Monday, August 3, 2015

ለሳሙኤል አወቀ መታሰቢያ ደም ተለገሰ

ሐምሌ ፳፯ (ሃያ ሰባት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ሰኔ 8 ቀን 2007 ዓ.ም. ደብረማርቆስ ከተማ ውስጥ ለተገደለው ወጣት ሳሙኤል አወቀ መታሰቢያ ሀምሌ 26 ቀን 2007 ዓ.ም በሰማያዊ ፓርቲ ፅ/ቤት ደም ተለግሷል፡፡

የሰማያዊ ፓርቲ አባላት፣ ደጋፊዎችና ሌሎችም ሳሙኤልን ለማስታወስ የተገኙ ግለሰቦች ደም ሰጥተዋል፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ በዛሬው ቀን ደም መስጠት ያስፈለገው ሳሙኤልን ለማስታወስ መሆኑን ገልጾ በቀጣይም ሳሙኤልን የሚዘክሩ ሌሎች ፕሮግራሞች እንደሚደረጉ ገልጾአል፡፡
አቶ ዮናታን አክሎም ‹‹እንደሚገድሉት እያወቀ ትግሌን አደራ ያለውን ወጣት ሳሙኤልን ደም በመለገስና በሌሎች ፕሮግራሞችም እንዘክረዋለን፡፡ የምንታገለው ስርዓት ገዳይ ቢሆንም እኛ ግን በደማችን ነፍስ እናድናለን›› ብለዋል።
በሌላ በኩል አቶ አብርሃም ጌጡ በቤተሰብና በጠበቃ እንዳይጠየቅ ተከልክሏል።
በአቶ ማሙሸት አማረ ካቢኔ የመኢአድ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ የነበረው አቶ አብርሃም ጌጡ በቤተሰብና በጠበቃው እንዳይጠየቅ መደረጉን ቤተሰቦቹ ገልጸዋል፡፡አቶ አብርሃም ጌጡ ሰኔ 12 ቀን 2007 ዓ.ም ቤቱ በፖሊስ ተከቦ ከታሰረ በኋላ 5ኛ ፖሊስ ጣቢያ ታስሮ ጉዳዩን በልደታ ፍርድ ቤት ሲከታተል ቆይቷል፡፡
ፍርድ ቤቱ ለፖሊስ ተደጋጋሚ ቀጠሮ ከሰጠው በኋላ ምርመራዬን አልጨረስኩም ላለው ፖሊስ ፣ ‹‹የመጨረሻ ቀጠሮ›› በሰጠበት ወቅት ፖሊስ ወደ ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ በማዛወር አራዳ ፍርድ ቤት ሲያቀርበው እንደቆየ ተገልጾአል፡፡
አቶ አብርሃም ጌጡ በሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ታስሮ በነበረበት ወቅት ከፍተኛ ድብደባ እንደደረሰበት የገለጹት ቤተሰቦቹ ሀምሌ 12 ቀን 2007 ዓ.ም. ወደ ማዕከላዊ ምርመራ መዛወሩን ገልጸዋል፡፡
ይሁንና ወደ ማዕከላዊ ከተዛወረ በኋላ በቤተሰብና በጠበቃውም እንዳይጠየቅ በመከልከሉ ያለበትን ሁኔታም ለማወቅ መቸገራቸውን ገልጸዋል፡፡ ‹‹ወደ ማዕከላዊ እንደተዛወረ ብናውቅም በአሁኑ ወቅት የት እንዳደረሱት እርግጠኛ መሆን አልቻልንም›› ሲሉ ቤተሰቦቹ መናገራቸውን ነገረ ኢትዮጵያ ዘግቧል።

No comments:

Post a Comment