(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 24/2010)በኢትዮጵያ ዘረኝነትና መከፋፈልን ማጥፋት እንደሚገባ በፓርላማ የሃገር መሪነትን ስልጣን የተረከቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አስገነዘቡ።
ኢትዮጵያ የገጠማትን ፈተና ወደ እድልና መልካም አጋጣሚ መቀየር እንደሚገባ ዶክተር አብይ ለፓርላማው በስልጣን ርክክብ ስነስርአቱ ላይ ተናግረዋል።
ካለፉት 27 አመታት ወዲህ ባልታየ ሁኔታ ኢትዮጵያን ከፍ በማድረግ ያወደሱት ዶክተር አብይ ሰብአዊነት ያለው ንግግር በማድረግ በብዙዎች ዘንድ አድናቆትን አትርፈዋል።
ዶክተር አብይ አህመድ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ከአቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ስልጣኑን በመረከብ በፓርላማ ተሰይመዋል።
በዚሁ ስነስርአት ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ታዲያ ካለፉት 27 አመታት ወዲህ ባልታየ ሁኔታ ኢትዮጵያን ከፍ በማድረግ የሕዝቡን አንድነት የሚያስተሳስር ንግግር አድርገዋል።
ኢትዮጵያ በታሪኳ ታላቅ ሃገር ሆና የቆየችው ሁሉም ብሔሮች በከፈሉት ማስዋዕትነት ነው ብለዋል።
በአሁኑ ጊዜ በሃገሪቱ በተፈጠረው ችግር አለም ሳይቀር በአግራሞትና በስጋት የተመለከተው ሁኔታ እንደተፈጠረም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናግረዋል።
እናም አሉ ጉድለቶች ተቀርፈው አስቸኳይ መፍትሄ የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች አሉ ነው ያሉት።
ከዚህ ቀደም አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ ለመጀመር እድሎች ተገኝተው በአግባቡ መጠቀም እንዳልተቻለም አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገልጸዋል።
እናም የአሁኑ የስልጣን ሽግግር አዲስ ምዕራፍ የሚጀመርበት ይሆናል ብለዋል።
እንደ ዶክተር አብይ አህመድ ገለጻ በኢትዮጵያ ዘረኝነትና መከፋፈል ጠፍቶ ሕዝቡ ልዩነቱን በማቻቻል አንድነቱን ማጠናከር ይኖርበታል።
በኢትዮጵያ የሃሳብ ልዩነትን ማስተናገድ በዲሞክራሲያዊ አስተሳሰብ የመጀመሪያውና የመጨረሻው መርህ ሊሆን እንደሚገባም ዶክተር አብይ ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ችግሮች ሕይወታቸው ለተቀጠፈው ኢትዮጵያውያንም በይፋ ይቅርታ ጠይቀዋል።
በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው ገብተው እንዲሰሩና በጋራ አብረን ሃገራችንን እናሳድግ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
ከኤርትራ ጋር ውይይት እንዲጀመርም የሁለቱን ሕዝቦች አንድነት በማስታወስ ከሃገሪቱ መንግስት ምላሽ እንደሚጠብቁ ዶክተር አብይ ገልጸዋል።
የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ የማነ ገብረመስቀል ለቢቢሲ በሰጡት መግለጫ ሰላም ለሁለቱም ሃገር ሕዝብ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል ሆኖም በቅደሚያ የኢትዮጵያ ወታደሮች ከግዛታችን ሊወጡ ይገባቸዋል ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለሴቶች፣ ለወጣቶች እና ለልዩ ልዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት እንደሚገባም አሳስበዋል።
ዶክተር አብይ ስለ እናታቸውና ስለባለቤታቸው ያላቸውን ፍቅር በመግለጽ ለዚህ ደረጃ ላበቋቸው ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
No comments:
Post a Comment