Monday, December 15, 2014

በከፍተኛ ህመምና እንግልት ላያ ያለው የጋዜጠኛ ተመስገን ዳሳለኝ የቃሊቲው ክራሞት

ተሜን ትላንት መጎብኘት ተከልክሎ ዛሬ ግን ተፈቀደ!

Tariku Desaleng

ትላንት እሁድ ታህሳስ 5/07 ዓ.ም ተሜን ለመጠየቅ ታላቅ ወንድማችን ባሳዝነው ደሳለኝና ሰውዓለም ታዬ ወደ ቃሊቲ አምርተው ነበር፡፡ እኔ ደግሞ ዛሬን እንኳን ልረፍ ብዬ የነርሱን መምጣት ለመጠበቅ ወስኛለሁ፡፡ መድረሳቸውን ለማረጋገጥ በማለዳ ስደውል ግን የሰማሁት የጠበኩትን አልነበረም፡፡ በተመስገን ጉዳይ ላይ ምንም ብሰማ ላለመራድ በመወሰኔ ተረጋግቼ ማውራቴን ቀጠልኩ፡፡ “ደርሰናል፤ ተመስገንን መጠይቅ ግን አትችሉም” ብለውናል ሲሉ ነገሩኝ፡፡ አልደነገጥኩም፤ ሰሞነኛው የእስር ቤቱ አስተዳደር ተከታታይ እርምጃ ይሄ እንደሚመጣ ይናገር ነበር፡፡


ነገሩ እንዲህ ነው፦ ከ12 ቀናት በፊት ከቃሊቲ ዞን 3፣ ወደ ቃሊቲ ዞን 3 6ኛ ቤት አሸጋገሩት፡፡ በአገባቡ መጠየቅ የማይሞከር ሆነ፡፡ ከጠያቂ ጋር ለመገናኘት በባለ ማዕረግ ወታደሮች መታጀብ ተመስገንን የገጠመው የ6ኛ ቤት የመጀመሪያ ፈተና ነበር፡፡ 5 ደቂቃ ደግሞ የትኛውም የዕርሱ ጠያቂ ለመጨዋወት የተሰጠው የጊዜ ገደብ ነው፡፡ ተሜ ፈገግ እንዳለ መጥቶ እንዴት ናችሁ ብሎ ጠይቆን ፈገግ እንዳለ ተመለሰ፡፡ የእኛን ምላሽ ስለመስማቱም እንደተጠራጠርኩ ከእስር ቤቱ ወጣሁ፡፡ ከ 10 ቀናት በፊት አሁንም ከአጃቢ ወታደሮች ጋር መጣ፡፡ ለመጠየቅ በተፈረደልን 5 ደቂቃ ውስጥ የቤተሰቡንና የከተማውን ወሬ ተንፍሰን ተለያየን፡፡ ተሜ አንድም ቃል ሳያወጣ አዳመጠን፡፡ ወዲያውም ስንብት ተከተለ፡፡

ከ 8 ቀናት በፊት የጠያቂና እስረኛ መገናኛ ቦታ ላይ ቆመን ተሜን ሳያመጡት ደቂቃዎች ነጎዱ፡፡ ከቆይታ በኋላ ወታደሮቹ ተመስገን እንደሌለና የት እንዳለ እንደማያውቁ ነገሩን፡፡ ቃሊቲ ውስጥ ሆኖ አናውቅም ማለት ምን ማለት ነው? በተለምዶ ወንድነት የሚባለውን ፈተናና እልህን በሚያስጨርስ መለማመጥ ተሜ የት እንዳለ ለመናገር ፈቀዱ፡፡ በልዩ ጥበቃ ስር መሆኑን ተረዳን፡፡

በልዩ ጥበቃ ስር ተሜ ለብቻው አንዲጠየቅ ተወስኖ ለብቻው አገኘነው፡፡ በፃፋቸው ፅሁፎች ብቻና ብቻ 3 ዓመት የተፈረደበትን ጋዜጠኛ ለብቻው በልዩ ጥበቃ ስር እንዲጠየቅ ማድረግ ምን ማለት ይሆን? ከ6 ቀናት በፊት ተሜን በልዩ ጠበቃ ስር መጠየቅ ግድ ሆኗል፡፡ ይህን መቻል ደግሞ የእኛም የእርሱም ብቸኛ አመራጭ ነው፡፡ ከዚህ የባሰው ደግሞ አረፋፍዶ መጣ፡፡ ከርቀት አሳይተውን ልባዊ ሠላምታ ብቻ ተለዋውጠን ተመለስን፡፡ ይሄንን አለመቻል ይቻላል? በርግጥ አይፈቀድ ይሆናል እንጂ ይቻላል፡፡

