በሰሜን ወሎ ሰልጣኝ የመከላከያ ሰራዊት አባላትን ለመመልመል የሚደረገው ሙከራ አለመሳካቱን ተከትሎ ፣ ካደሬዎችና ደላሎች ቤት ለቤት እየዞሩና በየገበያ ቦታዎች እየተገኙ የመከላከያ አባል ለሚሆኑት መንግስት 3 ሺ ብር እንደሚከፍል ሲቀሰቅሱ ሰንብተው የተወሰኑ ወጣቶችን ለማስመዝገብ ችለው ነበር። ይሁን እንጅ ህብረተሰቡ የተመዘገቡ ወጣቶችን ፈልጎ በማግኘት “ ማንም ልትወጉ ነው ፣ የጎንደር ወንድሞቻችሁን ነው ወይስ ግብር በዝቶብናል ብሎ የሚጨኸውን ነጋዴ ለማፈን” የሚሉ ጥያቄዎችንና ምክሮችን በማቅረብ፣ ወጣቶች ሃሳባቸውን እንዲቀይሩ ለማድረግ መቻሉን የገለጸው ወኪላችን፣ ወጣቶቹ ወደ ሚሊሺያ ጽ/ቤት በመሄድ “ ሃሳባቸውን መቀየራቸውንና ለመሄድ እንደማይፈልጉ” ተናግረዋል። የሚሊሺያ ጽ/ቤት አባላት በበኩላቸው መንግስትን አታላችሁዋል በማለት ለማስፈራራት ሙከራ ቢያደርጉም ወጣቶቹ ግን “ አንሄድም” በሚለው አቋማቸው በመጽናት ተበትነዋል። ትናንት እሁድ የዞን ሚሊሺያ ጽ/ቤት ፣ የዞኑ ፖሊስና የጉባ ላፍቶ ወረዳ ፖሊስ በጋራ ሆነው በእያቅጣጫው በመዞር 17 የሚሆኑ ተዘምግበው አንሄድም ያሉ ወጣቶችን በመያዝ ጎንደር በር ፖሊስ ጣቢያ ወስደው አስረዋቸዋል።
የታሰሩት ወጣቶች ግን “ በጭራሽ አንሄድም” የሚል መልእክት ለቤተሰቦቻቸው መላካቸውን ወኪላችን ገልጿል።
በተለያዩ አካባቢዎች አዳዲስ ወታደሮችን ለመቅጠር የተደረገው ሙከራ መክሸፉን ተከትሎ፣ ወጣቶችን በደላላ ማፈላለግ መጀመሩን ኢሳት በቅርቡ መዘገቡ ይታወቃል።
(ኢሳት ዜና መስከረም 28 ቀን 2010 ዓም)
No comments:
Post a Comment