Friday, December 26, 2014

ከድንበር ጋር በተያያዘ በአማራና በትግራይ ክልል ከፍተኛ ውጥረት ነግሶአል

ታኀሳስ ፲፯(አስራ ሰባት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የአካባቢው ነዋሪዎች እንደገለጹት ታህሳስ 16 ቀን 2007 ዓም በሶረቃ ከተማ ከ70 ያላነሱ ከትግራይ ክልል የመጡ ታጣቂዎች፣ ከምስላል ወደ ስላንዴ በረሃ የሚሰራውን መንገድ ለማስቆም ተኩስ በመክፈታቸው 2 አርሶ አደሮች ሲቆስሉ፣ በአብራጅራ ወረዳ የሚገኙ ጸረ ሽምቅ እየተባሉ የሚጠሩ ሃይሎች ከህዝቡ ጋር በመሆን የአጸፋ ተኩስ በመክፈታቸው ታጣቂዎች ከአካባቢው ተሰውረዋል።
ፌደራል ፖሊስ ወደ አካባቢው በመሄድ ህዝቡን ለማነጋገር ሙከራ በማድረግ ላይ ሲሆን፣ በአማራ ክልል በኩል ያሉ የአራት ወረዳ ህዝብ እስከ ታህሳስ 30 ድንበራችን ካልተከለለ እና የታሰሩ ሰዎች ካልተፈቱ እርምጃ እንወስዳለን በማለት ማስጠንቀቃቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል .
ሌሎች ወገኖች እንደሚሉት ደግሞ የትግራይ ክልል እያስታጠቀ የሚልካቸው ታጣቂዎች በአማራ ክልል ያሉ ብአዴኖችን እያስቆጣ ነው። ግጭቱንም የሁለቱ የፖለቲካ ድርጅቶች ግጭት አድርገው የሚወስዱት ወገኖች አሉ። ሁለቱም ክልሎች የድንበር ችግሩን እስካሁን ለመፍታት አለመቻላቸው በአካባቢው ለሚነሳው ተደጋጋሚ ግጭትና ለሚጠፋው የሰው ህይወት ምክንያት መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች ይገልጻሉ። ህወሃት ስልጣን በያዘባቸው የመጀመሪያዎቹ አመታት ከአማራ ክልል መሬት በመውሰድና ወደ ትግራይ በማካለል የቀድሞ የህወሃት ታጋዮችን አስፍሮበታል በሚል በተደጋጋሚ እንደሚተች ይታወቃል።


No comments:

Post a Comment