Tuesday, April 17, 2018

ጠ/ሚኒስትሩና የመቀሌ ቆይታቸው

ጋዜጠኛ መሳይ መኮንን
ሰኞ ሶስተኛ ሳምንታቸውን ይጀምራሉ። ባለፉት ሁለት ሳምንታት በጉዞ፡ በስብሰባ፡ በጉብኝት፡ ተጠምደው ቆይተዋል። ጂጂጋ ሄደው፡ አምቦ ደርሰው ከመቀሌ ቆይተው ወደ አዲስ አበባ ተመልሰዋል። በመሃል በቤተመንግስት ''ተፎካካሪ'' በሚል ከሚጠሯቸው የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች፡ ሲቪክ ማህበራት፡ ታዋቂ ሰዎች ጋር እራት በልተዋል። ነገ 25ሺህ የሀገሪቱን ወጣቶች ይሰበስባሉ።
በዚሁ ከቀጠለ ወደ ባህርዳር ጎራ ብለው የአማራውን ህዝብ መጎብኘታቸው ይጠበቃል። አንዱ ጋር መጥተው ሌላው ጋር መቅረት ችግር አለውና ወደ ሀዋሳ አቅንተው፡ አሶሳ ደርሰው፡ ከሰመራ ጎራ ብለው፡ ከጋምቤላ አርፈው፡ ከሀረር ጆጎል ሄደው፡ ድሬ ከዚራን ብለው ከሸገር አዱ ገነትም ህዝቡን ሰብስበው ኢትዮጵያዊነትን ሰብከው፡ በጣፋጭ ንግግሮች አረስርሰው የጫጉላ ጌዜያቸው እስኪያበቃ እረፍት ባጣ ጉዞ መሰንበታቸው የሚጠበቅ ነው።

ነጋዴዎችን መሰብሰባቸው አይቀርም። ከአራቱም አቅጣጫዎች ሴቶችን ጠርተው ሊያነጋግሩ ይችላሉ። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችም ለብቻቸው ውይይት ያስፈልጋቸዋል። ከ1ሚሊየን በላይ የሚሆኑ የኢትዮጵያ መምህራን እንዳሉም መዘንጋት አይገባም። አርሶ አደሮች የልማታዊው መንግስት አንቀሳቃሽ ሞተር መሆናቸው ይታወቃል። አርብቶ አደሮችም የኢህአዴግ የጀርባ አጥንት በመሆናቸው ከአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር በጫጉላው ሽርሽር ወቅት ቢገናኙ መልካም ነው።😛
ለዚህ ጫጉላ ሽርሽር ሁለት ወርም የሚበቃ አይመስልም። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መቀሌ ላይ ከጣሏቸው አንዳንድ ነጥቦች በቀር በኦህዴድ ስብሰባዎች ላይ የነገሩንን፡ ባለፉት ወራት በተለያዩ በቃለመጥይቆቻቸው የሰበኩንን፡ በበዓለ ሲመታቸው ዕለት ከፍ አድርገው ያሳዩንን የተከበረችና ታላቅ የሆነችውን ኢትዮጵያን ይዘው ቀጥለዋል።
በአንጻሩ የሀገሪቱ ችግር እንደዛው ነው። መታሰሩ ቀጥሏል። የንጹሃን ግድያ አልቆመም። የእርስ በእርስ ግጭቶች በመጠነም፡ ጉዳት ስፋትም ቀጥለዋል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዳለ ነው። እነአንዳርጋቸው አልተፈቱም። እነ ታዬ ደንደአ እዚያው እስር ቤት ናቸው። የህወሀቶች ስግብግብነት ልጓም አጥቶ እየገሰገሰ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጊዜ ይሰጣቸው የሚለው ድምጽ በርክቶ ይሰማል። እስከመቼ? ምን ሲያደርጉ እንመዝናቸው? ለሚለው ተያያዥ ጥያቄ ሾላ በድፍን እንጂ መልስ የሚሰጥ የለም። ካለም አልተሰማም። የጫጉላው ወቅት በዝቷል። ሸልፋቸው ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ አንገብጋቢ ጉዳዮች ተቆልለው እሳቸው ጉብኝቱ ላይ ብቻ ማተኮራቸው ለትዝብት ዳርጓቸዋል። ዛሬ ከደቡብ ኢትዮጵያ እንደምንሰማው በግጭት የሰነበቱት ጉጂዎችና ጌዲዮዎች ወደለየለት ጦርነት ውስጥ ገብተዋል። መንደሮች እየተቃጠሉ ነው። ሰዎች እያለቁ ነው። ሺዎች እየተሰደዱ ነው። አንድ መሪ እንዲህ ዓይነት ቀውስ ሲከሰት መደበኛ ስራዎችን አቁመው ግብረሃይል አቋቁመው ቀውሱን ለማርገብ ይጥራል እንጂ በዙረት አይጠመድም።
መቀሌ ምን ተፈጠረ?