ከ 5 ቀናት በፊት በልዩ ጥበቃ ስር ከዋለችው ክፍል ተሜ በመገረም ውስጥ ሆኖ መጣ፡፡እንደተያየን ሁሌም የማትቀረውን ጥያቄ ሰነዘረ፡፡ ‹እማዬ እንዴት ነች?›፤ እንደሁሌውም ‹‹ደህና ናት›› ስል መለስኩለት፡፡ ተሜን እንዴት ነህ አይባልም፡፡ ፊቱ ላይ የሚታየው ብርሃናማ ብርታትና ፅናት አፍ አውጥቶ ይናገራል፡፡ ‹እኔ ያለሁበት ክፍል ያሉት እስረኞች አሳዝነውኛል፤ ተመስገንን ሠላም በላችኋል፤ ምንድነው ያላችሁ በማለት በካቴና ያስሯቸዋል፤ ይደበድቧቸዋል› ሲለኝ ወዲያው ድንጋጤ ወረረኝ፡፡ ዝም አልኩ፡፡ ብቸኛ እንዲሆን ፈልገዋል ማለት ነው፡፡ በክፍሉ ውስጥ ያሉት እስረኞች ተሜን በስህተት እንኳን ላለመናገርና ላለማየት እንዴት እነደሚሳቀቁ ታየኝ፡፡

የኢትዮጲያ ብሔራዊ ቡድን ከናይጄሪያ አቻው ጋር አዲስ አበባ ላይ ጨዋታውን ሲያካሄድ ቦንብ ሊያፈንዳ ሲል እንደተያዘ የተነገረለት ሱማሌያዊ እስረኛ አብሮት እንደታሰረ ነገረኝ፡፡ ‹‹እስረኞቹ አንድ ለአምስት ተደራጅተዋል፤ በየቀኑ ከእስር ቤቱ ሀላፊዎች ጋር ስብሰባ ያደርጋል፡፡ ሀላፊዎቹ ‹ተሰብሰብ› ብለውኝ ነበር፡፡ የመጣሁት እስረኛ ሆኜ እንጂ ለስብሰባ አይደለም› ስላቸው ዝተውብኝ ሄዱ››….. እየሳቀም ‹‹ከሰውኛል›› አለኝ፡፡ ፍርዱን ተቀብሎም ሌላ ክስ? ‹በሽብርተኝነት ከተከሰሰው ሱማሊያዊ እስረኛ ጋር በመሆን የቃሊቲን እስር ቤት ለማቀጠል አሲረሃል› ብለውኛል ሲለኝ ደንገጥኩ፡፡ እንደዚህ ሆኜ የማውቅበት ቀን ያለም አይመስለኝም፡፡ ተሰንባበትን ወጥቼም ቀልቤ እዛው ነበር፡፡ እነዚህ ሰዎች ከቂሊንጦ ዝዋይ፣ ከዝዋይ ቃሊቲ ዞን 3፣ ከቃሊቲ ዞን 3 ቃሊቲ ዞን 3 ስድስተኛ ቤት፣ ከቃሊቲ ዞን 3 ስድስተኛ ቤት ደግሞ ወደ ቃሊቲ ልዩ ጥበቃ ስር ያሸጋገሩት ይሄን አስበው ይሆን እንዴ?! ይህ ላይሆን የሚችልበት ምክኒያት ከልምድ ፈልጌ አጣሁ፡፡

ከ 2 ቀናት በፊት ተሜን ለማየት ስሄድ በልዩ ጥበቃ ስር በሁለት አጃቢ ወታደሮች መካከል ሆኖ ከእኔ ኋላ ደግሞ ሲቪል የለበሰ ሰው መገናኛ ራዴዮኑን እንደያዘ ቆሟል፡፡ ወደ ኋላ ተመልሼ በተከታታይ የሆኑትን ነገሮች ሳስታውሳቸው፡፡ አንድ ቀን ‹ተመስገንን መጠየቅም አይችልም ሊሉ እንደሚችሉ ቅደመ ግምት ወስጄ ነበር፡፡ ቃሊቲን ሊያፈነዳ አሲሯል የሚለውን ክስን ግን አልገመትኩም ነበር ምክኒያቱም የተመስገንን ስብና አይደለም እኔ አሳሪዎቹ በድንብ ያውቁታልና ተብሏል› ፡፡

