(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 8/201) የወንድምን ደም ማፍሰስ፣ ህጻናትን ማሰቃየት ትችላላችሁ ኢትዮጵያን መበተን ግን መቼም አይሳካችሁም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቡራዩ ሰሞኑን የተፈጸመውን ግድያ ተከትሎ የተፈናቀሉ ዜጎችን ከጎበኙ በኋላ እንደተናገሩት የወንድሞቻችሁን ደም በመጠጣት የምትረኩ ሃይሎች ኢትዮጵያን ማፍረስ ግን ህልም ነው ሲሉ ጠንከር ያለ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ተፎካካሪና አክቲቪስት ነን ባዮች በማስተዋል እንድትንቀሳቀሱ እጠይቃለሁ ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
መንግስት ለተጎጂዎች ድጋፍ እንደሚያደርግ በመግለጽ ከጎናችሁ ነን በማለት የተፈናቀሉ ዜጎችን አጽናንተዋል።
በፖሊስ ሪፖርት መሰረት በቡራዩ ጥቃት ከ25 ሰዎች በላይ ተገድለዋል። ህጻናት፣ ነፍሰ ጡር፣ አቅመ ደካማ የሆኑ አዛውንቶች የጥቃቱ ሰለባ ሆነዋል።
በሺዎች የሚቆጠሩት ከቀዬአቸው ተፈናቅለው አዲስ አበባ በትምህርት ቤት ውስጥ ተጠልለዋል። በዛሬው ዕለት እነዚህ ተፈናቃይ ዜጎችን የጎበኙት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ድርጊቱን አሳፋሪና የኢትዮጵያውያን የውርደት ታሪክ ሲሉ ገልጸውታል።
እንደሀገር ተዋደንና ተፋቅረን መኖር ካልቻልን እንደዚህ ዓይነት አሳፋሪ ክስተቶች ወደፊትም መቀጠላቸው አይቀርም ብለዋል።
ከአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ አቶ ታከለ ኡማ ጋር በመሆን ተፈናቃዮቹን የጎበኙት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በእናንተ ቦታ ሆኜ ማየት ይከብደኛል በምንችለው ሁሉ ከጎናችሁ ቆመን የመጣውን አደጋ እንቀለብሰዋለን ሲሉ ቃል ገብተዋል።
እናንተንም ወደ ነበራችሁበት እንመልሳችኋላን፣ ድርጊቱን የፈጸሙትን ለፍርድ ለማቅረብ የሚቻለውን ሁሉ እናደርጋለን ብለዋል ዶክተር አብይ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቡራዩ ተፈናቃዮችን በጎበኙ ጊዜ ያስተላለፉት መልዕክት የሰሞኑን ጥቃት ባደረሱና በስም ባልተገለጹ ሃይሎች ላይ ያነጣጠረ ነው።
የወንድሞቻችሁን ደም በማፍሰስ ህጻናትን በማስጨነቅ ተሳክቶላችኋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ኢትዮጵያን መበተን ግን መቼም አይሳካላችሁም ብለዋል።
የወንድማችሁን ደም መጠጣት የሚያረካችሁ ከሆነም ጠጡት፣ ኢትዮጵያን ማፍረስ ግን ህልም ነው ሲሉ ጠንከር ያለ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ይህን የምታደርጉ ሃይሎች የጊዜ ጉዳይ እንጂ መሸነፍ ብቻ ሳይሆን ሀሳባችሁም እንደሚቀበር አልጠራጠርም በማለት ድርጊቱን ለፈጸሙት አካላት መልዕክት ሰደዋል።
ይህ ድርጊት አሸናፊ የሌለው የቁልቁለት ጉዙ መሆኑን ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በዚሁ ከቀጠለ ሁሉም በተራ ይደርሰዋል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ይህን ድርጊት የሚፈጽሙ ወገኖች ዓላማቸው የተጀመረውን የለውጥ ሂደት ማክሸፍ ነው ይህ ከተሳካላቸው ኢትዮጵያ ከሸፈች ማለት ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
መንግስትን ወደነበርንበት የመኮርኮምና የማፈን እርምጃ ለማስገባት የሚደረገውን ግፊት አንፈልገውም ያሉት ጠላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የጀመርነው የዲሞክራሲ መንገድ ማላገጫና መቀለጃ እንዳይሆን ሁላችንም በጋራ ልንቆም ይገባል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ለመገናኛ ብዙሃንና አክቲቪስቶችም መልዕክት አስተላልፈዋል። በስም ያልጠቀሷቸው የሚዲያ ሰዎች ጥቃቱ እንደሚፈጠር ቀድመው ያውቃሉ ብለዋል።
ሲፈጸም ደግሞ የሚያባብሱ፡ ደምወዛቸውና ምንዳቸው ይሀው የሆኑ ሰዎች አሉ።
በእነዚህ የሚዲያ ሰዎች አካሄድ ተጠልፋችሁ አብራችሁ የጥፋቱ ተባባሪ እንዳትሆኑ ሲሉ በተለይ ለወጣቱ ትውልድ መልዕክታቸውን አሰምተዋል።
ተፎካካሪና አክቲቪስት ነን ባዮች በማለት የጠቀሷቸው ወገኖችንም ማስተዋል ይኑራችሁ ሲሉ መክረዋል።
ወጣቶች በማያውቁት አጀንዳ ከመነዳት እንዲቆጠቡ መልዕክት ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ኢትዮጵያውያን የከፈሉት መስዋዕትነት ዋጋ እንዳያጣ የሚችለው ሁሉ እንዲያደርግ አደራ በመስጠት ጥሪ አድርገዋል።
No comments:
Post a Comment