የዶ/ር አብይ የመቀሌው ቆይታቸው ብዥታን የፈጠረ፡ ደጋፊዎቻቸውን ሳይቀር ትካዜ ውስጥ የከተተ ሆኗል።በእርግጥ የእሳቸው መመረጥ በህወሀት መንደር ድንጋጤን ፈጥሯል። የትግራይ ተወላጆች ሁሉም ማለት ባይቻልም አብዛኛው ደስተኛ እንዳልነበር በተለያዩ መልኩ መረዳት ይቻላል። ለአሜሪካን ድምጽ ሬዲዮ ቃላቸውን የሰጡ ሁለት የትግራይ ምሁራን የተናገሩትን ወስደን የትግራይ ህዝብን የልብ ትርታ ከለካነው የዶ/ር አብይ መመረጥ ምቾት የሚሰጥ አይደለም። እናም የትግራይን ህዝብ ይሁንታ ማግኘት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ትኩረት የተሰጠው ይመስላል። ይህን ማድረጋቸው ችግር አይሆንም። ያኮረፈን ማነጋገር ይገባቸዋል። መሪነታቸው ለትግራይ ህዝብ ጭምር በመሆኑ ቀርበው ሊያነጋግሩት እንደሚገባ ይታመናል። በዚህ ተቃውሞ የሚያቀርብ ያለ አይመስለኝም። ጉዳዩ እዛ ሄደው ምን ይላሉ የሚለው ነበር።
እንደመለስ ዜናዊ ''ወርቅ ህዝብ ናችሁ፡ በእሳት የተፈተናችሁ'' የሚል ቃል ይወጣቸው ይሆን? ብሎ የሰጋ ቢኖር አያስገርምም። እንደሃይለማርያም ደሳለኝ '' ለትግራይ ህዝብ ከፍለን የማንጨርሰው የ100 ዓመት እዳ አለብን'' ብለው ቢያስደነግጡንስ? የሚል ፍራቻ ያደረበት ሰውም ሊኖር ይችላል። ሰውዬው እንደሃይለማርያም የሚጃጃሉ አይሆኑም፡ ለራሳቸው ክብር ያላቸው፡ ደፋር ሰው በመሆናቸው ነጥብ ጥለው አይወጡም በሚል እርግጠኛ ሆነው የተናገሩም ነበሩ።
ለእኔ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የመቀሌው ጉብኝት የትግራይን ህዝብ መከፋት በመጠኑ ያስታገሰና የህወሀት መሪዎችን ድንጋጤ በትንሹ ያበረደ ከመሆን ያለፈ ብዙም ትርጉም አልነበረውም። በትግርኛ መናገራቸውን አድንቄዋለሁ። መቀሌዎችም ከልባቸው ሲያጨበጭቡላቸው የነበረውም አንድም በአፋቸው ስላናገሯቸው ነው። የቋንቋ ሃያልነቱም ይሄው ነው። ዋናው ጉዳይ ከሆነውና ካደረጉት በላይ በዚህን ወቅት ምን ሊያደርጉ ይችሉ ነበር? የሚለው ነው።
በእርግጥ በመጡበት መንገድ አላገኘኋቸውም፡፡ ባስለመዱን የንግግር ቅኝት ከጆሮዬ አልገቡም። ይልቅስ ከመለስና ከሃይለማርያም ንግግሮች የተጣቀሱ፡ እርስ በእርስ በሚጋጩ አስተሳሰቦችና አቋሞች የተሞሉ፡ ግማሽ እውነት፡ ከፊል ሽንገላ የሞላበት፡ ከምናውቃቸው ጥልቅ አስተሳሰብ ወጥተው እንደአንድ ተራ የኢህአዴግ አመራር ባዶ የቃላት ጋጋታ ያጠላበት ንግግር ነው የሰማሁት። በእነዚያ ቃለመጠይቆችና የመድረክ ንግግሮች የምናውቃቸው፡ በፓርላማው የሰማናቸው፡ አብይ መቀሌ ላይ ጠፍተውብኛል።
