Sunday, December 14, 2014

ወዛደር እና ወታደር ይለይለት! – ከዳንኤል ፈይሳ

(ጨዋታው ተጀምረ፡፡ ይህ ጨዋታ ለሕዳሴው ግድብ ድጋፍ ሲባል የሚደረግ መሆኑን ያለማሳወቅ አያስፈልግም፡፡ ያለእንደዚህ ያሉ የድጋፍ ሰጪ ጨዋታዎች የህዳሴው ግድብ ፕሮጄክት አይጠናቀቅም ሲሉ ቃል አቃባዩ እንጂነር ስመኘው ገልፀዋል፡፡)

በሃገራችን ኢትዮጵያ እንደ ውሃ ወለድ በሽታዎቻችን ብዛት ሁሉ ሁኔታ-ወለድ የሆኑ ብዙ ክስተቶች ያጋጥማሉ፡፡ከነዚህ መሃል በተለይ በፖለቲካው መስክ ሰዎች የሚያገኙት ስፍራ ከማንነታቸው ጋር የማይገጥም እየሆነ ተቸግረናል፡፡ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ለያዥ ለገናዥ ያስቸገረው የወታደሮቻችን ሁኔታ ነው፡፡ ጉዳዩ እንኳን ለእኛ ለሲቪሎቹ ለራሳቸውም ለወታደሮቹ እንደቸገራቸው ያስታውቃል፡፡እና ካወቅክ ምን ትቀባጥራለህ?! እና ካልቾ!.. ከቀረበልኝ ግን ‹‹እኔን ስትጠልዝ ጎሉ ወዳንተ ነው የሚገባው!›› ከማለትውጪ ምን እላለሁ? – ምንም፡፡(0 ለ 1)እንዴት ቢሉ ዳኛው ፍትሃዊ ነዋ! (0 ለ 1) አላልኳችሁም ?..ጨዋታው ቀጥሏል፡፡



የወታደር ስራ ምን ነበር ? አሁን አሁን የወታደር ልጆች አባቶቻቸውን “መቼ ነው ጦር ሜዳ የምትሄደው አባዬ ” ብለው ሳይጠይቁ እንደማይቀር መገመት አያዳግትም፡፡ አሊያም “የሰው ሃገር ነው እንዴ የምትጠብቀው – እኛ በኪራይ ቤት እየተሰቃየን-ይደብራል፡፡” ሳይሉም አይቀሩ እነሱ ምን አለባቸው…መጠየቅ ነው፡፡ ታዲያ ለልጆችችን መልስ ከሌለን ለማን ሊኖረን ነው?! (1 ለ 1)፡፡
ወታደሮቻችን ውሎአቸው ፋብሪካዎች ውስጥ መሆኑን አንጠላም፡፡ ግና የህዝብ አደራ አለባቸውና የህዝቡን ሮሮ ሰምተው ምላሽ መስጠትም ይጠበቅባቸዋል፡፡

ወታደር ፋብሪካ ሲውል ወታደርነቱ ቀርቶ ወዛደር ይሆናል፡፡ ወዛደር ገንዘብ ለማግኘት ሲል ምርቱን ከብረትነት ወደ ብርጭቆነት እያራቀቀና እያሳነሰ ገቢውን ያሳድጋል፡፡ ልዩነቱ የባህሪ ይሆናል፡፡ ከህዝባዊ ታማኝነት ወደ ትርፋማ ሰራተኛነት የባህሪ ለውጥ ያመጣል፡፡ይሻላል ታዲያ…?! (1 ለ 2 እረፍት ወጡ) ጨዋታው ባብዛኛው በወታደሮች ሜዳ ላይ ተከናውኗል፡፡ ምናልባት በምቹ ኑሮ ላይ ያሉቱ፣ ጥሩ አሳላጭ ሆነው ፋብሪካዎቹን ሲዘውሩት እያየን ነውi….ውትድርናን እንደህይወት ጥሪያቸው የተቀበሉና የሃገራቸውን ሐላፊነት በተሰጣቸው ወታደራዊ ግዳጅ ብቻ መወጣት አለብን ብለው ያመኑቱ ግን ውስጣቸው እየተብሰለሰለ “ሀገሬ ምን ያህል ጠላት እያፈራች ነው?…በየትኛው ግንባር አደጋ ይጣልባት ይሆን?…ለዘለቄታው ጠንካራ ህዝባዊ መሰረት ያለው ሰራዊት ለመገንባት የምንችለው በምን ስልት ነው?…ወዛደርነታችን ለዚህ ሰራዊት ዕውን መሆን ማረጋገጫ ይሰጠን ይሆን?” …በሚሉ የሃሳብ ውርጅብኞች ተውጠው ይውላሉ፡፡

