ኢሳት ዜና :-ከወራት በፊት 111 በመቶ የደሞዝ ጭማሪ ያደረገው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሺን፣ በአማራ እና በኦሮምያ ክልል በተከታታይ ተገቢ የሆነ የደሞዝ ማስተካካያ አላደረገም በሚል ጥያቄ ሲቀርብብት ቆይቷል።
ሰሞኑን የካቢኔ አባላት ተሰብስበው የአማራ ክልል ጋዜጠኞች ከግንቦት ሰባት እና አርበኞች ግንባር እንዲሁም የኦሮምያ ክልል ጋዜጠኞች ከኦነግ ጋር የሚሰሩትና ለኢሳት መረጃ በማቅረብ በክልሎች መንግስት ላይ ህዝቡ አመኔታ እንዲያጣ የሚያደርጉት በገንዘብ ችግር የተነሳ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል።
ይህን ተከትሎም የሁለቱንም የክልል መገናኛ ብዙሃን በቦርድ ሰብሳቢነት የሚመራው የመንግስት ኮሚኒኬሺን መስሪያ ቤት ከሌሎች የመንግስት መስሪያ ቤት ሰራተኞች በተለየ ከ80 እስከ 100 ፐርሰንት ጭማሪ እንዲያገኙ ተወስኖላቸዋል፡፡
በዚህ ውሳኔ መሰረት የአንድ አስተባባሪ ደሞዝ እንደ የስራ መደቡ 9 ሺ 810 ብር እንደሚከፈለው ታውቋል፡፡ ጭማሪው ከሌሎች መስሪያ ቤቶች ጋር ሲነፃፀር ከመቶ ፐርስንት በላይ ብልጫ አለው፡፡
ይህንን ጭማሪ ተከትሎ ተጠቃሚ ያልሆኑ ደጋፊ የስራ ሂደት ሰራተኞች ማለትም ሾፌር ፤ ላይብረሪ ፤ፅሃፊዎች ፤ ጥበቃ እና ዝቅተኛ የስራ መደብ ተደርገው የተቆጠሩት የፋይናንስ መደብ ሰራተኞች ተቃውሞ ቢያነሱም፣ “ልቀቁ ሌላ ይቀጠራል” በመባላቸው ቅሬታቸውን ለዘጋቢያችን ገልጸውላታል።
ደጋፊ ሰራተኞች ክስ የመሰረቱ ቢሆንም ይህ ነው የሚባል ውጤት አላገኙም።
No comments:
Post a Comment