በባህርዳር፣ ጎንደርና ሌሎችም በርካታ የሰሜንና ደቡብ፣ የምእራብና ምስራቅ ጎጃም ከተሞች የነበረውን ህዝባዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ተከትሎ ፣ በርካታ የክልሉ ልዩ ሃይል አባላት ከህዝብ ጎን ቆመዋል በሚል ልዩ ሃይሉን በፌደራል ደረጃ አዋቅሮ የእዝ ሰንሰለቱም በህወሃት እንዲመራ የሚደረገው ጥረት በልዬ ሃይል አባላት ተቃውሞ አጋጥሞታል። ሰሞኑን ልዩ ሃይሉ ከክልል እዝ ወጥቶ በፌደራል ደረጃ መዋቀር ይገባዋል የሚል አጀንዳ በጥንቃቄ ለተመረጡ የልዩ ሃይል አዛዦች ለውይይት የቀረበ ቢሆንም፣ ተሰብሳቢዎቹ ግን “ እኛ ከአማራ ፖሊስ ውስጥ ተመልምለን ወደ ልዩ ሃይል ስንገባ የተነገረን በክልሉ ልዩ ሃይል ውስጥ እንድንሰራ ተነግሮን ነው። አሁን በፌደራል ደረጃ ይዋቀር የሚለው ነገር እኛን አይመለከተንም። የስራ ውል የያዝነው ከክልሉ ፖሊስ ጋር በመሆኑ እቅዱን ለመቀበል ፈቃደኞች አይደለንም” የሚል መልስ በአንድ ድምጽ ሰጥተዋል።
በ2008 ዓም በነበረው ህዝባዊ የለውጥ እንቅስቃሴ የልዩ ሃይል አባላት ከህዝብ ጎን በመሰለፍ በህወሃት ደጋፊዎች ላይ ጥቃት እንዲደርስ አድርገዋል በማለት ህወሃት ክስ ሲያሰማ ቆይቷል። የህወሃቱ ዶ/ር አዲሱ ገብረእግዚአብሄር የሚመሩት የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን የሚባለው የአገዛዙ ተቋምም እንዲሁ በልዩ ሃይሉ ላይ ወቀሳ አቅርቦ ነበር።
በክልሉ ውስጥ እስከ 8 ሺ የሚደርሱ የ ሃይል አባላት እንዳሉ ይገመታል። ልዩ ሃይሉ ተጠሪነቱ ለክልሉ መንግስት ነው። ህወሃት በ አስቸኳይ አዋጅ እና በግምገማ ስም የልዩ ሃይሉን ለማዳከም ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። የአሁኑ እቅድ ልዩ ሃይሉን ህወሃት በሚመራው የፌደራል ፖሊስ አወቃቀር ስር በማስገባት በቀጥታ ለመቆጣጠር እንዲሁም የመከላከያ ሰራዊት በክልሉ ህዝብ ላይ ሲፈጽም የነበረውን ግድያና የአፈና ዘመቻ አብዛኞቹ የልዩ ሃይሉ አባላት ሲቃወሙት በመቆየታቸው ተመሳሳይ ተቃውሞ እንዳይነሳ ለማኮላሸት ታስቦ የተደረገ መሆኑን ምንጮች ለኢሳት ገልጸዋል። (ኢሳት ዜና–መስከረም 30/2010)
No comments:
Post a Comment