Friday, September 14, 2018

የቴዲ አፍሮ የሙዚቃ ኮንሰርት ተራዘመ

(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 4/2011) በአዲስ አበባ በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ለነገ የታቀደው የድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን የሙዚቃ ኮንሰርት መራዘሙ ታወቀ።

መስከረም አምስት ቅዳሜ በሚሊኒየም አዳራሽ የተዘጋጀው የሙዚቃ ኮንሰርት ከ20ሺ በላይ ትኬቶች ተሽጠው ያለቁ መሆናቸውን የገለጹት የኢሳት ምንጮች በአንድ ሳምንት እንዲራዘም መደረጉን ገልጸዋል።

ከአዲስ አበባ አስተዳደር በኩል ኮንሰርቱ እንዲራዘም መጠየቁም ታውቋል።

ከአንድ ዓመት በፊት ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኘው ኢትዮጵያ የተሰኘው አልበም ከወጣ በኋላ የድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን የሙዚቃ ኮንሰርት በሀገር ውስጥ እንዲያቀርብ ታቅዶ እንደነበረ ቢገለጽም በተለያዩ ምክንያቶች ሲስተጓጎል ቆይቷል።

በባህር ማዶ በአሜሪካና አውሮፓ ኢትዮጵያ ወደ ፍቅር ጉዞ የተሰኘውን የሙዚቃ ኮንሰርት በማቅረብ የቆየው ድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን በሀገር ቤት ባህርዳር ላይ ተመሳሳይ ዝግጅቱን ማሳየቱ የሚታወስ ነው።

በአዲስ አበባ የሙዚቃ ኮንሰርት ለማዘጋጀት ለአዲስ አበባ አስተዳደር ጥያቄ ያቀረበው ቴዲ አፍሮ ለእንቁጣጣሽ ዋዜማ አቅዶ የሚሌኒየም አዳራሹ በሌላ ፕሮግራም በመያዙ ለአንድ ሳምንት እንዲያራዘምና እንዲያካሂድ ተፈቅዶለት ነበር።

ይህም ሲደረግ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት በተላከ ደብዳቤ መሆኑንና ያም ደብዳቤ ብዙ እንግዶችን በአንድ ላይ የምንጋብዝበት መድረክ ስላስፈለገን ነውና ተባበሩን የሚል ይዘት ያለው ነው ብሎናል በውጭ ሃገር የቴዲ አፍሮ የሙዚቃ ኮንሰርት አስተባባሪው ጴጥሮስ አሸናፊ።

ነገ በሚሌኒየም አዳራሽ ለታቀደው የቴዲ አፍሮ የሙዚቃ ኮንሰርት ከ20 ሺህ በላይ ቲኬቴች ተሽጠው ማለቃቸውን አስተባባሪው ተናግሯል።

በዓይነቱ የተለየ እንደሚሆን የተነገረለትን ይህን ኮንሰርት ለመታደም፣ በሙዚቃ አፍቃሪው ዘንድ ከፍተኛ ጉጉት እንደነበረ የሚገልጹት አዘጋጁ አዳራሹ መያዝ ከሚችለው በላይ ቲኬቶች መሸጣቸውንም ጠቅሰዋል።

ሆኖም አዲስ አበባ ላይ በተፈጠረው ችግር ምክንያት ለነገ የታቀደው ኮንሰርት በአንድ ሳምንት መራዘሙንና ይህንንም የአዲስ አበባ መስተዳድር ከቴዲ አፍሮ ጋር በመነጋገርና ፍቃዱን በመጠየቅ የተደረገ መሆኑም አስተባባሪው ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ከተፈጠረው ግጭት ጋር ተያይዞ ነገ ተጨማሪ አደጋ እንዳይከሰት ለጥንቃቄ በሚል የመራዘም ጥያቄው ከከተማው አስተዳደር መቅረቡን የገለጹት አስተባባሪው ቴዎድሮስ ካሳሁንም ጥያቄውን ተቀብሎ በሚቀጥለው ሳምንት ቅዳሜ እንዲካሄድ ተስማምቷል።

No comments:

Post a Comment