በወረቀት የሰፈረውና የተዘጋጁበት የ18 ደቂቃ ንግግር ነጭ ከጥቁር የተደባለቀበት፡ ሽንገላና እውነት የተፈራረቁበት፡ ሴጣንና መላዕክ የተጠሩበት፡ ግማሽ እውነት ከፊል ተረት ያጠላበት ነው ማለት ይቻላል። መለስ ዜናዊን ጨምሮ ኢትዮጵያን እንደሀገር የሚጠሉና ሀገር ያጠፉ ክፉ ሰዎችን ስም እየጠሩ ማወደሳቸው ግን የፖለቲካ ጨዋታ ሊሆን ይችላል ብለን ይቅር ብለናቸዋል። አጼ ሚኒሊክን ከአድዋ ጋር አንስተው ባወደሱበት አንደበታቸው፡ ከመንደሩ ርቆ ማየት ሳይችል ይህቺን አለም የተሰናበተውን መለስ ዜናዊን ማንቆለጳጰሳቸው ለጆሮ ይቀፋል። ይጋጫልም። በአንድ ሰው ውስጥ እንዚህ ሁለት ግለሰቦች እኩል ቦታ ካላቸው ችግር አለ ማለት ነው። በበዓለ ሲመታቸው አንድም ቦታ ስሙን ያልጠሩትን መለስ ዜናዊን መቀሌ ላይ ''ብጻይ መለስ'' እያሉ ማወደስ የእውነት አምነውበት ወይስ የህወሀትን አመራሮች ለማስደሰት? ፖለቲካ አስቀያሚነቱ እዚህ ላይ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የህወሀትን ሰማዕታት አወድሰዋል። ዘላለማዊ ክብርንም ተመኝተዋል። ከምንም በላይ የጎረበጠኝ ይህ ንግግራቸው ነው።መሰረታዊ ጥያቄ ላንሳ። ዶ/ር አብይ የኢህአዴግ አመራር እስከመሆናቸው እንድንዘነጋ ያደረገን የትኛው ተግባራቸው ነው? እስከአሁን በተግባር የተለካ ምን ሰርተው ነው ቀልባችን የወደዳቸው? ንግግር... ንግግር... ንግግር ነው። ጥልቅ አመለካከታቸው ነው። ስለኢትዮጵያ ያላቸው ፍጹም ያልተዛነፈ ስሜት ነው። በእርግጥ ከዚያ ያለፈ ስለጠቅላይ ሚኒስትሩ ምን አውቀን፡ በምን ለክተን ወደድናቸው? ታዲያ ብቸኛው ፍቅርን የሸመቱበት፡ ተወዳጅነትን ያገኙበት ንግግራቸው ሆኖ ሳለ እሱም እርስ በእርሱ ሲጋጭ፡ ሀሳባቸው ከቀደመው ጋር ሲላተም፡ ከእሳቸው ምን ቀረን ብንል - ማን ነው ጥፋተኛ የሚለን?
ለትግራይ ሰማዕታት አክብሮት መስጠቱ አይከፋም። አምነውበትም ይሁን ሳያምኑ፡ ተገፍተውም ይሁን ገፍተው በዚያ ጦርነት ህይወታቸውን ያጡ ክብር ይገባቸዋል። ሆኖም ሰማዕት የሆኑለትን ዓላማ ማወደስ ትልቅ ፋወል ነው። የሌላውን የሚመሩትን ህዝብ ማስቀየም ነው። የህወሀት ዓላማ የተቀደሰ አልነበረም። ኢትዮጵያን ለማጥፋት ተማምለው ጫካ የገቡና ባለፉት 40ዓመታት በበረሃና በቤተመንግስት የኢትዮጵያን አንድነት ሲገዘግዙ እድሜአቸውን የጨረሱና የሸበቱ ህወሀቶችን ቅዱስና የተባረኩ አድርጎ ከማሳየት የከፋ የኢትዮጵያን ህዝብ የሚያስቀየም፡የሚያበሳጭ ምን ይኖር ይሆን?
