ኢሳት ዜና (ሐምሌ 07 2007)በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ውስጥ ተንሰራፍቶ ያለውን አፈናና የአንድ ብሄር የበላይነት በመሸሽ በርካታ ወታደሮች የትጥቅ ትግሉን በመቀላቀል ላይ መሆናቸውን በሽግግር መንግስት ወቅት የኢትዮጵያ ዲፕሎማት የነበሩት አቶ መሀመድ ሀሰን ለኢሳት አስታወቁ።
ሰሞኑን ወደ ኤርትራ በመጓዝ በዚያ የሚገኘውን የትጥቅ ትግል መመልከት እንደቻሉ የተናገሩት የቀድሞው ዲፕሎማት፣ በቆይታቸው ከሰራዊቱ ጋር የተሰደዱ በርካታ ወታደሮችን እንዳነጋገሩ ገልጸዋል።
እንደ ፈረንጆች አቆጣጠር በ 1994 አ.ም ስራቸውን በገዛ ፍቃዳችው እንዳቋረጡ የተናገሩት አቶ መሀመድ ሀሰን፣ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ብሄራዊ ጦር የተባለ ሰራዊት እንዳሌላትና ሁኔታው የአፓርታይድ ጦር ሊያስብለው እንደሚችል አስረድተዋል።
በጦሩ ውስጥ ሀገራዊ ስሜት የለም ማለት ይቻላል የሚሉት አቶ መሀመድ የአንድ ብሔር ተወላጆች ብቻ በኦፊሰርነትና በተለያዩ ሀላፊነት ቦታዎች ተመድበው እንደሚገኙ ገልጸዋል።
ነዋሪነታቸውን በቤልጂየም ያደረጉትና የቤልጂየም የሰራተኛው ፓርቲ አባልና አመራር የቀድሞው የኢትዮጵያ ዲፕሎማት መሀመድ ሀሰን የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት በአሁኑ ወቅት በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ መሆናቸውን መረዳት እንደሚችሉ በቃለ ምልልሳቸው አመልክተዋል።
ሰሞኑን በአርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነት ዴሞክራሲ ንቅናቄ የተጀመረው ጥቃትም በመንግስት ላይ አለመረጋጋትን ሊያመጣ እንደሚችልም ገልጸዋል።
በስልጣን ላይ ያለው ገዢው መንግስት የከፋፍለህ ግዛን ስርአት ዘርግቶ እንደሚገኝ ያስታወቁት መሀመድ ሐሰን በአማራ፤ ኦሮሚያ፤ ጋምቤላ፤ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልና የተለያዩ አካባቢዎች የተለያዩ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች ሲፈጸሙ ቆይተዋል ብለዋል።
No comments:
Post a Comment