ወታደር በክፉ ቀን ደጀን ፣ በደግ ቀን መከታ፤ መሆኑ ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም የሙያውን ሥነምግባርና የወታደሩን ክብር በጠበቀ መሆንም ይገባዋል፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ ወታደሩ ፋቲኩን የጣለበትን እስኪረሳና ቱታውን አሸርጦ ደፋ ቀና ሲል ማየት ደስ አይልም፡፡
ሰው ከተሰማራ እንደየስሜቱ
በዋለበት ሥፍራ አይቀርም ማፍራቱ
የህክምና ሊቅ በሽታን መርማሪ
ሲሆን ደስ አይልም ፊደል አስቆጣሪ፡፡ (1 ለ 3)
… ስትል የጥንቷ ድምፃዊት መንበረ እንዳዜመችው ያለ ዘመን ላይ ነን ማለት ነው፡፡ያ ደግሞ በዛሬዋ ኢትዮጵያ አይገርምም፡፡ምክንያቱም አንድ ከዩኒቨርሲቲ የተመረቀ ተማሪ ተስፋው በኮብሎ ስቶን ግንበኝነት ህይወቱን ለመግፋት የኢሃዴግ አባልነት ካርዱን መጨበጥ መሆኑን በልማታዊ እድገትነቱ የሚመካበት መንግስት ያለበት ዘመን ላይ ነንና፡፡ ይህስ ይሁን ‹‹ጀነራል ያንን ብሎን አቀብለኝ፡፡ጎንበስ አትልም እንዴ?… ዳይ ፍጠን! ሲባል ካልቀፈፈው ይመቸው፡ ፡አትታዘቡኝና ጦርሜዳ ሄዶ ከሚሞት ሳይሻለው አይቀርም፡፡ይህ ብቻም አይደለ በተለይ በልዩ ግዳጅ መሳሪያ ያልታጠቁ
የከተማ ውስጥ ሽብርተኞችን እንዲይዙና በቁጥጥር ስር እንዲያውሉ በሚሰጣቸው ግዳጅ ሚፈፅሙት ጀብድ ቀላል አይደለም፡፡ ምክንያቱም በግዳጅ ውስጥ ሲሆኑ በካልቾ በጥፊ በሰደፍ በመማታት ካልቻሉ ለግምገማ የሚያቀርቧቸው አስገዳጆች አብረዋቸው ፋቲክ ለብሰው እንደሚሰለፉ ይናገራሉ፡፡ እኛ ግን ፌደራሎች መሃል አግአዚዎች ያሉ አይመስለንምና ብዙ ጊዜ ወዛደሮቹን ከወታደሮቹ መለየት አቅቶን እንቀባጥራለን፡፡የምር ተገቢ አይደለም፡፡ እንደውም ፌደራሉ ቆርጦ መነሳት ባቃተው ህዝብ በእጅጉ ይበሳጫል ይባላል፡፡ቢቸግረው ነው ወደ ህዝቡ ለመቀላቀል እንዲመቸውና ከሲቪሉ ህዝብ ጋር በመመሳጠር ብሎኑን እያጠበቀ የላላውን ለመወጠር የሚሞክረው፡፡አሁንስ ገባችሁ ? (1 ለ 4) (1 ለ 4 ይህ አራተኛ ጎል የተቆጠረው በፌደራሉ ነበር ግን ዳኛው በእፍርት ለካድሬው መዘገበው እንጂ፡፡ምክንያት ሲባል ፌደራሉ ጎሉን በራሱ ላይ ነዋ ያገባው ብለው ፍርዱን ገምድለዋል-ዳኛው፡፡)

