Thursday, September 6, 2018

የዲያስፖራ ኤጀንሲ ሊቋቋም ነው

(ኢሳት ዲሲ–ጳጉሜ 1/2010) በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ የዲያስፖራ ኤጀንሲ ሊቋቋም መሆኑ ተገለጸ።

 በዳይሬክተር የሚመራውና ምክትል ዳይሬክተር የሚኖረው የዲያስፖራ ኤጀንሲ በራሱ በጀት ኖሮት፣ለፓርላማው በራሱ ሪፖርት የሚያቀርብ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዛሬ ለጋዜጠኞች ገልጸዋል።


 በውጭ ሃገር የሚኖረውን ኢትዮጵያዊ መብት ለማስጠበቅ እንደሚቋቋም የተገለጸው የዲያስፖራ ኤጀንሲ፣በሚኒስትሮች ምክር ቤት ከጸደቀ በኋላ አንዳንድ የሕግ ጉዳዮች ሲያልቁ ስራ እንደሚጀርም ተመልክቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ በሐምሌ ወር 2010 ወደ አሜሪካ በተጓዙበት ወቅት በሶስት ዋና ዋና የአሜሪካ ከተሞች በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር መወያየታቸው ይታወሳል።

በዋሽንግተን ዲሲ፣በሎስ አንጀለስና በሚኒሶታ ሚኒያፖሊስ ከተማ ከፍተኛ ሕዝባዊ ድጋፍ የተጎናጸፉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ዲያስፖራው ሃገር ቤት ያሉ የተቸገሩ ወገኖቹን እንዲረዳ ጥሪ ማድረጋቸው ይታወሳል።

በዚህም ጥሪ መሰረት ኢትዮጵያውያን የሚለግሱትን ድጋፍ የሚያስተባብር ኮሚቴ መዋቀሩ ይታወሳል።

No comments:

Post a Comment