ሐምሌ ፲ (አስር) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ሴንተር ፎር ስትራቴጂክ ኤንድ ኢንተርናሽናል ስተዲስ የተባለው ተቋም " ከአሜሪካ ጉዞ በፊት የአሜሪካ ፖሊሲ በኬንያና በኢትዮጵያ" በሚል ርእስ ባዘጋጀው ፓናል ውይይት ላይ የተገኙት በጆርጅ ማሶን ዩኒቨርስቲ የግጭት አስወጋጅ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ቴሬንስ ሊዮንስ እንደተናገሩት ኢህአዴግ በቅርቡ በኤርትራ ላይ ጦርነት ለማወጅ የሰጠውን መግለጫ አሜሪካ እንደማትደግፈውና እንደማትተባበር በግልጽ ማስታወቅ እንደሚገባት መክረዋል። የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ባለስልጣናት ኢህአዴግን "አምባገነኑ ጓደኛችን" በማለት እንደሚገልጹት የተናገሩት ፕሮፌሰሩ፣ አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት በ3 ምሰሶዎች ላይ አረፉ መሆኑን ተናግረዋል። ኢትዮጵያ የሚመሰገን የኢኮኖሚ እድገት ብታገኝም፣ ፕሬዚዳንት ኦባማንም ሆነ ሌሎች ኢትዮጵያን ለሚጎበኙት የምመክራቸው ታች ወርደው የህዝቡን ኑሮ እንዲያዩ ነው ብለዋል። ሽብረተኝነትን በመዋጋትም በኩል በኢትዮጵያና በአሜሪካ መካከል የተለያዩ ፍላጎቶች ስላሉ አሜሪካ ጥቅሙዋን በትክክል መግለጽ እንደሚገባትና እነዚህ ግንኙነቶች የአሜሪካን ዘላቂ ጥቅም ያረጋግጣሉ ወይ የሚለውን መመለስ እንደሚገባ ተናግረዋል። ሰብአዊ መብትን በተመለከተ ኢህአዴግ 100 በመቶ አሸንፌያለሁ ማለቱ፣ በራሱ አገዛዙ ምን ያክል ጠንካራ አምባገነን መሆኑን ያሳያል ያሉት ፕሮፌሰሩ፣ የአሜሪካንና የኢህአዴግን ግንኙነት ከግብጽና ከፓኪስታን አምባገነን መንግስታት ጋር ካለው ግንኙነት ጋር አመሳስለውታል። ኢትዮጵያ ሲቪል ሶሳይቲውን በሙሉ ሽባ የሚያደርግ ህግ ማውጣቱንም አክለዋል። የአሜሪካ ባለስልጣናት በኢትዮጵያ ላይ ተጽኖ ለማድረግ ያላቸው ጉልበት አነስተኛ መሆኑን እንደሚገልጹ የገለጹት ምሁሩ፣ የፕሬዚዳንቱ ጉብኝት በራሱ ትልቅ ጉልበት መሆኑን ገልጸዋል። ጋዜጠኞች እንዲፈቱ፣ የኢትዮጵያ ሙስሊም መሪዎች እንዲፈቱ፣ የሲቪክ ተቋማት ህግ እንዲሁም የጸረ ሽብር ህጉ እንዲለወጥ ወይም እንዲሻሻል ፕ/ት ኦባማ ተጽኖ ማድረግ እንዳለባቸው ተናግረዋል። ኢትዮጵያ አካባቢውን ታረጋጋለች የሚለው አስተሳሰብ ጥያቄ ውስጥ መግባት እንዳለበት ያመለከቱት ፕሮፌሰሩ፣ ኢትዮጵያ በሶማሊያና ኤርትራ የምትሰራውን የማተራመስ እንቅስቃሴ በማንሳት አሜሪካ የወደፊት ጥቅሟን በማሰብ ጉዳዩን እንደገና ማየት አለባት ብለዋል። ሰሞኑን የኢህአዴግ መንግስት ያወጣው በእብሪት የተሞላ የጦርነት ነጋሪት አደገኛ መሆኑን የገለጹት ፕ/ሩ ፣ ፕሬዚዳንት ኦባማ በዚህ ጉዳይ ላይ ከእናንተ ጋር አንተባበርም በማለት ለኢህአዴግ ባለስልጣናት በግልጽ ሊናገሩ እንደሚገባ ጠቁመዋል። የኤርትራን ድንበር ዘልቆ መግባት ከፍተኛ ቀውስ ያስከትላል ሲሉ ፕ/ት ቴሬንስ አስጠንቀዋል :: ሌሎች ፓናሊስቶች በኢትዮፕያና በኬንያ ስላለው ሰብአዊ መብት ጥሰት ፣ ፕ/ት ኦባማ መከተል ስለሚገባቸው ፖሊሲ አስተያየት ሰጥተዋል። በውይይቱ ላይ ከኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕና ከሂውማን ራይትስ ወች የተወከሉ ተናጋሪዎች ሲቀርቡ፣ በኬንያ የቀድሞው የአሜሪካ አምባሳደር ማርክ ቤላሚም ተገኝተዋል፡፡
No comments:
Post a Comment