(አዲስ አድማስ ታህሳስ 11 2007 ዓ.ም):-ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ፣ ‹‹የቤተ ክርስቲያን አባቶችና ቤተ ክርስቲያን ዕውቅና በሰጠችው ማኅበር ላይ ተገቢ ያልኾነ ቃል ተናግረዋል›› ባላቸው አንዳንድ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አድባራት አስተዳዳሪዎች ላይ ያሳለፈው ውሳኔ አፈጻጸም ‹‹ሕገ መንግሥቱንና ሰብአዊ መብትን የሚፃረር ነው›› በሚል ፓትርያርኩ ማገዳቸው ተገለጸ፡፡ ፓትርያርኩ ባለፈው ኅዳር 30 ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት በጻፉት ደብዳቤ ‹‹አፈጻጸሙ እንዲቆይ›› በማለት ያገዱት የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ፣ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትና በጠቅላይ ቤተ ክህነት በተካሔዱ ጉባኤዎች÷ ‹‹ተገቢ ያልኾነ ቃል ተናግረዋል፤ ይህም አነጋገር ጉባኤውን ቅር አሰኝቷል፤›› ያላቸው የአድባራት አስተዳዳሪዎች፤ቀኖናዊ ምክርና ተግሣጽ እንዲሰጣቸው በአንድ ድምፅ ተስማምቶ ያሳለፈው እንደነበር ተጠቅሷል፡፡
በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት፣ በመንበረ ፓትርያርክና በጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌል አዳራሾች በተካሔዱት ስብሰባዎች የቤተ ክርስቲያኒቱን መልካም አስተዳደርና ወቅታዊ ችግሮች የተመለከቱ የጉባኤተኞች አስተያየቶችና ሐሳቦች መቅረባቸውን በደብዳቤያቸው ያስታወሱት ፓትርያርኩ፤ ተሰብሳቢዎቹ ሐሳባቸውንና አስተያየታቸውን በግልጽ መናገራቸውና አሉ የተባሉ ችግሮች መፍትሔ እንዲያገኙ መጠየቃቸው ‹‹በዓለም አቀፍ ደረጃም ኾነ በሀገራችን ለሕዝብ የተፈቀደ ዴሞክራሲያዊ መብት መኾኑ አያጠያይቅም›› ብለዋል፡፡ ሐሳባቸውንና አስተያየታቸውን በግልጽ ያቀረቡ ሰዎችን መገሠጽና መውቀስም ሕገ መንግሥቱን እንደሚፃረር ጠቁመዋል፡፡ጉባኤዎቹ በቤተ ክርስቲያን ጠሪነት የተካሔዱ እንደነበሩና ተሰብሳቢዎቹም የቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንት፣ አገልጋዮችና ሠራተኞች መኾናቸውን ፓትርያርኩ ጠቅሰው÷ የጎደለው እንዲሟላ የጠመመው እንዲቃና ያላቸውን አስተያየት በማቅረባቸው ተግሣጽና ማስጠንቀቂያ እንዲሰጣቸው ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳለፈው ውሳኔ ‹‹የስብሰባ ነፃነትንና መብትን ነፍጎ ሐቁ እንዳይነገር›› የሚከለክልና ውጤቱም ‹‹ጊዜ ያለፈበትን አፈና በማንገሥ ችግሮች ተባብሰው እንዲቀጥሉ የሚያደርግ ነው›› ብለዋል፡፡ “በውይይቱ ወቅት ‹‹የዳኅፀ ልሳን ወለምታ›› አጋጥሞም ከኾነ በወቅቱ ማብራሪያና ማስተካከያ ይሰጥበታል እንጂ እንደ ከባድ ጥፋት ተቆጥሮ ሰዎች ሊገሠጹበትና ሊወቀሱበት አይገባም፤ ሕግም አይፈቅድም፡፡” ሲሉ ገልጸዋል – በደብዳቤያቸው፡፡የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ‹‹ተገቢ ያልኾነ ቃል ተናግረዋል›› ያላቸው አንዳንድ የአድባራት አስተዳዳሪዎች በጠቅላይ ቤተ ክህነት በኩል ቀርበው ቀኖናዊ ምክርና ተግሣጽ እንዲሰጣቸው ያሳለፈው ውሳኔ ‹‹ሕግንና ሰብአዊ መብትን የሚፃረር›› ብቻ ሳይኾን ‹‹ትልቁን ጉባኤ በታሪክና በሕግ ዐዋቂዎች ዘንድ ግምት ውስጥ የሚጥለው እንዳይኾን አቡነ ማትያስ አስጠንቅቀው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶሱ ጉዳዩን እንደገና በጥልቀትና ከሕግ አንጻር ፈትሾ እንዲያጤነው በማለት አፈጻጸሙ እንዲቆይ አስታውቀዋል፡፡በሕገ ቤተክርስትያን ቅ/ሲኖዶሱ በሙሉ ድምፅ ተስማምቶ ያሳለፈውን ውሳኔ ፓትርያርኩ የማገድ ሥልጣን እንደሌላቸው ያመለክታል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ከተጠቀሰበት አግባብ አኳያም፣ “ቤተ ክርስቲያናችን በቂ ሕግጋት አሏት፤ እነዚህ ሕግጋት ማዕከሉ ተጠብቆ ሊሠራባቸው ይገባል፤” ሲልም ቅ/ሲኖዶሱ አሳስቧል፡፡ ባለፈው መስከረም መጨረሻ “የቤተ ክርስቲንን አስተዳደራዊ አስተሳሰብ ማበልጸግ” በሚል መርሕ በተካሔደው ስብሰባ አንዳንድ የአድባራት አስተዳዳሪዎች፤ ‹‹ፈጣሪ የለም ይላል፤ አሸባሪና አክራሪ ነው፤›› በማለት ቤተ ክርስቲያኗ ዕውቅና የሰጠችውን ማኅበረ ቅዱሳንን ከዓለም አቀፍ ጽንፈኞች ጋራ እያመሳሰሉ መወንጀላቸው ተገቢ እንዳልኾነና የማኅበሩ አገልግሎት ለቤተ ክርስቲያን አስፈላጊ እንደኾነ ቅዱስ ሲኖዶሱ አረጋግጧል፡፡‹‹ቆራጣ ደብዳቤ ይበቃዋል፤ ከመንግሥት ጋራ በመተባበር እስከ ጫፍ አድርሱልን፤ በቶሎ ቁረጡት›› እያሉ መጠየቅ፤ ሊቃነ ጳጳሳቱንም “ከፈለጉ ቆባቸውን አስቀምጠው ወደዚያው ይግቡ” እያሉ መዝለፋቸውስ በምን መመዘኛ ነው ዴሞክራሲያዊና ሕገ መንግሥታዊ የሚኾነው በማለት የሚገልጹ የስብሰባው ተሳታፊዎች በበኩላቸው፤ ፓትርያርኩ የውሳኔውን አፈጻጸም ማገዳቸው፣ አድሏዊ እንደሚያደርጋቸውና በካህናቱና በምእመናኑ ዘንድ መንፈሳዊ አባትነታቸውንና ታማኝነታቸውን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባው እንደሚኾን ጠቁመዋል፡፡
No comments:
Post a Comment