Friday, October 6, 2017

)በኢትዮጵያ ባለፉት 26 አመታት የተተገበረው የብሔር ተኮር ፖለቲካ ፈተና እየገጠመው መሆኑን ታዋቂው የአለም አቀፍ መጽሔት ዘ ኢኮኖሚስት ዘገበ።

(ኢሳት ዜና–መስከረም 26/2010)በኢትዮጵያ ባለፉት 26 አመታት የተተገበረው የብሔር ተኮር ፖለቲካ ፈተና እየገጠመው መሆኑን ታዋቂው የአለም አቀፍ መጽሔት ዘ ኢኮኖሚስት ዘገበ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ እየተስፋፋ የመጣውን የብሔር ግጭት የዳሰሰው ዘኢኮኖሚስት የክልል መንግስታት በፌደራል መንግስት ቁጥጥር የሚደረግባቸው ቢሆንም ከእጅ እያመለጡ ናቸው ብሏል። እናም የሕዝቡን አንድነት በማዳከም የጎሳ ፖለቲካን ሲያራምድ የቆየው የኢትዮጵያው አገዛዝ የማይወጣው ችግር ውስጥ እያስገባው መሆኑን ዘ ኢኮኖሚስት በሀተታው ዘርዝሯል። የዘ ኢኮኖሚስት ዘገባ በቅርቡ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች መካከል የተከሰተውን ደም አፋሳሽ ግጭት መነሻ አድርጎ በኢትዮጵያ ያለው የጎሳ ፖለቲካ ፈተና እየገጠመው መሆኑን ዘግቧል። የሀረር ከተማ የአንድነት መገለጫ እንደነበረች ያወሳው ዘ ኢኮኖሚስት የከፊል የራስገዝ አስተዳደር ቢኖራትም በአብዛኛው የኦሮሞና የአማራ ተወላጆች እንደሚኖሩባትም ነው የገለጸው። በቁጥራቸው ትንሽ የሆኑት ሀረሪዎች ሌሎችም በብዛት የሚኖሩባትን የሀረሪ ክልል እንደሚያስተዳድሩና ይህም ችግር ሲፈጥር መቆየቱንም መጽሔቱ አስታውሷል። ዋናው ችግር ግን ይላል ዘኢኮኖሚስት ሰፊ ድንበር በሚጋሩት በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ መካከል የተፈጠረው ግጭት ከ70 ሺ በላይ እንዲፈናቀሉና በመቶዎች ደግሞ በግፍ እንዲገደሉ ማድረጉ ነው። እነዚህ ተፈናቃዮች ደግሞ ሐረር ከተማን ማጨናነቃቸውን ዘገባው ጠቅሶ የኢትዮጵያ በቋንቋ ላይ የተመሰረተ ፌደራሊዝም ባመጣው ጣጣ አካባቢው እየተመሰቃቀለ መሆኑን ዘ ኢኮኖሚስት ዘግቧል። ከተለያዩ ብሔሮች የተደበላለቁትን ጨምሮ ማንም ሰው በመታወቂያው ብሔሩን እንዲገልጽ መገደድም ለእርስ በርሱ መገዳደልና ለግጭቱ መባባስ ሰበብ ሆኗል ነው ያለው። ዘ ኢኮኖሚስት እንደገለጸው በሕወሃት የሚመራው አገዛዝ ብሔሮችን በመከፋፈል በእጅ አዙር ግን ክልሎችን ሲቆጣጠር ቆይቷል። አሁን ግን ክልላዊ መንግስታት እየጠነከሩና ከአገዛዙ ቁጥጥር ውጪ እየሆኑ መሄዳቸውን መጽሔቱ በሀተታው አመልክቷል። እንደ ዘ ኢኮኖሚስት ዘገባ ክልላዊ መንግስታት ዋነኛ አጀንዳቸው የብሔራቸውን ጥቅም ብቻ ማስጠበቅ ነው። ለዚሁም የኦሮሚያ ክልላዊ አስተዳደር በአዲስ አበባ ልዩ ጥቅም መጠየቁንም ለአብነት አንስቷል። በሶማሌ ያለው አስተዳደርም ልዩ ፖሊስ በማቋቋም እየፈጸመ ያለው የሰብአዊ መብት ረገጣና የመስፋፋት ሕልም በክልሉ ፕሬዝዳንት አብዲ መሀመድ ጊሌ የሚዘወር መሆኑን መጽሔቱ ዘርዝሯል። እናም በሕወሃት የሚመራው የፌደራሉ አገዛዝ በእንዲህ አይነት ምስቅልቅሎች ውጥረት ውስጥ መግባቱንና ሁኔታውን መቆጣጠር አለመቻሉን ዘኢኮኖሚስት በዘገባው አስፍሯል። በቋንቋ ላይ የተመሰረተው ፌደራሊዝም ሕወሃት ስልጣን ላይ ከወጣ በኋላ ተግባራዊ ሲደረግ የኢትዮጵያ ችግር ብቸኛ መፍትሄ ሆኖ ይቆጠር ነበር። አሁን ግን ይላል ዘ ኢኮኖሚስት የግጭትና የአለመተማመን እንዲሁም የአመጽ መንስኤ እየሆነ መምጣቱን እየተመለከትን ነው ብሏል። ክሪስቶፎር ቫን ዳር ቤከን የተባሉ የሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ ፕሮፌሰርን ጠቅሶ ዘኢኮኖሚስት እንዳለው የሕዝቡን አንድነት በመሸርሸር እውን የተደረገው ብሔር ተኮር ፖለቲካ በመጨረሻ ችግር እየፈጠረ ይገኛል። እናም አሁን አንድነትን ለመመለስ የሚደረገውን ሙከራ ፈታኝ አድርጎታል ማለታቸውን ዘ ኢኮኖሚስት ዘግቧል።

No comments:

Post a Comment