Wednesday, July 8, 2015

ፍ/ቤቱ በእነ ዘላለም ወርቃገኘሁ ላይ ብይን ሳይሰጥ ቀረ

በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር
       በእነ ዘላለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ የተመሰረተባቸው የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችና ሌሎች በተመሳሳይ መዝገብ የተካተቱ ተከሳሾች ላይ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለዛሬ ተከሳሾች በነጻ ይሰናበቱ ወይስ ይከላከሉ በሚለው ላይ ብይን ይሰጣል ተብሎ ተጠብቆ የነበር ቢሆንም ብይኑ ሳይሰጥ ተቀጥሯል፡፡
የሰማያዊ ፓርቲ፣ የአንድነት እና የዓረና ትግራይ አመራሮች የሺዋስ አሰፋ፣አብርሃ ደስታ፣ ሀብታሙ አያሌው እና ዳንኤል ሺበሽን ጨምሮ 10 ተከሳሾች ዛሬ ሐምሌ 1/2007 ዓ.ም በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ 19ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው ፍርድ ቤቱ መዝገቡን መርምሮ ብይን እንዳልሰጠ ተገልጾላቸው ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል። ፍርድ ቤቱ የአቃቤ ህግ ምስክሮች ቃል በጽሑፍ ተገልብጦ ከመዝገቡ ጋር እንደተያያዘለት ገልጾ፣ ነገር ግን ተከሳሾች በጠበቆቻቸው አማካኝነት አቃቤ ህግ አለኝ ስላለው ተጨማሪ የሰነድ ማስረጃ ጉዳይ ያቀረቡትን መቃወሚያ መርምሮ ብይን ስላልሰጠበት ዋናው ጉዳይ ላይ ለመበየን አለመቻሉን አስረድቷል፡፡ ስለሆነም ተከሳሾች ባቀረቡት የተጨማሪ ሰነድ መቃወሚያ ላይ ብይን ለመስጠት ለነገ ሐምሌ 2/2007 ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ በሌላ በኩል ችሎት በመድፈር ተፈርዶባቸው ከቂሊንጦ ወደ ቃሊቲ የተዘዋወሩት አብርሃ ደስታ፣ ዳንኤል ሺበሽ እና የሺዋስ አሰፋ በቃሊቲ እስር ቤት አያያዝ ላይ ቅሬታ አሰምተዋል፡፡ በዚህም ዳንኤል ሺበሽ ህክምና እያገኘ እንዳልሆነና ምክንያቱ ሳይገለጽለት ጠያቂ እንደተከለከለ በመጥቀስ አቤቱታውን ቢያሰማም ፍርድ ቤቱ በቀጣይ ቀጠሮ በጽሑፍ ይዘህ ቅረብ የሚል ምላሽ ሰጥቶታል፡፡ ዳንኤል በበኩሉ ፍርድ ቤቱ እንዲህ ቸልተኛ የሚሆን ከሆነማ አቤቱታየን አንስቻለሁ ብሏል፡፡

No comments:

Post a Comment