(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 4/2010) የሐሮማያ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በተቋሙ ውስጥ ምግብ በመከልከላቸው ግቢያቸውን ጥለው መውጣታቸው ተነገረ።
ተማሪዎቹ በዩኒቨርስቲው የሚቀርብላቸው ምግብ በመቆሙ ሕይወታቸውን ለማቆየት ግቢያቸውን ለቀው ወደ ሐሮማያ ከተማ ለመሔድ ተገደዋል።
ዩኒቨርስቲው ለተማሪዎቹ ምግብ እንዳይሰጥ የከለከለው በግቢው ውስጥ የትምህርት ማቆም አድማ በመጀመሩ ነው ተብሏል።
የሃሮማያ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በግቢያቸው ውስጥ ተማሪዎች በወታደራዊ እዝ/ኮማንድ ፖስት/በመታሰራቸው ይህንኑ በመቃወም ትምህርት አቁመዋል።
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ሁለት ተማሪዎች ለአዲስ ስታንዳርድ ዘጋቢ እንደገለጹት በሐሮማያ ዩኒቨርስቲ በቀጠለው የእስር ርምጃ እስካሁን 20 ተማሪዎች በኮማንድ ፖስቱ በቁጥጥር ስር ውለዋል።
እናም ለምን ተማሪዎቹ ታሰሩ በሚል የትምህርት ማቆም አድማ በቀሩት ተማሪዎች በመጀመሩ ዩኒቨርስቲው በግቢው ውስጥ የሚሰጠው ምግብ እንዲቆም ማድረጉን ተማሪዎቹ ገልጸዋል።
በዚህም ምክንያት የአለማያ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ምግብ ፍለጋ ከተቋማቸው 5 ኪሎ ሜትር ርቃ ወደምትገኘው ሃሮማያ ከተማ መሄዳቸው ነው የተነገረው።
የሃሮማያ ከተማ ነዋሪዎች ለተማሪዎቹ ምግብ እየሰጧቸው እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል።
የሃሮማያ ዩኒቨርስቲ አመራሮች ከአገዛዙ ታጣቂዎች ጋር በመሆን ተማሪዎቹ ትምህርት እንዲጀምሩ ያለበለዚያ ግን እንደሚባረሩ ሲያስጠነቅቁ እንደነበር የአይን እማኞች ተናግረዋል።
አዲስ ስታንዳርድ የዩኒቨርስቲውን አመራሮች ስለጉዳዩ ለማነጋገር ሙከራ ቢያደርግም እንዳልተሳካለት ገልጿል።
No comments:
Post a Comment