Wednesday, December 3, 2014

አሶሳ በከፍተኛ የመከላከያ ጥበቃ ስር መውደቁዋ ተሰማ፡፡


ኀዳር ፳፬(ሃያ አራት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-9ነኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል የሚያስተናግደው የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዝግጅት ማጠናቀቁን ቢገልጽም፣ በአካባቢው መንግስትን የሚቃወሙ ኃይሎች በተለያየ ጊዜያት በደፈጣ ውጊያ ጥቃት ማድረሳቸው ያሰጋው መንግስት በአካባቢው ከፍተና ወታደራዊ ሃይል አሰማርቷል።
ህዳር 29 ከሚካሄደውን በዓል ጋር ተያይዞ አደጋ ሊከሰት እንደሚችል ብዙዎች የሚሰጉ ሲሆን፣ ጥቂት የማይባሉ አመራሮች፣ ባለሃብቶችና ታዋቂ ሰዎች በተለያዪ ሰበቦች የጉዞ እቅዳቸውን የሰረዙ መሆኑ ታውቆአል፡፡
በቤንሻንጉል ክልል የተመሠረተው የአባይ ግድብ ጨምሮ በዋና ከተማዋ አሶሳ ከወትሮው በተለየ መልክ በኮንቮይ የታገዘ ከፍተኛ ጥበቃ እየተደረገ ሲሆን ለጸጥታ ሲባል እንደልብ መዘዋወር መከልከሉ ተሰምቷል፡፡
የፌዴሬሽን ምክርቤት የዘንድሮው በዓል የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሕገመንግስቱን ያጸደቁበትን 20ኛ ዓመት ጭምር የሚያከብሩበት ታሪካዊ ዕለት መሆኑን በመጥቀስ በተደጋጋሚ መግለጫ የሰጠ ሲሆን ይህንን በዓል ለማክበርም ከ2ሺ500 በላይ እንግዶች ወደስፍራው ይጓዛሉ ተብሎ ይጠበቅ እንደነበር ታውቆአል፡፡
ከተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የተውጣጣ ቡድን ነገ ሐሙስ ወደስፍራው የሚያቀና ሲሆን ከኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን (የቀድሞ ኢቲቪ) ብቻ ከ100 በላይ ጋዜጠኞችና ባለሙያዎች አሶሳ መግባታቸው ታውቆአል፡፡
በስተሰሜን ምዕራብ ሀገሪቱ ክፍል የሚገኝ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በአሁኑ ሰዓት የህዝብ ቁጥሩ 964 ሺ 647 ደርሷል፡፡ በክልሉ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ማለትም በርታ ፤ ጉሙዝ ፤ ሽናሻ ፤ ማኦ፣ ኮሞ ኦሮሞና አማራ የሚገኙ ሲሆን እነዚህ ብሔር ብሔረሰቦች ከዚህ ሥርዓት ቀጥተኛ ተጠቃሚ ካለመሆናቸውም በላይ መሬታቸው ለውጪ ባለሃብቶች ጭምር ያለፈቃዳቸው በገፍ የሚሰጥ በመሆኑ በጅምላ የመፈናቀል አደጋና በሰፈራ ስም ከቀዩአቸው እንዲሰደዱ በመደረጋቸው በሕዝቡ ውስጥ ከፍተኛ ቅሬታ መኖሩን ዘጋቢያችን ገልጻለች።


No comments:

Post a Comment