ከድንበር ማካለል ጋር በተያያዘ ከሃምሌ ወር ጀምሮ በኦሮምያና ደቡብ ክልሎች የድንበር ከተሞች መካከል የተነሳው ግጭት እስካሁን አለመቆሙን ነዋሪዎች ገልጸዋል።
የአካባቢው ባለስልጣናት የሁለቱን አካባቢዎች ድንበር ለመለየት በሄዱበት ወቅት የተፈጠረው ግጭት 100 ሺ የሚሆኑ ዜጎችን ያፈናቀለ ሲሆን፣ ግጭቱን ለመቆጣጠር በሚል የፌደራል ፖሊስ በስፍራው ተሰማርቶ መጠነኛ ሰላም አውርዶ ነበር። ይሁን እንጅ ግጭቱ እንደገና በማገርሸቱ አሁንም ሰዎች እየተገደሉ ነው። ባለፉት ሶስት ቀናት በአማሮ ወረዳ 3 የኮሬ ብሄረሰብ አባላት ሲቆስሉ፣ አንድ የቡርጂ ብሄረሰብ ተወላጅም ተገድሏል። በጉጂ ብሄረሰብ በኩልም 3 ሰዎች መገደላቸውን ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
የተፈናቀሉ ሰዎች አሁንም ወደ ቦታቸው ባለመመለሳቸው ለከፍተኛ ስቃይ ተዳርገዋል። ከአማሮ ዲላ የሚወስደው መንገድ እንደተከፈተ ተገልጾ የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች እንዲሄዱ ከተገደዱ በሁዋላ ከፍተኛ ተኩስ ተከፍቶባቸዋል። ከቡርጂ ቡሌ ሆራ የሚወስደው መንገድ አሁንም ዝግ እንደሆነ ነው።
የሁለቱም ክልል ነዋሪዎች ወደ ድንበር ማካለል አንገባም የሚል አቋም በመያዙና ችግሩን ራሳችን እንፈታዋልን የሚል አቋም በመያዛቸው የአካባቢው ካድሬዎች ህዝቡን ስብሰባ በመጥራት የድንበር ማካለል እንዲኖር ለማሳመን እየተንቀሳቀሱ ነው።
(ኢሳት ዜና መስከረም 28 ቀን 2010 ዓም)
No comments:
Post a Comment