Wednesday, December 2, 2015

በኦሮምያ የተለያዩ አካባቢዎች የተነሳው ተቃውሞ አድማሱን እያሰፋ ነው

ኀዳር ፳፪ (ሃያ ሁለት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የፌደራል መንግስት ያወጣውንና የኦሮምያ ክልል ምክር ቤት ወይም ጨፌ ኦሮምያ በአዲስ አመት የስራ ዘመኑ ያጸደቀው አዲሱን የአዲስ አበባ ካርታ ተከትሎ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ከደምቢዶሎ እስከ ሃረር ተዛምቷል። ተቃውሞውን ተከትሎ በብዙ የዩኒቨርስቲዎች፣ የሁለተኛና አንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል።

የኦሮሞ ፌደራሊስት ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኦፌዴን) ሊቀመንበር አቶ በቀለ ነገዓ እንዲሁም የኦሮሞ ህዝብ ኮንግረስ ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና በድርጅታቸውና በመድረክ ስም በመንግስት እየተወሰደ ያለውን እርምጃ አውግዘዋል።
ተቃውሞው አድማሱን እያሰፋ በመምጣቱ እንዲሁም መንግስት ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሰራዊት አባላት በማሰማራቱ፣ በተማሪዎች ላይ የደረሱ ጉዳቶችን በትክክል ለማወቅ እንዳልተቻለ፣ ይሁን እንጅ ከሞት እስከ አካል መጉደል የሚደርሱ ጉዳቶች መፈጸማቸውን ሁለቱም ፖለቲከኞች ተናግረዋል።
አቶ በቀለ ነገአ የተማሪዎችን ተቃውሞ ህዝባዊ ያሉት ሲሆን፣ አንዱ የሌላው መብት ሲነካ ዝም ብሎ ማዬቱን አቁሞ በውስጥም በውጭም ያለው ኢትዮጵያዊ በአንድነት እንዲነሳ ጥሪ አቅርበዋል።
ሁለቱም መሪዎች ተቃውሞ ስለሚደረግባቸው አካባቢዎች ፣ የክልሉ ምክር ቤት ስለገባበት አጣብቂኝ፣ ስለመንግስት እርምጃና ስለድርጅታቸው አስተዋጽኦ የሰጡትን መግለጫ ከዜናው መጨረሻ እናቀርባለን።
በተመሳሳይ ዜና ደግሞ በኦሮምያ ክልል የተጀመረውን ተቃውሞ ተከትሎ በአዲስ አበባ የጸጥታው ሁኔታ እንዲጠናከር ትእዛዝ መተላለፉን የደረሰን መረጃ ያመለክታል። የፌደራል ፖሊሶች በተጠንቀቅ እንዲቆሙ እንዲሁም የደህንነት ሰራተኞች ማንኛውንም እንቅስቃሴ በንቃት እንዲከታተሉ ተዘዋል።

No comments:

Post a Comment