(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 25/2010)ባለፈው በጀት አመት በኢትዮጵያ ካሉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በ10 ዩኒቨርስቲዎች ብቻ የ3 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ጉድለት መኖሩን የጠቅላላ ኦዲት ቢሮ ገለጸ።
በመቀሌ ዩኒቨርስቲ ብቻ 64 ሚሊየን ብር ጉድለት በመኖሩ በፓርላማ የመንግስት ወጭ አስተዳደርና ቁጥጥር ኮሚቴ ተቋሙን መገሰጹ ታውቋል።
በኢትዮጵያ ካሉ 158 የመንግስት ተቋማት ብቻ ባለፈው አመት የ20 ቢሊየን ብር ጉድለት መገኘቱን የጠቅላላ ኦዲት ቢሮ መግለጹ ይታወሳል።
በኢትዮጵያ የተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች በበጀት እጥረት ምክንያት የአመቱን የትምህርት ክፍለ ጊዜ በአስቸኳይ እንዲያጠናቅቁ ተማሪዎች በተፋጠነ ሂደት ተከታታይ ፈተናዎችን እየወሰዱ ይገኛሉ።
ከፍተኛ የገንዘብ እጥረት አለ በሚባልበት በዚህ ሁኔታ ግን የመንግስት ዩኒቨርስቲዎች ከፍተኛ ገንዘብ እያባከኑና የጉድለቱ መጠን ከልክ በላይ መሆኑ ይነገራል።
በጠቅላላ ኦዲት ሪፖርት መሰረት ባለፈው አመት ብቻ በ10 የኢትዮጵያ ዩኒቨርስቲዎች የ3 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር ጉድለት ተገኝቷል።
ከነዚሁ ዩኒቨርስቲዎች መካከል ደግሞ የመቀሌ ዩኒቨርስቲ 64 ሚሊየን ብር አጉድሏል ነው የተባለው።
ፎርቹን አዲስ የተባለው ጋዜጣ እንደዘገበው በፓርላማ የመንግስት ወጪ አስተዳደር ቁጥጥር ኮሚቴ ጉድለቱን አስመልክቶ የመቀሌ ዩኒቨርስቲን ተችቷል።
ጉድለቱ ከደሞዝ አከፋፈል ጋር በተያያዘ ያለ ደረሰኝ የተስተናገደ በመሆኑ ደረሰኝ ስለሌለው ወጪ እና ያልተወራረደ በሚል የሚገለጽ መሆኑ ነው የተነገረው።
የመቀሌ ዩኒቨርስቲ ግን ወጭው በምክንያት የወጣ ነው በሚል ለማስረዳት ሙከራ ማድረጉን ጋዜጣው የተቋሙን ሃላፊዎች ጠቅሶ ዘግቧል።
በኢትዮጵያ ካሉ 158 የመንግስት ተቋማት ብቻ በባለፈው በጀት አመት የ20 ቢሊየን ብር ጉድለት መኖሩን የጠቅላላ ኦዲት ቢሮ ሪፖርት ያመለክታል።
No comments:
Post a Comment