Tuesday, December 15, 2015

ገዢው ፓርቲ በንጹሃን ዜጎች ላይ የሚወስደውን እርምጃ አጠናክሮ ቀጥሎአል

ታኀሳስ ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በኦሮምያ የተነሳውን ህዝባዊ አመጽ ተከትሎ የገዢው ፓርቲ ወታደሮች በንጹሃን ዜጎች ላይ የሚወስዱትን እርምጃ አጠናክረው የቀጠሉ ሲሆን፣ ዛሬ ማክሰኞ ብቻ ከ11 ያላነሱ ሰዎች ተገድለዋል። የዛሬውን ጨምሮ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ በገዢው ፓርቲ የተገደሉ ሰዎች ቁጥር ከ50 በላይ መሆኑን መረጃዎች አመልክተዋል።

በጊንጪ በወታደሮች የተገደለውን ሰይፉ ቱራን ለመቅበር የወጡ ነዋሪዎች፣ ባስነሱት ተቃውሞ በጋሌሳ ትምህርት ቤት አስተማሪ የሆኑት መምህር በቀለ ደርሶን ጨምሮ አቶ አበበ ገቢሳና አቶ መርሳ በጂ የተባሉ አርሶአደሮች ተገድለዋል።
በወለንቆሚ በነበረው ግጭት ደግሞ 8 ሰዎች በአጋዚ የጦር አባላት መገደላቸው የታወቀ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል 2ቱ የ9ኛ ክፍል ሴት ተማሪዎች ናቸው።
በአወዳይ ዛሬ ነዋሪዎች ከፍተኛ ተቃውሞ አድርገው የዋሉ ሲሆን፣ ወደ ድሬዳዋና ሀረር የሚደረገው የተሽከርካሪ ጉዞ ተቋርጦ አርፍዷል። በሃረርም ግጭት ይነሳል በሚል ነዋሪዎች ልጆቻቸውን ከትምህርት ቤት ሲያወጡ ታይተዋል። የሃረሪ ፖሊሶች ዩኒፎርማቸውን በመቀየር ኦሮሞውንና ሀረሪውን ለማጋጨት እየንተቀሳቀሱ መሆኑንም አስተማማኝ መረጃ ደርሶናል። ትናንት በቡራዩ የተደረገውን ተቃውሞ ተከትሎ በርካታ ወጣቶች ወደ እስር ቤት ተግዘዋል።
በአብዛኛው የኦሮምያ አካባቢዎች የሚታየውን ተቃውሞ ተከትሎ መንግስት የጸጥታ ሃይሎችን ወደ አካባቢው በብዛት እያሰማራ ነው። በአዲስ አበባም መንግስት ጥበቃውን እያጠናከረ ነው። ጠዋት ካዛንችስና ትምህርት ሚ/ር በር ላይ ብረት ለበስ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ቆመው የታዩ ሲሆን፣ የፌደራልና የአዲስ አበባ ፖሊሶችም በፒካፕ መኪኖች ተጭነው ቅኝት ሲያደርጉ አርፍደዋል።ከቤተመንግስቱ በአንድ ኪሎ ሜትር ርቀት ዙሪያ ከፍተኛ ጥበቃ በመካሄድ ላይ ነው።
መንግስት በዘፈቀደ በኦሮሞ ተወላጆች ላይ የሚፈጽመው ግድያ ያሳሰበው መድረክ መግለጫ አውጥቷል። በመግለጫውም የኢህአዴግ ህገወጥ እርምጃዎች እንዲቆሙ ጠይቋል።
የገዢው ፓርቲ ድርጊት የሀገራችንን ደህንነትና የሕዝቦቻችንን እኩልነትና አንድነት ለማይሹ ኃይሎች አፍራሽ እንቅስቃሴ ቀዳዳ እየሰጣቸው መሆኑ መድረክን በእጅጉ ያስሰበዋል የሚለው መግለጫው፣ በጸጥታ ሃይሎች የተገደሉ የ32 ሰዎችን ስም ዝርዝር ይፋ አድርጓል። ከመቶ ባለይ ዜጎች መቁሰላቸውን፣ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ለእስር መዳረጋቸውን መድረክ አስታውቋል፡፡
መድረክ በቅርቡ በጎንደር ከተማ በሚገኘው ወሕኒ ቤት በእስረኞች ላይ የተፈጸመው ግዲያ እንዳሳሰበውም ገልጿል። በመግለጫው ማጠቃለያም ለከተማዋ ልማት የሚወጡ እቅዶችም የሕገመንገሥቱን ድንጋጌ የሚያከብሩ ሆነው የአከባቢውን አርሶ አደሮች መብትና ጥቅም በሚገባ የሚያስጠብቅ እንዲሆኑ፣ በቅርቡም መንግሥት ሕገወጥ እርምጃ ለመውሰድ በተንቀሳቀሰበት ምክንያት በኦሮሚያ ክልል ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፎችን ባደረጉና በሌሎችም ሰላማዊ ዜጎች ላይ እየተፈጸመ ያለው የኃይል እርምጃ በአስቸኳይ እንዲቆም፣ እስከአሁን የዜጎችን ሕይወት በሕገወጥነት ያጠፉና ሌሎች ጉዳቶችን ያደረሱ የመንግሥት አካላትም ለሕግ እንዲቀርቡና ለሟቾቹ ቤተሰቦችም ተገቢው ካሳ እነዲከፈላቸው እንዲደረግ ፣ በቅርቡ በጎንደር ከተማ በሚገኘው ወሕኒ ቤት የተገደሉ በርካታ ዜጎች ጉዳይ በአስቸኳይ ተጣርቶ የሰላማዊ ዜጎችን ሕይወት ያጠፉና ጉዳት ያደረሱ አካላት ለፍርድ እንዲቀርቡና ለሟቾቹ ቤተሰቦችም ተገቢው ካሳ እንዲከፈላቸው እንዲደረግ እንጠይቃለን ብሎአል።
ህዝቡ ሕገመንግሥታዊ መብቶቹን ለማስከበር ሰላማዊ ትግሉን እንዲያጠናክርም መድረክ ጥሪው አቅርቧል። የአፍሪካ ቀንድ የሰብአዊ መብት ሊግ በበኩሉ በመንግስት ታጣቂዎች የተገደሉ 40 ሰዎችን ስም ዝርዝር ይፋ አድርጓል። የድርጅቱ ዳይሬክተር አቶ ጋሮማ በቀለ የሟቾች ቁጥር ከዚህም በላይ ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል።
የተለያዩ ብሄረሰቦችን እርስ በርስ ለማጋጨትና አቅጣጫ ለማሳት የሚደረገውን ሙከራ ኢትዮጵያውያን በጋራ እንዲያከሽፉትም ጥሪ አቅርበዋል ።

No comments:

Post a Comment