ዶ/ር አብይ ሁሉንም ማስደሰት አይችሉም። ሀርነት የምታወጣቸው እውነት ብቻ ናት። ሽንገላን የፖለቲካ መስመራቸው ቅኝት ማድረግ የለባቸውም። ህወሀቶችን ለማስደሰት የኢትዮጵያን ህዝብ ማስቀየም አይገባቸውም። ያ መቀሌ መሃል የቆመው ሀውልት ለኢትዮጵያ አንድነት፡ ዳር ድንበሯ እንዲከበር ደም አጥንታቸውን የከሰከሱ፡ በኤርትራ በረሃ፡ በትግራይ አፈር ውስጥ ተቀብረው የቀሩ የኢትዮጵያ ልጆችን ወቃሽ፡ ተሸናፊ አድርጎ የሚያሳይ ሀውልት ነው። ከቀድሞ መንግስት ጎን ተሰልፈው የሞቱ ኢትዮጵያውያን ስለኢትዮጵያ እንጂ ስለመንግስቱ ሃይለማርያም አለነበረም። የደርግ ጭቆና አንገሽግሾን ነው በረሃ የወረድነው የሚለው ተረት ተረት አይሰራም። ደርግ ገና ስልጣን ከመያዙ በረሃ የገቡ ሰዎች ጭቆናውን የት አይተውት እንደሆነ ለመጠየቅ እንወዳለን። ከህወሀት ማኒፌስቶ ላይ የተጻፈው የደርግ ጭቆና አይደለም። ህወሀት ደርግም ባይኖር በወቅቱ ሊኖር የሚችል የትኛውም የኢትዮጵያ መንግስት መውጋቱ የማይቀር ነው። ዓላማው የትግራይን ሪፑብሊክ ለመመስረት ነበርና።
እናም ዶ/ር አብይ በመቀሌ የመገንጠል አጀንዳ ቀርጾ፡ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን የማፈራርስ እኩይ ዓላማ ሰንቆ የኢትዮጵያ ጠላት ከሆኑ ሀገራት በሚሰጥ እርጥባንና የመሳሪያ ድጋፍ ወደ ቤተመንግስት የገሰገሰን ጸረ ኢትዮጵያ ድርጅት የሆነውን ህወሀትን ሲያወድሱ ትዝ ያለኝ ያ ታሪካዊ ንግግራቸው ነው። ካራማራ አፈር ውስጥ አጽሙ ስለተቀበረው የአማራ ልጅ የነገሩን፡ ከአድዋ አፈር ጋር ደም አጥንቱ ስለተቀላቀለው የኦሮሞ ጀግና ያወሱን፡ በመተማ ለኢትዮጵያን ነጻነት ሲል አንገቱን ለሰይፍ ስለሰጠው የትግራይ ንጉስ የተረኩልን አንድ በአንድ ከጆሮዬ ጓዳ አቃጨለ። እንዴት ይሆናል?
ዶ/ር አብይ ከመቀሌ ነዋሪዎች ጋር ያደረጉት ውይይት ላይ ሌላ ሰው መስለው ነው የቀረቡት። ሁሉን ነገር በቅንነት መመልከት የሚመርጡት ዶ/ር አብይ፡ የትኛውንም ሃይል በፍቅርና በአክብሮት በመጥራት ቀልብን የሚሰርቁት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፡ ችክ ካለውና ከጠነዛው የኢህአዴግ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ትርክት ወጥተው ሊበራል አስተሳሰብ ይዘው ብቅ ያሉት ኮሎኔል አብይ--በመቀሌው ስብሰባ ላይ ቅኝታቸውን ቀይረው፡የኢህአዲግነት ጭምላቸውን አጥልቀው፡ በአጭሩ መለስ ዜናዊን መስለው ሳያቸው በልቤ ያሳደርኩትን ተስፋ አዳመጥኩት። በእሳቸው አሻግሬ የተመለከትኩትን መልካም ጊዜ እንዳላጣ ሰጋሁ። ምነው ዶክተር?
