(ኢሳት ዜና መጋቢት 25 ቀን 2010 ዓ/ም) ባለፈው ሳምንት በነበረው የፍርድ ቤት ውሎ አቶ መላኩ ፋንታ በተወሰኑ ክሶች ነጻ እንደተባሉ፣ ደህንነቶች ዳኞችንና የዳኞቹን ፕሬዝዳንት ጭምር በመሰብሰብ እንዳነጋገሯቸው፣ “ ለምንድነው ነፃ የላችሁት?” የሚል ጥያቄ እንደጠየቁዋቸው ምንጮች ገልጸዋል። ዳኞቹ “ ሰውየው ከታሰረ ረጅም አመት ነው፣ ክሱን በደንብ አይተን የሚያስፈርድበት ሆኖ አላገኘነውም” ብለው ሲመልሱ፣ ደህንነቶቹም “ከአሁን በሁዋላ ባሉበት ክሶች ላይ እንድትፈርዱበት፣ ነፃ እንዳትሉት” ብለው ሲያስፈራሩ፣ ምክትል የዳኞች ሰብሳቢ ስብሰባውን ጥለው ወጥተዋል። ጋዜጠኞች የፍርድ ቤት ውሎውን እንዳይዘግቡ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸውም ታውቋል ። የፋና ጋዜጠኛ በቀኑ ስድስት ሰአት የዜና ፕሮግራም ላይ ዜናውን ከሰራችው በሁዋላ፣ የስድስት ሰአቱ ዜና አስራ አንድ ሰአት ላይ የሚደገም ቢሆንም ፣ በደህንነቶች ትእዛዝ ዜናው እንዳይደገም ተደርጓል። የፋናዋ ጋዜጠኛም ተጠርታ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷታል ። ኢቢሲ የእነመላኩን የፍ/ቤት ዘገባ በተከታታይ ይሰራ የነበረ ቢሆንም፣ አቶ መላኩ ነጻ በተባሉበት ቀን ዘገባውን አልሰራም። አቶ መላኩ የቀራቸው አራት ክሶች ሲሆኑ፣ በአራቱም ክሶች ጥፋተኛ ተብለው እንዲፈረድባቸው ደህንነቶች ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ነው። ባለፈው በተሰጠው ውሳኔ ላይም ዓቃቢ ህግ ይግባኝ እንዲጠይቅ ታዟል ። “ ኢቢሲም ሆኑ ሌሎች የመገናኛ ብዙሃን አቶ መላኩ ነፃ ሲባሉ ያልዘገቡት ህዝቡ እንዲያውቅ ስላልተፈለገ ፣ ህዝብ እንዲያውቅ የተፈለገው ወንጀለኛነቱን እንጂ ነፃ ሰው መሆኑን አይደለም “ ሲሉ ምንጮች ተናግረዋል።
No comments:
Post a Comment