Tuesday, April 3, 2018

እነአቶ መላኩ ፈንታ በተወሰኑ ክሶች ጥፋተኛ ተባሉ

(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 25/2018) በከባድ የሙስና ወንጀል ተከሰው ከአራት ዓመታት በላይ ሲከራከሩ የከረሙት እነአቶ መላኩ ፈንታ በተወሰኑ ክሶች ጥፋተኛ ሲባሉ በሌሎች ክሶች ደግሞ በነፃ ተሰናበቱ፡፡
አቶ መላኩና አቶ ገብረ ዋህድ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተርና ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሆነው በሚሠሩበት ወቅት ሙስና ፈጽመዋል በሚል ክስ ቀርቦባቸው ነበር ።
በዚሁ ክስ የተካተቱት አቶ መላኩ ፈንታ፣ አቶ ገብረ ዋህድ ወልደ ጊዮርጊስ፣ አቶ በላቸው በየነ፣ አቶ ማሞ አብዱ፣ አቶ አሞኘ ታገለና አቶ ጥሩነህ በርታ ናቸው፡፡
ተከሳሾቹ ባቀረቡት የመከላከያ ምስክሮችና የሰነድ ማስረጃዎች ሊያስተባብሉ አልቻሉም በሚል ጥፋተኛ ናቸው ሲል በተወሰኑ መዝገቦች ላይ ፍርድ ቤቱ ወሳኔ ሰጥቷል፡፡
ሁለቱም ተከሳሾች ያማቶ ኢትዮጵያ የተባለ ድርጅት መክፈል የሚገባውን ግብር ባለመክፈሉ ከተወሰነበት ግብር 50 በመቶ አስይዞ መከራከር ቢኖርበትም፣ ሥልጣናቸውን ያላግባብ በመጠቀምና ዝቅ አድርገው በመገመት የመንግሥት ሥራን በማያመች ሁኔታ መምራታቸውን ማስተባበል ባለመቻል ጥፋተኛ ተብለዋል፡፡
አቶ ገብረ ዋህድ ጥፋተኛ የተባሉት በተመሳሳይ የክስ መዝገብ በአምስተኛ ክስ ነው።