እሺ ለምን የውስጥ ነፃነታችሁን አታውጁም፡፡ ፊት ለ ፊት ሽጉጣችሁን አስቀምጣችሁ ለምን በወኔ አትነጋገሩም፡፡እናንተ ፊት ለፊት ባለመነጋገራችሁ የተነሳ ሕዝቡ እርስበርስ እንዲናቆር እያደረጋችሁ መሆኑን ለምን ትዘነጋላችሁ፡፡ ለዚህ እኮ ነው ለደሞዙ ብቻ ሲል የታዘዘውን የሚሰራ ወዛደር ሆናችኋል የምላችሁ፡፡ ለምሳሌ ጡረታ አወጣጣችሁ ራሱ ትክክል አይደለም፡፡ ሰው መስራት እየቻለ ለምን ጡረታ ይወጣል፡፡እድሜያችንን የሚያውቀውኮ ፈጣሪ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ አበባው ሳይረግፍ ፍሬ አያፈራም የሚል አጉል ፍልስፍናችሁን አቁሙ፡፡ በአበባው ወቅት ነው መነጋገር፡፡በወጣትነትህ ለፍቅር ተሰዋ ይላልና፡፡ አበባ የወጣትነት ምልክት ነው፡፡ነፃነት ሌላቸው ነፃ አውጪዎች ሆናችሁ እኮ፡፡ እናንተ ሰራታችሁ ቀርቶ ድፍን የኢትዮጵያ ገበሬ አርሶ በምግብ እህል ራሳችንን ነፃ አላወጣንም፡፡ አቦ አውልቁ ሁለቱንም ልብስ ዳይ ውጡ …እንዳትባሉ!

የቀድሞ ሰራዊትን ያየ በድል አይቀልድም፡፡ አያፈገፍግም፡፡ ከህዝብ ጋር ያልወገነ ውትድርናና ውዝድርና አያዋጣም፡፡ለመሆኑ ከህዝቡ ጋር የሥጋ ዝምድና የሃይማኖት ወይ የእድርና ማህበር ጉርብትና የላችሁም እንዴ? … ይህስ ኖረ አልኖረ ሰብዓዊነትን ያህል ፀጋ ከውስጣችሁ ጠፍቷልን ከጠፋ አልፈርድባችሁም፡፡ ግን ያንን ወደ ግዑዝነት የለወጣችሁን ጨካኝ አገዛዝ በዝምታ እስከመች ታገለግላላችሁ!? (ባለቀ ሰዓት አምስተኛው ጎል ገባ፡፡ጨዋታው 1 ለ 5 ተጠናቀቀ፡፡) ፌየር ፕሌይ !አንድ ለ አምስት የሚለው ስልት ከዚያች ቀን ጀምሮ ውጤታማ መሆኑ ተረጋገጠ፡፡
ምን ያደርጋል ወዛደር አምስት ቢያገባም ጨዋታው በድጋሚ እንዲደረግ ሳቦታጅ ተሰራ፡፡ የፌየር ፕሌይ አዘር ሳይደ ነዋ፡፡ያልመረረው ወታደር ያው በድጋሚ ሊጋጠም አብሮ እየሰራ ይገኛል፡፡ቀጣዩ ተጋጣሚ ፖሊስ ሲሆን ጨዋታው ቂሌ እንዲሆንለት ጠይቋል፡፡ ገና ፡፡

ለማንኛውም ወዛደርና ወታደርን ለይተን የምናይበት የኢትዮጵያውያን የክብር ዘመን ያምጣልን!
ነፍሴ አሜን በል ከአሚን ይቀራል ይላሉ እኛ ሰፈር ያሉ ባለሱቅ፡፡
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኖራለች!


No comments:

Post a Comment