Monday, September 3, 2018

የአርበኞች ግንቦት ታጋዮች አባላት ወደ አገራቸው ተመለሱ

 ( ኢሳት ዜና ነሐሴ 28 ቀን 2010 ዓ/ም ) ኤርትራ ውስጥ በትጥቅ ትግል ላይ የቆዩ የሰራዊቱ አባላት ትናንት ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ በተለያዩ ከተሞች ህዝቡ ወደ አደባባይ በመውጣት አቀባበል አድርጎላቸዋል። በሁመራ፣ በጎንደርና በወረታ ህዝቡ ወደ አደባባይ ወጥቶ አቀባባል አድርገዋል። ለታጋዮች አቀባበል ያደረጉት የክልሉ የኮሚኒኬሽን ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን፣ በተለያዩ ጎራ የተሰለፉ ወንድማማቾች በተሰለፉበት ጎራ አንደኛው ሌላኛውን ሊያሸንፍ ይችላል፣ ኢትዮጵያ ግን አታሸንፍም ብለዋል።
የአማራ ክልል መንግስት ሰራዊቱን በታላቅ ወንድማዊ ፍቅርና አክብሮት እንደሚቀበላቸውና የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው ተናግረዋል። አርበኞች ግንቦት7ትን በመወከል ንግግር ያደረጉት አቶ ሞላ ይግዛው፣ መሳሪያችን አስቀምጠን የብዕር፣ የሃሳብ ትግል ለማድረግ ወደ አገራቸውን መግባታቸውን ተናግረዋል። ታጋዮች ወደ አገራቸው ሲመለሱ መቋቋሚያ እንደሚሰጣቸው፣ ለወደፊቱም በዘላቂነት ሳይቸገሩ ከህብረተሰቡ ተቀላቅለው አስተዋጽዖ የሚያደርጉትበት መንገድ እንደሚቀየስ የአርበኞች ግንቦት7 ዋና ጸሃፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ተናግረዋል፡፡ በሰሜን ጎንደርና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የትጥቅ ትግል ሲያካሂዱ የቆዩ ሃይሎች ቁጥራቸው ከፍተኛ በመሆኑ እነሱን ወደ ሰላማዊ ህይወት ቀይሮ ማቋቋም ትልቅ ፈተና መሆኑን የገለጹት አቶ አንዳርጋቸው፣ እነዚህ የሰራዊት አባላት የተኩስ አቁም እንዲያደርጉ እንደተነገራቸውም ገልጸዋል። እነዚህን ታጋዮች ወደ ሰላማዊ ኑሮ እንዲመለሱ ለማድረግ ከመንግስት፣ ከአለማቀፍ ድርጅቶችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተነጋገሩ መሆኑንም አክለው ተናግረዋል ሰራዊቱን በዚህ ሰዓት መበተን ትክክል ነው ወይ ተብሎ ለተጠየቁት ደግሞ፣ በአገሪቱ ውስጥ ያለውን የፖለቲካ ሁኔታ አይቶ ድርጅቱ እዚህ ውሳኔ ላይ መድረሱን ገልጸዋል።

No comments:

Post a Comment