ዶ/ር አብይ ወደ መቀሌ ከማምራታቸው በፊት በቤተመንግስት በነበረው የእራት ግብዣ ላይ ስለተፎካካሪ ፓርቲዎች የተናገሩትም ከቀደሙት የኢህአዴግ መሪዎች በቋንቋ እንጂ በስትራቴጂ የተለየ አልነበረም። አማራጭ አቅርቡ የሚለው የኢህ አዴግ ድርቅ ያለ አቋምን አንጸባርቀዋል። በ1997ቱ ምርጫ የኢህ አዴግ ተቃዋሚዎችን የማሳነስና በህዝብ ዘንድ ደካማ አድርጎ የማሳጣት አቅጣጫው አማራጭ እንደሌላቸው ደጋግሞ መግለጽ ነበር። ቅንጅት ዳጎስ ያለ፡ አዳዲስ ሀሳቦችን የሰነቀ፡ ሀገሪቱን በተሻለ አቅጣጫ የሚወስድ አማራጭ ይዞ ነበር። መለስ ዜናዊ የቅንጅትን መሪዎች በሙሉ እስር ቤት አስገብቶ፡ የቅንጅት ቢሮ እንዲሰበር አድርጎ በቅንጅት የተዘጋጀውን ሰነድ በመዝረፍ የራሳቸው አድርገው መጠቀማቸውውን በቅርበት ለምናውቅ የ ''አማራጭ አቅርቡ'' አንድ ዓይነት ዜማ ለምን ደጋግማ እንደምትሰማ እንረዳለን። ዶ/ር አብይ ይህንኑ ዜማ በቤተመንግስት ሲያቀነቅኑ ስሰማ ስለእሳቸው ጥያቄዎች ውስጤ መነሳት ጀምረዋል።
ወደ መቀሌ እንመለስ። የትግራይን ህዝብ ወርቅ ነው ብለዋል። በእሳት የተፈተነ ወርቅ መሆኑን ተናግረዋል። ከአቶ መለስ የ1985ቱ ንግግር ''እንኳን ከእናንተ ተፈጠርኩ።'' የሚለው ሲቀር ሌላውን ብለውታል። በእርግጥ መለስ ዜናዊ ሲናገረው ለሌላው ህዝብ ካለው ጥላቻ መሆኑ ይገባናል። ዶ/ር አብይን በዚያ ደረጃ መለካት ተገቢ አይደለም። ስለየትኛውም ህዝብ ጥላቻ እንደሌላቸው እንገነዘባለን። እንደመለስ ዜናዊ አንዱን ህዝብ ከላይ ሰቅለው ሌላውን ለመደፍጠጥ በለው የተናገሩት ነው ለማለት ፈጽሞ የሚቻል አይደለም። በመሰረቱ ወርቅ ብሎ አንድን አካል መግለጹ ችግር አይደለም። መለስ ዜናዊ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ እንዲህ ዓይነቱን አገላለጽ ችግር እንዲኖረው በማድረጉ እንጂ። እናምበአቶ መለስ ያ ንግግር ለተጎዳ ሌላው ኢትዮጵያዊ የዶ/ር አብይ መድገም ጥሩ ስሜት አይሰጥም። ቃል ከባድ ነው። በቃል የተነገረ መቼም አይጠፋም።
ዶ/ር አብይ በኦሮሚያ ክልል ስለታሰሩት የትግራይ ተወላጆች የተናገሩትም ጥያቄ የሚጭር ነው። የህግ የበላይነትን ለማስፈን የሰውዬውን ቁርጠኝነት አደጋ ውስጥ የሚከት ነው። ያለወንጀላቸው፡ በየእስር ቤቱ የሚማቅቁ፡ በህወሀት ገራፊዎች ስጋቸው የተተለተሉ ኢትዮጵያውያንን ነጻ እንዲወጡ ያደርጋሉ ተብለው ሲጠበቁ ህዝብን ለመጨረስ እጅ ከፍንጅ ተይዘው የታሰሩትን የህወሀት አባላትን ለትግራይ ህዝብ ስንል እንፈታቸዋለን ማለታቸው አስደንግጦኛል። ከህግ አንጻር ግዙፍ ስህተት ነው። የሚያስተላልፈው መልዕክትም አደገኛ ነው። የትግራይን ህዝብ ቁጣ ለማብረድ ይህን ያህል ርቀት መሄዳቸው ትዝብት ላይ የሚጥላቸው ነው።
