ከአንድ ዓመት በፊት በርካታ እስረኞች በግፍ ባለቁበት የቂሊንጦ እስር ቤት ቃጠሎ ወቅት በእስር ቤቱ አድማ አስነስታችኋል፣ ለማምለጥ ሙከራ ድርጋችኋል ተብለው ክስ ከቀረበባቸው እስረኞች ውስጥ ሁለት ታራሚዎች በአሰቃቂ ሁኔታ በደረሰባቸው ድብደባ መገደላቸው ተዘግቧል። ግድያው ሲፈጸም በስፍራው የተመለከቱ እስረኞች ጥቅምት 15 ቀን 2010 ዓ.ም ለፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ ወንጀል ችሎት በቀረቡበት ወቅት የዓይን እማኝነታቸውን ለችሎቱ ተናግረዋል።
በእነ ብስራት ብርሃኑ የክስ መዝገብ 15ኛ ተከሳሽ የሆኑት አቶ አለማዬ ዋቄ ማሞ ቂሊንጦ እስር ቤት ውስጥ በደረሰበት ድብደባ ሕይወቱ ማለፉን 1ኛ ተከሳሽ የሆኑት አቶ ብስራት ብርሃኑ ለፍርድ ቤቱ እማኝነታቸውን ሰጥተዋል።
አቶ ብስራት አበራ ሁኔታውን ሲገልጹ ''የእስር ቤቱ ኃላፊ የሆኑት ሱፐር ኢንተንደንት አሰፋ ኪዳነ አጠገባችን እያለ ነው ሁላችንም ላይ ድብደባው የተፈጸመብን። አቶ አለማዬ ዋቄን ፊቴ ላይ እያየሁ ነው ልቡን ረግጠው የገደሉት።'' ሲሉ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል። ከአቶ አለማዬ ዋቄ በተጨማሪ መሀመድ ጫኔ ገበየሁ የተባሉ እስረኛም በድብደባ ብዛት ህይወቱ እንዳለፈ እስረኞቹ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል።
ሟች አለማዬ ዋቄ ከአሁን ቀደምም በተደጋጋሚ ለችሎቱ መደብደቡን በመግለፅ አቤቱታ ማቅረቡን እስረኞቹ ለፍርድ ቤቱ አስታውሰዋል። የጳውሎስ ሚሊኒዬም ሆስፒታል የአለማዬ ዋቄን አሟሟት የሚገልፅ 6 ገፅ የምርመራ ውጤት ለፍርድ ቤቱ ልኳል። የምርመራ ሪፖርቱ ግን "እንደማንኛውም ሰው ኢንፌክሽን ነበረበት" በማለት ከመግለጽ ውጪ ቀሪውን ዝርዝር የምርመራ ውጤት ፍርድ ቤቱ ሳይገልጸው አልፎታል።
"ባለፈው ፍርድ ቤት ከዚህ ማረሚያ ቤት አስወጡኝ። ይገድሉኛል ብሎ ተናግሮ ነበር። ሁላችንም አደጋ ላይ ነን። የት እንሂድ? ገዳዮች እጅ ነው ያለነው። እኔ ተመልሼ ወደ ቂሊንጦ አልሄድም። ይገድሉኛል። እዚሁ በጥይት ይግደሉኝ። " በማለት ለህይወቱ መስጋቱን በመግለፅ አቶ ብስራት አበራ ከችሎት አልወጣም ብሎ ነበር።
ሁሉም እስር ቤቶች ስቃይ የሚፈፀምባቸው ቢሆኑም ለህይወቱ ሲል ከቂሊንጦ ወደ ማዕከላዊም ወይም ወደ ቃሊቲ ቢዛወር እንደሚመርጥ ለፍርድ ቤቱ አረድቷል። ፍርድ ቤቱ ግን ከቂሊንጦ ወደ ሌላ እስር ቤት እንዲቀየር ትዕዛዝ እንደማይሰጥ አስታውቋል።
ከተከሳሾቹ አንዱ "ዛሬም የተናገርኩት በህይወቴ ፈርጄ ነው። ጓደኞቼን እንደገደሏቸው ይገድሉኛል። አልሄድም!" ብሎ ችሎት ውስጥ የቆየ ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱ "ምንም ልናደርግ አንችልም" ስላለው ከቆይታ በኋላ ከችሎት ወጥቷል። ሆኖም ችሎቱ በር ላይ ፖሊሶች እጁን ከሚገባው በላይ አጥብቀው በማሰር ስለዛቱበት ወደ ችሎቱ ተመልሶ በመግባት እጁን ለፍርድ ቤት በማሳየት እንደዛቱበት እና ያቀረበው አቤቱታ ተጨባጭ ስለመሆኑ ችሎቱ በር ላይ የተፈፀመውን ድርጊት ቢያስረዳም ፍርድ ቤቱ ላቀረበው አቤቱታ ምንም ዓይነት እርምጃ ሊወስድ አልቻለም። በእስር ቤቱ ጠባቂዎች የደረሰበትን ሰቆቃ አስመልክቶ ከችሎት ውጭ ለነበረው ህዝብ ህይወቱ አደጋ ላይ መሆኑን እና የህልውና አደጋ እንዳዣበበት ድምፁን ከፍ አድርጎ አሰምቷል።
በእነ ብስራት አበራ የክስ መዝገብ የተከሰሱት ተከሳሾች ለምርመራ ሸዋ ሮቢት እስር ቤት ተወስደው ሰቆቃ እንደተፈጸመባቸው እና ቂሊንጦ እስር ቤትም ተመሳሳይ በደል እየደረሰባቸው እንደሚገኝ ለፍርድ ቤት አቤቱታቸውን አቅርበዋል። ፍርድ ቤቱም የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን እንዲያጣራ ባዘዘው መሰረት ኮሚሽኑ ቂሊንጦ ሄዶ እስረኞቹን ቢያነጋግርም የምርመራ ውጤቱን አላቀረበም። የኮሚሽኑን የምርመራ ውጤት ለመስማት ፍርድ ቤቱ ተደጋጋሚ ቀጠሮ ቢይዝም ኮሚሽኑ ምርመራውን አለማቅረቡን ገልፆ ለህዳር 4 ቀን 2010 ዓ.ም ምርመራውን ለምን እንዳላቀረበ በችሎት እንዲያስረዳ ሲል ትዕዛዝ መስጠቱን ችሎቱን ተከታትሎ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው በፌስቡክ ገጹ ላይ አስነብቧል።
"ከአሁን ቀደምም መሃመድ ጫኔን ገድለዋል። አሁን አለማየሁን ገድለዋል። ሁላችንም ዋስትና የለንም። በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እያለን እንኳን ከዚሁ ሁሉ እስረኛ ውስጥ በአንድ እስረኛ ላይ እንኳ አትፈርዱም። ቀድመው ገድለው ይጨርሱናል። በሚቀጥለው ቀጠሮ ደግሞ የእኔን የሞት ዜና ልትሰሙ ትችላላችሁ" በማለት እስረኛው አቤቱታውን አሰምቷል።
ባለፉትው አራት ወራት ውስጥ ብቻ አየለ በየነ፣ መሃመድ ጫኔ እና አለማዬ ዋቄ እስር ቤት ውስጥ በደረሰባቸው ድብደባ በግፍ ተገለዋል። አቶ አግባው ሰጠኝ፣ አቶ ዘመነ ጌጤና አቶ ለገሰ ወ/ሃና በተደጋጋሚ በተፈጸመባቸው ኢሰብአዊ ድብደባ ምክንያት ጤናቸው መታወኩ ተዘግቧል።
No comments:
Post a Comment