Friday, April 13, 2018

በምዕራብ ጉጂ ዞን የተነሳውን ግጭት ተከትሎ ዜጎች እየተገደሉና እየተሰደዱ ነው

 (ኢሳት ዜና ሚያዝያ 05 ቀን 2010 ዓ/ም) የአካባቢው ነዋሪዎች እንደገለጹት በጉጂና በጌዲዮ ማህበረሰብ መካከል የተነዛውን ወሬ ተከትሎ በተፈጠረው ግጭት ከሁለቱም ወገን በርካታ ዜጎች ሳይገደሉ አልቀረም። በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ወደ ጌዲዮ ዞን፣ ቡሌ ሆራና ሌሎችም አካባባቢዎች እየተሰደዱ ነው። የግጭቱ መንስኤ በውል ባይታወቅም ኢሳት ያነጋገራቸው ሰዎች እንደሚሉት በጉጂ ዞን ቀርጫ ወረዳ ውስጥ የሚኖሩ የጌዲዮ ተወላጆች አካባቢው ወደ ደቡብ ክልል እንዲካለል ሊጠይቁ ነው የሚል ወሬ በመነዛቱ በኦሮምያ ክልል ስር የሚገኙ ጉጂዎችን በማሰቆጣቱ የተጀመረ ግጭት ነው። በጌዲዮ በኩል ደግሞ ጉጂዎችን ሊጨርሱዋችሁ ነው የሚል ወሬ እንዲሰራጭ በመደረጉ ግጭት እንዲፈጠር ተደርጓል ሲሉ ነዋሪዎች ይናገራሉ። ሌሎች ደግሞ በጉጂ ዞን የሚኖሩ የጌዲዮ ተወላጆች በቋንቋችን እንማር የሚል ጥያቄ
በማቅረባቸው የተፈጠረ ግጭት መሆኑን ይናገራሉ። ግጭቱ በባንቆ ዳላቱ፣ ባንቆ ባያ፣ ባንቆ ሚጪጫ፣ ባንቆ ጨልጨሌ ፣ ሃሎ ባሪቲ፣ ቀርጫ፣ ጋሌሳ ነጌሶ፣ ጋሌሳ ዲዲሳ እና ሌሎችም ቀበሌዎች እየተካሄደ ነው። በግጭቱ ምክንያት የትራንስፖርት አገልግሎትም ተቋርጧል። በአሁኑ ሰኣት መከላከያ ሰራዊት ወደ አካባቢው ተሰማርቷል። በ1987 እና 92 ዓም ተመሳሳይ ግጭት ተክስቶ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወታቸው አልፏል። ኢህአዴግ አገሪቷን እስከተቆጣጠረበት ጊዜ ድረስ ጉጂና ጌዲዮ በፍቅር አብረው ይኖሩ የነበሩ ብሄረሰቦች ናቸው። በሁለቱ ብሄረሰቦች መካከል አብረው ተጋብተው የሚኖሩ፣ ታናሽና ታካቋ ተብለው የሚቆጣጠሩ እንደነበሩ፣ ከ1983 ዓ.ም በሁዋላ በተፈጠረው የብሄር ፖለቲካ አስተሳሰብ ግጭቶች እየተከሱ መምጣታቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ።

No comments:

Post a Comment