Wednesday, April 18, 2018

ወ/ሮ ጠይባ ሃሰን የአቶ ለማ መገርሳ ምክትል ሆነው ተሾሙ

(ኢሳት ዜና ሚያዝያ 10 ቀን 2010 ዓ/ም) የሻሸመኔ ከተማ ከንቲባ የሆኑት ወ/ሮ ጣይባ ሃሰን የኦሮምያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ተሹመዋል። በሻሸመኔ ህዝባዊ የለውጥ ትግል በሚካሄድበት ወቅት፣ የአጋዚ ወታደሮች ሲወስዱት የነበረውን እርምጃ አጥብቀው በመቃወም እንዲሁም በተለያዩ ዝርፊያዎች የተሰማሩ የህወሃት አባላትን በቁጥጥር ስር በማድረግና በድፍረት ለመገናኛ ብዙሃን አሳባቸውን በመስጠት የሚታወቁት ወ/ሮ ጣይባ ሃሰን ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው መመረጣቸው ኦህዴድ ጠንካራ አባሎቹን ወደ ማዕከል እየሰበሰበ የሚል አስተያየት እንዲሰጥ አድርጓል። የኦፌኮ ም/ል ሊመንበር አቶ በቀለ ገርባ ከእስር ሲፈቱ እርሳቸውን ለመቀበል በተዘጋጀ ስነስርዓት ላይ በመገኘታቸው አድናቆት ሲቸራቸው የቆዩት የአዳማ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች ሃቤቤ ደግሞ የኦህዴድ ማዕከላዊ ጽ/ቤት ሃላፊ ሆነው
ተሹመዋል። ሃሳባቸውን በድፍረት በመግለጽ የሚታወቁት የክልሉ የኮሚኒኬሽን ሃላፊ የነበሩት አቶ አዲሱ አረጋ ደግሞ የገጠር የፖለቲካ እና የአደረጃጃት ሃላፊ ሆነዋል። የመንግስት የኮሚኒኬሽን ሃላፊ የሆኑት ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ ደግሞ ከፌደራል ስልጣናቸው ተነስተው ወደ ክልል በመውረድ የአቶ አዲሱ አረጋን የቀድሞ ቦታ በመያዝ የክልሉ የኮሚኒኬሽን ሃላፊ ሆነዋል። በሌላ በኩል ደግሞ አዲሱ ጠ/ሚኒስትር ነገ ሃሙስ የካቢኔ አባሎቻቸውን በፓርላማ አቅርበው ያሾማሉ ተብሎአል። ለአመታት አፈ ጉባኤ በመሆን የሰሩት አቶ አባ ዱላ ገመዳም ከስልጣናቸው ተነስተው አዲስ አፈ ጉባኤ እንደሚሾም ፓርላማው ካወጣው መርሃ ግብር ለመረዳት ተችሎአል። አዲስ የሚሾመው አፈ ጉባኤ ከኦህዴድ ውጭ እንደሚሆን አቶ አባ ዱላ ለቢቢሲ የአማርኛው ክፍል በሰጡት ቃለ ምልልስ ጠቅሰዋል።

No comments:

Post a Comment