Thursday, October 12, 2017

በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩና ሁሉን አቀፍ አስተዳደር እንዲኖር ግፊት የሚያደርገው ኤች አር 128 በኮንግረስ ድምጽ እንዳይሰጥበት ያዘገየው በአሜሪካ ምክር ቤት የመከላከያ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መሆኑ ተጠቆመ።

(ኢሳት ዜና –ጥቅምት 2/2010) በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩና ሁሉን አቀፍ አስተዳደር እንዲኖር ግፊት የሚያደርገው ኤች አር 128 በኮንግረስ ድምጽ እንዳይሰጥበት ያዘገየው በአሜሪካ ምክር ቤት የመከላከያ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መሆኑ ተጠቆመ። የቋሚ ኮሚቴው ስብሳቢ ማክ ቶርንቨሪ በምክር ቤቱ አብላጫ ድምጽ ላለው ሪፐብሊካን ፓርቲ መሪ ኬቨን ማካርቲ በረቂቅ ሕጉ ላይ የ30 ቀን ጊዜ እንዲሰጣቸው በመጠየቃቸው የድምጽ አሰጣጥ ስነስርአቱ እንደዘገየ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተለው የኢትዮጵያ አድቮኬሲ ኔትዎርክ ስብሳቢ ዶክተር አርአያ አምሳሉ ገልጸዋል። እንደ ዶክተር አርአያ ገለጻ የመከላከያ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ኤች አር 128 እንዲዘገይ የፈለገው በኢትዮጵያ ያለው አገዛዝ ረቂቅ ሕጉ ከጸደቀ በጸረ ሽብር ጉዳይ ላይ ከአሜሪካ ጋር ያለውን ትብብር እንደሚያቆምበመግለጹ ነው። ይህም ቢሆን ግን በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አሁንም ወደ ኮንግረስ አባላት ስልክ በመደወል ረቂቅ ሕጉ እንዲጸድቅ ግፊታቸውን ይበልጥ እንዲያጠናክሩ ዶክተር አርአያ ጥሪ አቅርበዋል። ኤች አር 128
በኢትዮጵያ የተፈጸመው አጠቃላይ ግድያና እስር በገለልተኛ አካል ተጣርቶ በፈጻሚዎች ላይ ተጠያቂነት እንዲመጣ የሚያስገድድ የውሳኔ ሀሳብ ነው። በኮንግረስ ክሪስ ስሚዝ ስፖንሰር አድራጊነት የተረቀቀው ኤች አር 128 ከአሜሪካ የተወካዮች ምክር ቤት አባላት ከ66 በላይ የሚሆኑት ድጋፋቸውን ሰጥተውበታል። ረቂቅ የውሳኔ ሀሳቡም በምክር ቤቱ የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ በሙሉ ድምጽ ጸድቆ ከ4 መቶ በላይ አባላት ባሉት ኮንግረስ ሊጸድቅ ቀነ ቀጠሮ ከተያዘለት በኋላ ድንገት እንዲዘገይ ተደርጓል። ይህንኑ ረቂቅ ህግ እንዲጸድቅ በዋና ደጋፊነት ከሚያስተባብሩት መካከል ዋነኛው የኮሎራዶው ኮንግረስ ማን ማይክ ኮፍማን የድምጽ አሰጣጥ ስነስርአቱ የዘገየው በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሕጉ የሚጸድቅ ከሆነ በጸረ ሽብር ዘመቻው ካሁን በኋላ አንተባበርም ሲሉ በመዛታቸው መሆኑን ከዚህ ቀደም ገልጸው ነበር። ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለና ሕጉ እንዲጸድቅ ዘመቻውን እያስተባበረ ያለው የኢትዮጵያ አድቮኬሲ ኔትወርክ ሰብሳቢ ዶክተር አርአያ አምሳሉ በበኩላቸው በአሜሪካ ምክር ቤት የመከላከያ ቋሚ ኮሚቴ ሊቀመንበር ማክ ቶርንቨሪ የአምባሳደሩን ዛቻ መነሻ በማድረግ የ30 ቀን ጊዜ እንዲሰጣቸው መጠየቃቸውን ነው የተናገሩት። በኢትዮጵያ ያለው አገዛዝ ይህን ካደረገ በኋላ ረቂቅ ሕጉ እንዳይጸድቅ በውጭ ባሉ ደጋፊዎች አማካኝነት ተቃውሞ የሚል ዘመቻ መጀመሩንም ዶክተር አራአያ አምሳሉ ይናገራሉ። ይህም ደግፍ ከሚለው የኢትዮጵያውያን ዘመቻ በመኮረጅ እየተደረገ ያለ ተቃራኒ እንቅስቃሴ መሆኑን ነው የገለጹት። በሕወሃት ኢህአዴግ የሚመራው አገዛዝ ረቂቅ ሕጉ እንዳይጸድቅ እየተሯሯጠና ከፍተኛ ገንዘብ በማውጣት ወትዋቾችን እስከመቅጠር የደረሰው ኤች አር 128 በኢትዮጵያ ባለስልጣናት ላይ የጉዞ እቀባና የገንዘብ እገዳ እንዲጣል የሚጠይቅ አንቀጽ ስላለበት ነው ብለዋል። እናም ኢትዮጵያውያን ኤች አር 128 የተባለው ረቂቅ የውሳኔ ሀሳብ በኮንግረሱ ከጸደቀ በአገዛዙ ላይ ከፍተኛ በትር ስለሚያሳርፍ ግፊታቸውን አጠናክረው መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ዶክተር አርአያ አምሳሉ ጥሪ አቅርበዋል። እንደ ዶክተር አርአያ ገለጻ ኢትዮጵያውያን ምን ማድረግ እንዳለባቸው ለማወቅና በኮንግረስ አባላት ላይ የሚደረገውን ግፊት ለማጠናከር ኤች አር 128.org ከተባለው ድረ ገጽ መረጃውን ማግኘት ይችላሉ።

No comments:

Post a Comment