Wednesday, December 17, 2014

‹‹በሰላማዊ ሰልፈኛ ላይ ዱላ መሰንዘር ሽንፈት ነው›› እስክንድር ነጋ

ሰማያዊ ፓርቲ እና ሌሎች በትብብሩ ውስጥ የታቀፉ ፓርቲዎች በጠሩት የአዳር ሰልፍ ላይ የወጡ ሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ የተወሰደውን አሳፋሪ እርምጃ ሰምቻለሁ፡፡ እርምጃው ሁለት ነገሮችን በጉልህ ያሳዬ ነበር፡፡ አንደኛ የኢህአዴግ መራሹ መንግስት ሽንፍትን ያሳየ ነው፤ ሁለተኛው ደግሞ ሰላማዊ ትግሉ እየተጠናከረ መምጣቱን ያመላከተ ነው፡፡
አንተ ባዶ እጅህን መብትህን ለመጠየቅ ስትንቀሳቀስ፣ መሳሪያ ወደታጠቀ አካል በሰላም ስትገሰግስ ባለመሳሪያው ዱላውን ከሰነዘረብህ አሸናፊው አንተ ሰላማዊው ታጋይ ነህ፡፡ በትብብሩ ሰልፍ ላይ የሆነው ይኸው ነው፡፡ አሁን ሰላማዊ ትግሉ ፍጹም ሰላማዊነቱን እንደጠበቀ መጠናከር ነው ያለበት፡…፡ ሰላማዊ ትግል ላይ ልብ ማለት ያለብን ነገር አለ፤ እሱም ሰላማዊ ሆኖ መዝለቅ የሚለው ጉዳይ ነው፡፡

ሰላማዊ ታጋይ ይሰደባል፣ ይደበደባል፣ ይሞታልም፡፡ ግን ደግሞ ሰላማዊ ታጋይ አይሳደብም፣ አይደባደብም፣ አይገድልም፡፡ ይህ ከሆነ ሰላማዊ ትግል ያሸንፋል፡፡ አምባገነኖች ሰላማዊ ታጋዮችን በተለያየ መንገድ ከሰላማዊነታቸው እንዲወጡ ሊገፋፏቸው ይሞክራሉ፤ ስሜት ውስጥ በመክተትም የኃይል በትራቸውን ለማሳረፍ ይቋምጣሉ፡፡ ይህ ሴራ ሰላማዊ ታጋዮችን ሊያዘናጋቸው አይገባም፡፡
በቀደም በተደረገው ሰልፍ ላይ ድብደባው በሰላማዊ ሰዎች ላይ መፈጸሙ ለተደብዳቢዎቹ ሳይሆን ሽንፈቱ ለደብዳቢዎቹ ነው፡፡ በደረሰው ድብደባ ባፍርም፣ ባዝንም በውጤቱ ግን ደስተኛ ነኝ፤ ምክንያቱም ሰላማዊ ሰልፈኞች ሰላማዊነታቸውን አሳይተዋልና! በሰልፉ ወቅት ድብዳባ እና እስር የደረሰባቸውን የመብት ጠያቂዎች ሁሉ በርቱ ልላቸው እፈልጋለሁ፡፡ ባደረጉት ሰላማዊ እንቅስቃሴ በጣም ኮርቻለሁ፡፡ ሰላማዊና ህጋዊ ትግላችሁን ቀጥሉ ማለትም እፈልጋለሁ!
‹‹አሸናፊው ህዝብ ነው›› አንዱዓለም አራጌ
ግለሰቦች የለውጥ ሐዋርያ ሊሆኑ ይችላሉ፤ በዚያው ልክ የሚሳሳቱትም ግለሰቦች ናቸው፡፡ የግለሰቦች አስተሳሰብ ህዝባዊ ከሆነ ግን በአሸናፊው ህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ይኖራቸዋል፡፡ ምክንያቱም አሸናፊው ህዝብ ነው፤ አሸናፊው ሀገር ነው፡፡ የሁላችንም አሸናፊነት የሚገለጸው ሀገር ከፍ ከፍ ስትል ነው፡፡ ስለዚህ ስራችን ሁሉ ሀገርን ከፍ ለማድረግ መሆን አለበት፡፡
በትብብሩ ፓርቲዎች በተጠራው ሰልፍ ላይ የሆነውን ሰምቻለሁ፡፡ በሆነው ነገር አዝኛለሁም፤ ኮርቻለሁም፡፡ ያዘንኩት በደረሰው ድብደባ እና እስር ነው፡፡ የኮራሁት ደግሞ መብታቸውን በሰላማዊ መንገድ ሊጠይቁ በድፍረት አደባባይ በወጡት ታጋዮች ነው፡፡ በእነዚህ ታጋዮች የእውነት ኮርቻለሁ፡፡
በቀጣይ ፓርቲዎች በአጋርነት መስራት አለባቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ በተለይ በቀጣዩ ምርጫ ለመሳተፍ የሚፈልጉ ፓርቲዎች ከእጩ አቀራረብ ጀምሮ ተቀራርበው መስራት ይኖርባቸዋል፡፡ በተለይ ሰማያዊ እና አንድነት ተቀራርበው ቢሰሩ የበለጠ ውጤታማ የሚሆኑ ይመስለኛል፡፡ በተረፈ ግን በትብብሩ ሰልፍ ወቅት ጉዳት ለደረሰባቸው ሁሉ ጥንካሬን እንዲሰጣቸው እመኛለሁ፡፡ ትግላቸውንም አጠናክረው እንዲቀጥሉ አደራ እላለሁ፡፡
‹‹ቃላችሁን ጠብቃችኋልና ክብር ይገባችኋል፣ ኮርቸባችኋለሁም!›› የሺዋስ አሰፋ
ሰማያዊ ፓርቲ መርህ አለው፡፡ ያመነበትን ነገር ህጋዊና ሰላማዊነቱን ጠብቆ እንደሚፈጽም አውቃለሁ፡፡ ትብብሩ በጠራው ሰልፍ ላይም የሰማያዊ ወጣቶችና ሌሎችም ቃላቸውን ጠብቀው ሰልፍ ወጥተዋል፡፡ በእውነት በጣም ኮርቸባቸዋለሁ፡፡ እንደሁሌውም ቃላቸውን ጠብቀው ለህዝቡ መብት መቆማቸውን አይቼ ደስ ብሎኛል፡፡ እኔ በእስር ላይ ብሆንም ሌሎች የትግል ጓዶቼ ባደረጉት ነገር በጣም ነው ደስ የተሰኘሁት፡፡
ድብደባውና እስሩ የፈሪ ዱላ ነው፡፡ ኢህአዴግ በህዝብ ፊት ኪሳራን ነው ያተረፈው፡፡ ሰላምን እና ህግን ማስጠበቅ የሚቻለው በልምምጥ ሳይሆን ትክክለኛ መስመርን በመከተል ነው፡፡ በዚህ መሰረት የትግል ጓዶቼ ትክክለኛ መስመር ላይ እንደሆኑ ይገባኛል፡፡ በርቱልኝ ማለት እፈልጋለሁ፡፡ በዚህ መሰል ሰላማዊነት ነው አምባገነኖችን ማሸነፍ የሚቻለው፡፡


No comments:

Post a Comment