(ኢሳት ዜና–ጥቅምት 6/2010)የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለተከሳሾች የአቃቤ ህግ ምስክሮች ስም ዝርዝር ሊደርሳቸው ይገባል በሚል የነ ዶክተር መረራ ጉዲና ጠበቆች ያቀረቡትን ጥያቄ ውድቅ አደረገ። ከጥቅምት 23 ጀምሮም የአቃቤ ህግ ምስክሮች መደመጥ እንደሚጀምሩ ታውቋል። የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ሰኔ 30 2009 በዋለው ችሎት ላይ የእነ ዶክተር መረራ ጉዲና ጠበቆች የአቃቢ ህግ ምስክሮች ስም ዝርዝር ለተከሳሾች ሊደርሳቸው እንደሚገባ ጥያቄ አቅርበው ነበር። ይህንን ጥያቄ ተከትሎ ፍርድ ቤቱ ለተከሳሾቹ የምስክሮች ስም ዝርዝር ሊደርሳቸው ይገባል አይገባም የሚለውን ለመወሰን የህገ መንግስት ትርጉም ለሚሰጥበት የፌዴሬሽን ምክር ቤት መላኩን ተከትሎ የምክር ቤቱ ውሳኔ በዛሬው ችሎት ተደምጧል። የፌዴሬሽን ምክርቤት ለፍርድ ቤቱ በላከው ውሳኔ መሰረት የምስክሮችን ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል ስም ዝርዝራቸው ለተከሳሾች እንዲደርስ አለመደረጉ ከህገመንግስቱ ጋር እንደማይጋጭ አስታውቋል። ይህን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ተከትሎ የከፍተኛው ፍርድቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት የእነ ዶክተር መረራ ጉዲና የፍርድ ሂደት የምስክሮች ዝርዝር ሳይገለጽ እንዲቀጥል ወስኗል። ከጥቅምት 24/2010 ጀምሮ ምስክሮችን ለማዳመጥም ቀጠሮ ይዟል። በእለቱ የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ የተጠየቁት ዶክተር መረራ ጉዲና የተጠቀሰውን ወንጀል አልፈጸምኩም፣ጥፋተኛም አይደለሁም ብለዋል። የዶክተር መረራ ጉዲና ጠበቆች በበኩላቸው በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔም ሆነ ይህን ተከትሎ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ብይን ላይ ይግባኝ እንደሚጠይቁ ተናግረዋል። ህገ መንግስቱን እንዲተረጉም የዳኝነት ስልጣን የተሰጠው የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሁሉም ክልል ፕሬዝዳንቶችን፣የተመረጡ የክልል ምክር ቤት አባላቶችንና ሌሎች አስፈጻሚ አካላትን የያዘ የፖለቲካ ሃይል መሆኑ የሚታወቅ ነው።
No comments:
Post a Comment