ታኀሳስ ፲፬(አስራ አራት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ታህሳስ 10 /2007 ዓ.ም ለአምስት ሰዎች ሞትና ለበርካቶች አካል መጉደል ምክንያት በሆነው የተቃውሞ ሰልፍ ዙሪያ የገዢው መንግስት አስቸኳይ መግለጫ እንዲሰጡ ያስገደዳቸው የኃይማኖት አባቶች በመስቀል አደባባይ ዙሪያ ላይ የቀረበውን ጥያቄ በደስታ እንደተቀበሉት በመግለጫቸው መስጠታቸው እና ምዕመኑን እንደ ጥፋተኛ በመቁጠር ማግለላችው እንዳበሳጫቸው በትላንትናው ዕለት በቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ግቢ በሚስጥር የተሰባሰቡት የእምነቱ ተከታዮች ተናግረዋል፡፡ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉና ድምጻቸው እንዳይሰማ የፈለጉት የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እምነት ተከታይ የእምነቱ ተቆርቋሪዎች የቅዱስ ሚካኤልን በአል ለማክበር በተሰባሰቡበት ጊዜ ባደረጉት ውይይት ” እኛን የሚወክሉ የሃይማኖት አባቶች ለህዝቡ ይቆረቆራሉ እንጅ በህዝብ አይፈርዱም፡፡ ” በማለት ከምዕመናኑ ጎን በመቆም ድርጊቱን ያወገዙ ቢኖሩም አንዳንድ አባቶች ግን ምዕመኑን እንደ ጥፋተኛ መቁጠራቸው በከፍተኛ ሁኔታ ስሜታችውን እንደጎዳው ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡የተቃውሞ ሰልፉ በተካሄደ እለት ከሰዓት በኋላ መግለጫ ከሰጡት መካከል ስብሰባውን የመሩት አባት ” የተሰጠንን የቤት ስራ አከናውነናል፡፡” በማለት ለከንቲባ ጽሕፈት ቤት ለማሳወቅ
መሄዳቸውን እንደተናገሩ ያሳወቁ መሆኑን ተናግረው በነበረው የሃይማኖት መሪዎች ስብሰባ ያልተስማሙ አባቶች ምእመኑን በማስተባበር ሰላማዊ ሰልፍ ለመውጣት ወረቀት እየበተኑ መሆኑን በመናገር በህዝበ ክርስቲያኑ ላይ ርምጃ እንዲወሰድ መንገድ አመቻችተዋል በማለት አማኞች ድርጊቱን አውግዘዋል፡፡የሃይማኖት አባቶች በዕለቱ በሰጡት መግለጫ ” ሁሉም የቤተ ክርስቲያኒቱ መሪዎችና ተጠሪዎች ለተቃውሞ የወጡትን ምዕመናን ከየት እንደመጡ አናውቃቸውም፡፡የቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት አይደሉም፡፡ ” በማለት መናገራቸው ክርስቲያኑን እንደ ባእድ በመቁጠር ሃይማታዊ ሳይሆን ፖለቲካዊ አቋም በሚያንጸባርቅ ንግግር መሆኑ እንዳሳዘናቸው ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ከመንግስት ጋር የተጣበቁት የቤተ ክርስቲኒቱ አመራሮች ባያውቁንም አምላካችን ግን ያውቀናል ሲሉ የተሰሙት የእምነቱ ተከታዮች ዛሬ በጥይት ተደብድበን እንቅስቃሴውን ያቆምን ቢመስላቸውም እኛ ግን እርስ በርስ በመነጋገር የእምነታችን ድንበር ለማስከበር በቆራጥነት ተነስተናል በማለት የገዢው መንግስት አንዳች እንቅስቃሴ ቢጀምር በተቀናጀ መልኩ ተቃውሟቸውን እንደሚገልጹና አጸፋውን እንደሚመልሱ ተናግረዋል፡፡የሃይማኖቱ መሪዎች “ከመንግስት ጎን አብረን እንቆማለን ፡፡ሃይማኖትን ሰበብ በማድረግ ምርጫውን ለመበጥበጥ የሚደረግ እንቅስቃሴ ነው፡፡” በማለት ሃይማኖትን ከፖለቲካ ጋር ለማገናኘት መሞከራቸው ከዕምነት አባት የማይጠበቅ መሆኑን ተናግረው ይህ ማለት ገዢው መንግስት በቀጣይ ለሚወስደው እንቅስቃሴ መንገድ መክፈታቸው አግባብ አለመሆኑ ገልጸዋል፡፡ምዕመናኑ በየቤተክርስቲያኑና በሰፈር አካባቢ በመሰባሰብ ውይይጥ በሚያደርጉበት ጊዜ ከገዢው መንግስት የደህንነት አባላት ራሱን እንዲጠብቅና ልብ ለልብ ከሚተዋወቁት ሰዎች ጋር ብቻ በመነጋገር ለበለጠ ትግል ለመዘጋጀት ተስማመተዋል፡፡በእለቱ በሰላማዊ ሰልፉ ሕይወታቸው ላለፉት ወገኖች በቤተክርስቲያናት የፍትሃት ስርአት አለመደረጉ ያሳዘናቸው አማኞች በህዝቡ ላይ አፈሙዝ በማዞር የተኮሱትን የጸጥታ ሃይሎች ለፍርድ እንዲያቀርብ ሃቀኛ የሃይማኖቱ መሪዎች እንዲጠይቁ በተለያየ ሑኔታ ግፊት ለማድረግ ተስማምተዋል፡፡ባዶ እጁን በወጣ ህዝብ ላይ የተወሰደው እርምጃ አግባብ እንዳልሆነ የገለጹት ምእመናን ከህዝብ ጋር አብረው የሚኖሩ የከተማዋ የፖሊስ አበላት የህዝቡን ደም በከንቱ ፈሶ ሲቀር በዝምታ መመልከታቸው ትልቅ የታሪክ ጠባሳ ነው ሲሉም ተደምጠዋል፡፡
No comments:
Post a Comment