ነኅሴ ፰ (ስምንት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን በማንዱራ ወረዳ ቴዎድሮስ ስሜነህ የተባለ ሰው በፌደራል ፖሊስ አባላት ተደብድቦ ተገድሏል።
ቴዎድሮስ ከትናንት በስቲያ በፌደራል ፖሊስ አባላት ከቤቱ ተይዞ ጭካኔ በተሞላበት መንገድ ሲደበደብ አርፍዷል። ድብደባውን ተከትሎም ህይወቱ ወዲያውኑ ማለፉን ፣ የቀብሩ ስነስርዓት ትናንት መፈጸሙን ለማወቅ ተችሎአል። ቴዎድሮስ የተቃዋሚ ሃይሎች አባል ነህ ተብሎ ክትትል ሲደረግበት ቆይቷል።
ወጣት ቴዎድሮስ በሰላማዊ ትግል የሚያምንና ህዝቡን ለተቃውሞ ሲያስተባብር የቆየ ቢሆንም፣ ይህን እንቅስቃሴውን ያልወደዱት የመንግስት ባለስልጣናት ትግሉን እንዲያቆም ሲያስጠነቅቁት ቆይተዋል። ቴዎድሮስ ትግሉን እንደማያቆም መናገሩን ተከትሎ ወጣቶችን እየመለመለ ለአርበኞች ግንቦት 7 ይልካል የሚል ክስ የቀረበበት ሲሆን፣ ባለስልጣናቱ የልዩ ሃይል አባላትን ልከው ካስያዙት በሁዋላ፣ ለፍርድ ሳያቀርቡ፣ ፍጹም ጭካኔ በተሞላበት መንገድ መደብደባቸውንና ይህንን ተከትሎ ህይወቱ ወዲያው ማለፉን የአይን እማኞች ለኢሳት ገልጸዋል።
ሌሎች ወጣቶችም በተመሳሳይ መንገድ እየተፈለጉ መሆኑን የሚናገሩት የአካባቢው ነዋሪዎች፣ በክልሉ ከፍተኛ የሆነ የዘር መድሎ እንደሚካሄድና ኢላማ የተደረጉት የአንድ ብሄረሰብ አባላት ብቻ መሆናቸውን ይናገራሉ።
No comments:
Post a Comment