( ኢሳት ዜና መስከረም 08 ቀን 2011 ዓ/ም ) ከነሃሴ 21 የስራ ማቆም አድማ ጋር በተያያ የታሰሩት የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች እንዲፈቱ የድርጅቱ ሰራተኞች ለጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ በጻፉት ደብዳቤ አመልክተዋል። ሰራተኞቹ ጥያቄያቸው ፍትሃዊ ቢሆንም፣ ተገቢውን መልስ ከመስጠት ይልቅ ተገደው ወደ ስራ እንዲመለሱ መደረጉን ተቃውመው፣ ተቃውሞውን አስተባብረዋል በሚል የታሰሩት 9 ባልደረቦቻቸው ከእስር ተፈተው ስራቸውን እንዲጀምሩ እንዲደረግ ጠይቀዋል። ሰራተኞች በደብዳቤያቸው “ ያቀረብነው የመብት ጥያቄዎች መ/ቤቱ በቸልታ በማለፍ ጉዳዩ መጨረሻ ላይ ሲደርስ ሰራተኞው ሃላፊነቱን መወጣት እንዳልቻለ በማድረግ የማይገባ ግዴታ ውስጥ በማስገባት ወደ ስራ እንድንመለስ ከማድረግ ባለፈ የስራ ባልደረቦቻችን ሁሉም በጋራ በመሆን የመብት ጥያቄ ባቀረቡበት ሁኔታ 9ኙ ሰራተኞች ብቻ የጥያቄው አቅራቢዎችና የጉዳዩ አስተባባሪዎች እንዲሆኑ በማድረግ በእስር ሆነው በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጉላሉ ማድረጉ ተገቢነት የሌለው “ ነው በማለት አቤቱታቸውን አቅርበዋል። መስከረም 7 ቀን 2011 ዓም ለተጻፈው ደብዳቤ የጠ/ሚኒስትር ጽ/ቤት መልስ ይስጥ አይስጥ አልታወቀም። በጉዳዩ ዙሪያ ሰራተኞችን አነጋግረን ይዘን ለመቅረብ ሙከራ እንደምናደርግ ለመግለጽ እንወዳለን።
No comments:
Post a Comment