Thursday, September 6, 2018

የሜቴክ ዘረፋ የተደራጀ ሌብነት ነው ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ጳጉሜ 1/2010) በመሰረታዊ ብረታብረት ኮርፖሬሽን ሜቴክ ውስጥ የሚካሄደው ዘረፋ ብሔርን መሰረት ያደረገና እጅግ የተደራጀ ሌብነት መሆኑ ተገለጸ።

ሜቴክን ከምስረታው ጀምሮ የሚያውቁት ብርጋዴር ጄኔራል መላኩ ሽፈራው ለኢሳት እንደገለጹት በዘረፋው ሒደት በደላላነት በሚሊየን ዶላሮች የሃገሪቱን ሃብት የሚቀራመቱ ግለሰቦችን በዝርዝር አስቀምጠዋል።


ዘረፋውን በመቃወማቸውም ከተቋሙ የተባረሩና የተሰናበቱ የአማራ፣የኦሮሞና የሌላ ብሔረሰብ ተወላጆችን ስም ዘርዝረዋል።

በሃገር መከላከያ ሚኒስቴር የመረጃ መረብ ከፍተኛ ሃላፊ የነበሩት ብርጋዴር ጄኔራል መላኩ ሽፈራው ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት ትራም ከተባለ ሃንጋሪ ከሚገኝ ኩባንያ ጋር የ6 ሚሊየን ዩሮ ስምምነት ከተደረገ በኋላ የአጠቃላይ ገንዘቡ 10 በመቶ ኮሚሽን ለእነ ጄኔራል ክንፈ ዳኘው የጥቅም ሸሪኮች ከተከፈለ በኋላ ተግባራዊ ሳይሆን መቅረቱን አስታውሰዋል።

በአፋር ክልል “ወያኔ”የሚል ስያሜ የተሰጠው ተክል ወደ ነዳጅ ለመቀየር በሚል ለተያዘ ፕሮጀክት ከውጭ ኩባንያ ጋር የ10 ሚሊየን ዩሮ ስምምነት ከተደረገ በኋላ የኮሚሽን ክፍያው ተፈጽሞ ፕሮጀክቱ መክኗል ጄኔራል መላኩ ሽፈራው እንደገለጹት።

በኮምቦልቻ ብረታ ብረት ፣በሕዳሴው ግድብ የነበረውንም የዘረፋ ሁኔታ በዝርዝር የተመለከቱት ብርጋዴር ጄኔራል መላኩ ሽፈራው፣ከምንጣሮ ጋር እንዲሁም ከተርባይን ግዢ ጋር የተደረገውን የተቀናጀ ዘረፋም ተመልክተዋል።

በስኳር ኮርፖሬሽን፣በያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ፣በመብራት ሃይል የኢነርጂ ሜትር ግዢ እንዲሁም በመርከብ፣በታንክና በሌሎች የጦር መሳሪያዎች ግዢ ውስጥ የሜቴክና የሃገሪቱ ሃብት የባከነበትን ሁኔታ በዝርዝር ተመልክተዋል።

ሜቴክ 15 የግል መኖሪያ ቤቶችና ሆቴሎችን በመግዛት እንዲሁም በሰው አልባ አውሮፕላን ፕሮጀክት ያካሄደውን ዘረፋ የዘረዘሩት ብርጋዴር ጄኔራል መላኩ ሽፈራው በዚህ ሒደት ዋናዎቹ ተዋናዮች ከድርጅቱ ሃላፊዎች በተጨማሪ በድለላ የተሰማሩትን ዘርዝረዋል።

ብርጋዴር ጄኔራል መላኩ በድለላ ውስጥ ሲሳተፉ የነበሩትም አቶ ደግነህን ጨምሮ ኮለኔል ተወልደ፣ኮለኔል ክብሮም፣ኮለኔል አታክልቲና ሌሎችንም በዝርዝር አስቀምጠዋል። ይህንን በመቃወማቸውም ኮለኔል ጌትነት፣ኮለኔል ሽመልስ ክንዴ፣ኮለኔል አብዱሰላም ኢብራሒምና ሌሎች መኮንኖችም እንደሚገኙበት በቃለ ምልልሱ ላይ ገልጸዋል።

ከብርጋዴር ጄኔራል መላኩ ሽፈራው ጋር የተደረገውን ሙሉ ቃለ ምልልስ በኢሳት ቴሌቪዥንና በኢሳት ዩቲዮብ የምናቀርብ ይሆናል።

No comments:

Post a Comment