ዲያስፖራውን የገልጹበት ንግግራቸው ስለወልቃይት ምን እንደሚያስቡ ፍንጭ የሰጡበት ነው ማለት የሚቻል ነው። ዲያስፖራውን መረጃ የሚያገኘው ከፌስ ቡክ ነው የሚለው ድምዳሜአችው ግልብ ነው። ምናልባት የህወሀቶችን ትርክት በመድገም ከጎናቸው የተቀመጡትን ዶ/ር ደብረጺዮንን ለማስደሰት ይሆናል። ዶ/ር አብይ ቅንነት ያጣሁባቸው፡ ሙልጭ ያለ የኢህአዴግ ካድሬ መስለው በቀረቡበት በዚህ ንግግራቸው የዲያስፖራውን የመረጃ ምንጭ ፌስቡክ ብቻ እንደሆነ ሲናገሩ የእሳቸው አንደበት ስለመሆኑ እስከመጠራጠር የሚያደርስ ነው። ዲያስፖራው እዛ ኢትዮጵያ ካለው ኢትዮጵያዊ በላይ ስለኢትዮጵያ የየዕለት ክስተት መረጃ እንዳለው አጥተውት አይደለም። ኢህአዴጋዊ ባህሪያቸው አሸንፎአቸው እንጂ። የሰሜን ጎንደር ህዝብ ጥያቄው ልማት ነው፡ ውሃ ነው፡ መብራት ነው የሚለው ደረቅ ትርክታቸውን የሰማ አንድ ወዳጄ የመቀሌ ውሃ ስትጠጣ የምትናገረው እንዲህ ነው ብሎኝ አረፈ። አጃኢብ ነው። የወልቃይት የማንነት ጥያቄ፡ የሰሜን ጎንደር ህዝብ የነጻነት ረሃብ በእርግጥ ከመቀሌ ቁጭ ብሎ በኢህ አዴግ መነጽር ለሚመለከት ላይገለጽለት ይችላል። ወይም እንደዚያ ማሰብና መቀበል አይፈልግም።
ባልተለመደ መልኩ፡ ነጋዴዎች ናቸው፡ ለእንጀራቸው ሲሉ ህዝብን ያጋጫሉ፡ ከሚለው አንስቶ አንዳንድ የተጠቀሟቸው ቃላትና ሀሳቦች የዶ/ሩን ስብዕና ዝቅ አድርገው የሚያሳዩ ናቸው። ይህ መሆኑ ዶ/ር አብይ ከህወሀት ተጽዕኖ ለመላቀቅ የመቻላቸውን ነገር አሳሳቢ ያደርገዋል። ህወሀቶች በቀጣይም ፈላጭ ቆራጭ እንዳይሆኑ በዶ/ር አብይ በኩል ተስፋ ላደረጉ ሚሊዮኖች የመጀመሪያው የአደጋ መብራት ብልጭ ያለባቸው ይመስላል።
ዶ/ር አብይ የምር ስልጣን እንዲኖራቸው ከሚመኙትና ከሚናፍቁት አንዱ ነኝ። የጫሩት ተስፋ ወደ እውነተኛ ለውጥ እንዲቀየር ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ብዬ አምናለሁ። ጊዜ ይሰጣቸው ከሚሉት ጋር ጸብ የለኝም። ነገር ግን እጃችንን አጣጥፈን ከእሳቸው ተአምር ለመጠብቅ ብቻ በሚል ጊዜ የምንሰጥ መሆኑ ላይ ግን ልዩነት አለኝ። ትግሉን እንዳያስተኙት እሰጋለሁ። ለትግሉ የተላኩ ህመም ማስታገሻ መድሃኒት እንደማይሆኑ ምን ዋስትና አለን? አንዳንድ ምልክቶችን እያሳዩን ከንግግራቸው ባለፈ ዋስትና የሚሆን ነገር እያደረጉ ለዋናው ስር ነቀል ለውጥ ጊዜ እንዲወስዱ ቢደረግ አንድ ነገር ነው። አንጋጦ መና መጠበቅ ላይ ያተኮረው አካሄዳችን ግን አደጋ አለውና እናስብበት።

No comments:

Post a Comment