Tuesday, September 18, 2018

የማያዳግም ርምጃ ለመውሰድ ዝግጅት ተጠናቋል ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 8/2011) መንግስት ያለበትን የህግ የበላይነትና የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ ሃላፊነት ለመወጣት ማንኛውንም ህጋዊ፣ የማያዳግምና ተገቢ ርምጃ ለመውሰድ በሙሉ ዝግጅትና አቋም ላይ ነው ሲል የብሔራዊ የደህንነት ምክር ቤት አስታወቀ።
ምክር ቤቱ በወቅታዊው የኢትዮጵያ ሁኔታ ላይ ባወጣው መግለጫ የጥፋት ሃይሎች የመንግስትን ሆደ ሰፊነት ከአቅመ ቢስነት በመቁጠር የወጣቱን ስሜት በማነሳሳት የሚፈፅሟቸው ወንጀሎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሱና እየተበራከቱ በመምጣታቸው መንግስት ሰላምና መረጋጋትን የማስከበር ሃላፊነቱን ለመወጣት በመስራት ላይ ነው ብሏል።
ልዩነትን የሚያራግቡና ብጥብጥን የሚቀሰቅሱ አክቲቪስቶችና የፖለቲካ ፓርቲዎች እጃሁን ሰብስቡ ይላል የብሄራዊ ደህንነት ምክር ቤት መግለጫ።
የብሄራዊ ደህንነት ምክር ቤቱ ዛሬ ባወጣው መግለጫ የህግ የበላይነት የዲሞክርሲ ስርዓት ግንባታ አንዱ መገለጫ መሆኑን አጽንኦት ሰጥቶበታል።
የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ከህግ የበላይነት ውጭ ፈጽሞ የሚታሰብ አይደለም ብሏል የምክር ቤቱ መግለጫ።
አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት እንደቀደሙት መንግስታት ነገሮችን በሃይል ለመፍታት አይቸኩልም ይህ አዲስ አካሄድ ፍርሃትና አቅመ ቢስነት የመሰላቸው ሃይሎች ተሳስተዋል ብሏል።

የመንግስትን ትዕግስት እንደ ደካማነት በመቁጠር የወጣቱን ስሜት በማነሳሳት የሚፈጽሟቸው ወንጀሎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከተ መጥቷል ነው ያለው የብሄራዊ ደህንነት ምክር ቤት።
በአዲስ አበባና ዙሪያዋ ሰሞኑን የተከሰቱትን ጥቃቶች ያነሳው የብሄራዊ ደህንነት ምክር ቤት መግለጫ ይህን መሰል ጥቃት ወደ ሌሎች የሀገሪቱ አከባቢዎችም ለማስፋፋት ጥረት እያደረጉም ነው ብሏል።
ዓማላማቸው በተያዘው መስከረም ወር መጨረሻ የሚካሄደውን የኢህ አዴግ ጉባዔን ለማደናቀፍም ጭምር እንደሆነ በመግለጫው ተመልክቷል።
የእነዚህ በስም ያልተጠቀሱ ሃይሎች አቅደው፡ ድብቅ የፖለቲካ ዓላማ ይዘው ህዝብን ከህዝብ በማጋጨት ሀገሪቱን ወደማያባራ እልቂት ለመክተት የሚንቀሳቀሱ እንደሆኑ ደርሼባቸዋለሁ ያለው የብሄራዊ ደህንነት ምክር ቤት መግለጫ ይህን የሀገር አደጋ ለመቀልበስ መንግስት ማንኛውንም እርምጃ ለምውሰድ አቅሙ እንዳለው መግለጽ ያስፈልጋል ብሏል።
በመሆኑም ለዜጎች ህይወት ዋስትና ለመስጠት መንግስት ማንኛውንም ህጋዊና የማያዳግም እርምጃ መውሰድ የጀመረ ሲሆን ይህ ሁኔታ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል በማለት አሳስቧል።
ወጣቱም በስሜት እየተገፋፋ፣ የፖለቲካ ነጋዴዎችና ዘራፊዎች መሳሪያ እየሆነ አፍራሽ ወደሆነ ድርጊት መምጣቱን መረዳት ይኖርበታል ያለው የምክር ቤቱ መግለጫ በህገ-ወጥ ድርጊት ላይ የሚሳተፍ ወጣትና ማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል ህጋዊ እርምጃ የሚወሰድበት መሆኑን አውቆ ከጥፋት ተግባሩ እንዲሰበሰብ መንግስት ያሳስባል ሲል አስጠንቅቋል።
የብሄራዊ ደህንነት ምክር ቤቱ መግለጫ በስም ያልተጠቀሱ አክቲቪስቶችና የፖለቲካ ፓርቲዎች ልዩነትን ከሚያሰፉና ብጥብጥ ከሚያነሳሱ ድርጊቶች እንዲቆጠቡ ማሳሰቢያ ሰጥቷል። እጃችሁን አንሱ በማለትም ማስጠንቀቂያውን አስፍሯል።
በተያያዘ ዜና በቡራዩና አከባቢዋ በተፈጸመው ጥቃት ተጠርጥረው በተያዙ ግለሰቦች የባንክ ሂሳብ ውስጥ 8ሚሊየን ብር መገኘቱን የኦሮሚያ ክልል አስታወቀ።
የክልሉ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ እንደገለጹት 99 አባላት ካለው የጥቃት ፈጻሚ ቡድን ውስጥ ስድስት የጦር መሳሪዎች፣ የባንክ ደብተር፣ ሀሰተኛ ማህተሞችና ከ8 ሚሊየን ብር በላይ ገንዘብ ተገኝቷል።

No comments:

Post a Comment