ዛሬ ታህሳስ 6/07 ትላንት አታዩትም ያሉትን ተመስገን እንዳይታይ የከለከሉበት ምክኒያት ካለቸው ብለን ለማወቅ ቃሊቲ በጠዋት ነበር የደረስነው፡፡ ላናታችን እንደማይጠየቅ ስላልነገርናት የቋጠረችውን ስንቅ ይዘናል፡፡ አድራሻችንን ስናስመዘግብ ካሁን አሁን ተመስገንን መጠየቅ አይቻልም የሚል ድምፅ ብንጠብቅም አልሰማንም፡፡ ገቡ አሉን አለምንም ሀሳባቸውን ሳይቀይሩ በፍጥነት ገባን፡፡ በልዩ ጥበቃ ስር 1 ሰዓት ከለፍን በኋላ ተሜ መጣ፡፡ ትላንት አንተን መጠየቅ እንደከለከሉና ዛሬ እንደፈቀዱ ነገርነው “ምን ምክኒያት ነገሮቹ” ምንም ሁሉም ነገር ካለምክኒያት እንደሚደረገ የሚያውቀው ተሜ ሳቀ፡፡ “አሞኛል” ሰምቼዋለሁ ስላላመንኩኝ ግን ምን አልከኝ አልኩት ደገመለኝ ደነገጥኩኝ፡፡ ተሜ ሁሉንም ነገሮችን በሆዱ የሚያዝ ነው ግዴታ ካልሆነበት አይናገረም ዛሬ ወንድሜ አሞኛል አለኝ፡፡ ምን ያህል እንደታመመ አሰብኩት፡፡ “እዚህ ክፍል ከገባው ጀምሮ በሩ ስር ነው የምተኛው በሩ ከታች ክፍት ነው ወደ አልጋ እንቀይርሀልን ቢሉኝም ቅያሪውን ያደረጉት ከኔ ኋላ ወደ ክፍሉ ለመጡት እስረኞች ነው አሁን ጀርባዬ አብጧል ወገቤን በኋይል ያመኛል” አለኝ፡፡ ተሜ የወገብ ህመም አልፎ አልፎ የመዋል በብዙ ህክምና ተሸሎትም ነበር፡፡ አሁን ግን ሆን ተብሎ ንፋስ ባለበት ቦታ መሬት ላይ እንዲተኛ በመደረጉ ለደጋሚ ህመም ታዳርጓል፡፡ “ህክምና ጠይቄ ከልክለውኛል” በህመም ውስጥ ለውን ወንድሜን መርዳት እንደመላችል ሲገባኝ አንገቴን ደፋሁኝ፡፡

እናታችን ከሰኞ በኋላ ተመስገንን ለማየት እንደምትሄድ ነበር የምታውቀው፡፡ “እንግዲህ እናቴ ከነ ሙሉ ጤንነቱ ያየሽው ልጅሽ አሁን ህክምና አጥቶ በከፈተኛ ህመም ውስጥ ይገኛል፤” ብሎ ለመናገር ድፍረቱም የለኝ፡፡ እንዴት እንደዚህ ልላት ይቻለኛል? አሳሪዎቹ ልክ እንደልጅት ጨዋታ ዕቃዎቻችን ይዘን እንቁልልጭ አንደምንለው ተሜንም ቃሊቲ አምጥተውት ህመም ቢያሰቀየውም አናሰክመውም፤ ማየት ብትፈልጉም እኛ ስንፈልግ ብቻ ነው እምናሳያቹ፤ በማለት እንቁልልጭ እያሉን ነው፡፡ አውቃለሁ ተሜ በህምም ውስጥም፤ በብቸኝነት ውስጥ፤ በስቃይ ውስጥም፤ ብትሆ ለሀገርህ እየከፈልከው ባለው ነገር የበለጠ እየበረታህና እየጠነከርክ እንድምትሄድ ለዚህ ስል እፅናናለሁ፡፡ እናቴ ግን አይዞሽ! የሚያደርገውን ያወቀው ልጅሽ የሀገር ኩራት ከሆነ ሰንብቷልና፡፡

No comments:

Post a Comment