለዓለም አድርገው የሚቀበሉ ግዴለሾች፣ ወይም ጅሎች ናቸው።
በግፍ የበለጸጉ በግፍ ይደኸያሉ፤ ትናንት መንግሥቱ ኃይለ ማርያም በአንድ ቀን ስንቱን ሀብታም ባዶ እንዳደረገውና እንዳኮማተረው ይህ ትውልድ አላየም፤ ግን ሰምቷል፤ በደርግ ዘመን የመሬት አዋጁንና የትርፍ ቤቶች አዋጆች ያስከተሉትን ሐዘንና ድንጋጤ ያዩ ሰዎች እንዴት እንደገና ሊመጣ ይችላል ብለው ማሰብ ያቅታቸዋል? አንዱ የመክሸፍ ዝንባሌ እንዲህ በቅርቡ የሆነውን መርሳትና ምንም ትምህርት ሳያገኙበት ኑሮን እንደዱሮው መቀጠል ነው፤ ታሪክ የሚከሽፈው እንዲህ ትምህርት መሆን ሲያቅተው ነው፤ በየመንገዱ፣ በየቀበሌው በየስብሰባው ጥርሱን እየነከሰ የውስጥ ቁስሉን የሚያሽ ሰው ሞልቷል፤ የሚራገም ሰው ሞልቷል፤ ከተወለዱበት፣ከአደጉበትና ለስድሳ ዓመት ከኖሩበት፣ ሠርግና ተዝካር ከደገሱበት ሰፈር ተገድዶ መልቀቅ፣ በልጅነት አብረው እየተጫወቱ፣ በኋላም በትምህርት ቤት አብረው በጓደኝነት ከዘለቁ፣ በሥራ ዓለም ከገቡ በኋላ በቅርብ ወዳጅነት አብረው ከቆዩ፣ በአንድ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን በሃይማኖት በዓላት በደስታም በሐዘንም ከሃምሳ ዓመታት በላይ ያልተለያዩ ሰዎች ጉልበተኛ መጥቶ በግድ ሲበትናቸውና ሲለያዩ፣ መድኃኔ ዓለም ይበትናችሁ! ሳይሉ ይቀራሉ? በግፍ የበለጸጉ በዚህ እርግማን እየተበተኑ ይደኸያሉ፤ እግዚአብሔር በቀዳዳው ያያል፤ አትጠራጠሩ!
ሰውን ገድሎ በሬሣው ላይ ቤት ሠርቶ ሀብታም መሆን ልበ-ደንዳኖች ለአጭር ሕይወታቸው የሚጠቀሙበት ከንቱ ድሎት ነው፤ ሕገ-ወጥነት ነው፤ ግዴለሽነት ነው፤ በቅርቡ ኤርምያስ እንደነገረን የአዲስ አበባን የመሬት ዘረፋ የአዘዘው መለስ ዜናዊ ዛሬ ለአሻንጉሊት የተሠራች በምትመስል ቪላ ውስጥ በሥላሴ ቅጥር ግቢ ውስጥ ከሚገባው በላይ ድርሻውን ይዞአል፤ የሁሉም መጨረሻ ይኸው ነው፤ ኤርምያስ እንደሚነግረን የአዲስ አበባ የመሬት ዝርፊያ ከልማት ጋር የተያያዘ ሳይሆን ከዓመታት በፊት የነፍጠኞችን አከርካሪት ለመስበርና የወያኔን ትንሽ ልብ አፍኖ የያዘውን ጥላቻ ለማስተናገድ የታቀደ የሕመም መግለጫ ነው፤ ከኢትዮጵያ ሕዝብ አምስት ከመቶው ዓለም-አቀፍነት ሀበታምነት ደረጃ ላይ ሲደርስ ዘጠና አምስት ከመቶ የሚሆነው ደግሞ ወደለማኝነት ደረጃ ሲወርደ ምንም አይሆንም ብሎ ማሰብ — አይ ማሰብ የት አለ — መመኘት ሳያስቡት በድንገት የሚመጣውን የሕዝብንም፣የእግዚአብሔርንም ኃይል፤ አሜሪካ ተማሪ በነበርሁበት ዘመን (በድንጋይ ዳቦ ዘመን!) አንድ ተወዳጅ ዘፈን ነበር፡– ከቀኜ ብታመልጥ ከግራዬ አታመልጥም! የሚል።
ልማት ምንድን ነው? ከመጀመሪያውኑ መጠየቅ የነበረብን ጥያቄ ነው፤ እያንዳንዱ ሰው ኑሮውን ለማሻሻል፣ ከዛሬው ኑሮ ተምሮ ነገን የተሻለ ለማድረግ ብቻውን ወይም ከሌሎች ጋር በመተባበር የሚያደርገው ጥረት ነው፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ መክሸፍ ጎልቶ የሚታይበት የቁሞ መቅረት ጉዳይ ነው፤ እውነቱ ግን ቁሞ መቅረት አይደለም በአንጻራዊ መለኪያ ቁልቁለት መውረደረ ነው፤ እዚህ ላይ ቆም ብለን የሩቁን መክሸፍ ከቅርቡ መክሸፍ ለይተን እንመልከተው።
ዱሮ ከአክሱም ሐውልቶችና ከላሊበላ ሕንጻዎች ብንጀምር የመክሸፍ ተዳፋቱ ከባድ ነው፤ ከአክሱምና ላሊበላ የሕንጻ ሥራዎች ወደጭቃ ጎጆ ያለው ቁልቁለት ነው፤ ወደቅርብ ዘመን መጥተን በእኔ ዕድሜ የሆነውን ብናይ ወደ1950 አካባቢ ኢትዮጵያ በማናቸውም ነገር የአፍሪካ መሪ ሆና ነበር፤ ዛሬ ያለችበትን ሁሉም ያውቀዋልና አልናገርም፤ ልማት የሚባለውን ነገር ገና አልጀመርንም፤ ልማት በዝርፊያ፣ ልማት በትእዛዝ አይመጣም፤ ልማት የምንለው የማኅበረሰቡን እድገት እንጂ የጥቂት ሰዎችን መንደላቀቅ አይደለም፤ ልማት የምንለው ከእያንዳንዱ ዜጋ ነጻነትና ፈቃድ ጋር የተያያዘውን የጋራ እድገት እንጂ በጥቂት ጉልበተኞች የአገሩን ዜጎች በአገራቸው ስደተኞች የሚያደርገውን አፍርሶ መሥራት አይደለም።
No comments:
Post a Comment