ኬጂኤች ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ከ1998 እስከ 2001 ዓ.ም. ድረስ መክፈል የነበረበትን ግብር፣ በኦዲት ተረጋግጦበትና ይግባኝ ቢልም ፀንቶበት እያለ፣ ‹‹እንዲሻሻል›› የሚል ሕገወጥ ትዕዛዝ በመስጠት፣ የመንግሥትን ሥራ በማያመች አኳኃን መርተዋል ተብሎ፣ የቀረበባቸውን ክስ ማስተባበል አልቻሉም ተብሏል፡፡
አቶ መላኩና አቶ ገብረ ዋህድ በነፃ የተሰናበቱበት ክስ ደግሞ፣ በተመሳሳይ የክስ መዝገብ ከቀረበባቸው ሰባተኛ ክስ ነው፡፡
የተከሰሱበት ክስ ኦቨርኒጋስ ቴክኖሎጂ ሊሚትድ መክፈል የነበረበትን 34.3 ሚሊዮን ብር እንዲከፍል ከተወሰነ በኋላ ጠቋሚ ላልሆኑ ሰዎች ጠቋሚ እንደሆኑ በማስመሰል ሰነድ አዘጋጅተው እንዲመዘገቡ አድርገዋል የሚል ነበር፡፡
ክሱን በበቂ ሁኔታ በመከላከላቸው በነፃ ተሰናብተዋል፡፡ አቶ ገብረ ዋህድ ለብቻቸው ከተከሰሱበት ግብር ያልከፈሉ ድርጅቶችን ሕገወጥ የኦዲት ሪፖርት በመሥራት እንዲከፍሉ አስደርገዋል ተብሎ ከቀረበባቸው ክስ ነው፡፡
በብቃት በመከላከላቸውም በነፃ እንዲሰናበቱ ሲል ፍርድ ቤቱ ፍርድ ሰጥቷል፡፡
አቶ መላኩ 3.2 ሚሊዮን ብር ምንጩ ያልታወቀ ሀብት አፍርተዋል የሚል በዘጠነኛ ክስ፣ 1.4 ሚሊዮን ብር ቤት ለመገንቢያ ብለው ተበድረው 1,050,286 ብር ለባንኩ መክፈላቸው በአሥረኛ ክስ የተጠቀሰባቸው ነው።
ፍርድ ቤቱ ግን እሳቸው በሥራ ላይ የቆዩበትን ዘመን፣ ይከፈላቸው የነበረን ደመወዝ፣ የአገር ውስጥና የውጭ አገር አበል፣ እንዲሁም የቦርድ አባል በመሆናቸው ይከፈላቸው የነበረን ክፍያ በማሥላት፣ እንደ ወንጀል የተቆጠረውና ለክስ ያበቃቸው ገንዘብ ተገቢ ባለመሆኑ በነፃ አሰናብቷቸዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ ከቀትር በኋላ በሰጠው ፍርድ የተመለከተው ክስ ደግሞ የቀረበባቸውን አቶ መላኩ፣ አቶ ገብረ ዋህድ፣ አቶ አምኘ፣ አቶ ተመስገን ጉላላ፣ አቶ ያለው ቡላ፣ አቶ ነጋ ገብረ እግዚአብሔር (ነፃ ትሬዲንግና ባሰፋ ትሬዲንግ)፣ አቶ ከተማ ከበደ (ኬኬ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር)፣ አቶ ጌቱ ገለቴ (ጌት አስ ኢንተርናሽናል) እና አቶ ገብረ ሥላሴ ገብሬ (ኮሜት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር) ናቸው፡፡
ክሱ በዋናነት በተለይ ከላይ የተጠቀሱት የአቶ ነጋ፣ የአቶ ከተማ፣ የአቶ ገብረ ሥላሴና የአቶ ጌቱ ድርጅቶች በተሽከርካሪዎቻቸው ከውጭ የሚያስገቡት ጥሬ ዕቃ በጂቡቲ በኩል ጋላፊ ላይ በማሽን ተፈትሾ ማለፍ ሲገባው፣ ከአቶ መላኩና ከአቶ ገብረ ዋህድ ጋር ባላቸው የጥቅም ትስስር የተመረጡና የማይፈተሹ እንደሆኑና ‹‹ይለፍ›› የሚል ምልክት በመስጠት፣ እስከ መዳረሻ ድረስ ሳይፈተሹ እንዲያልፉ አድርገዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸው ነበር፡፡
ሆኖም ግን አቶ ነጋ፣ አቶ ከተማና አቶ ገብረ ሥላሴ በብቃት በመከላከላቸው በነፃ እንዲሰናበቱ ፍርድ ሰጥቷል፡፡
አቶ ጌቱ ገለቴ ግን ክሱ የተካሄደው በሌሉበት መሆኑን ጠቁሞ ጥፋተኛ ብሏቸዋል፡፡ አቶ መላኩና አቶ ገብረ ዋህድም ሥራን በማያመች አኳኃን መምራት በማለት ጥፋተኛ ብለዋቸዋል፡፡
ክስ ከተመሠረተባቸው ከ2006 ዓ.ም. መጀመርያ ወራት ጀምሮ ክሳቸውን ሲመረምር የከረመው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት የጥፋተኝነትና በነፃ እንዲሰናበቱ ፍርድ የሰጠው፣ ዓርብ መጋቢት 21 ቀን 2010 ዓ.ም. ከቀትር በፊትና በኃላ ነው፡፡
ፍርድ ቤቱ በሰጠው ትዕዛዝ በሁለቱም የክስ መዝገብ ጥፋተኛ የተባሉ ተከሳሾች በ15 ቀናት ውስጥ የቅጣት ማቅለያቸውን፣ እንዲሁም ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ ደግሞ በአሥር ቀናት ውስጥ የቅጣት ማክበጃ እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቶ፣ ለሚያዝያ 22 ቀን 2010 ዓ.ም. ቅጣት ለመወሰን ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

No comments:

Post a Comment