የዱሮ ወዳጄ ሰላምታዬ ይድረሽ። እንደምታውቂው ከተያየን ከሁለት አስርት አመታት በላይ ሆኗል። እኔም ካገሬ ከወጣሁ 21 ዓመት አለፈኝ። በጤናና በምቾት እንደምትኖሪ እሰማለሁ። እግዚአብሄርም መንግስትም ጥሩውን ነገር ሁሉ አብዝቶ እንዲሰጥሽ ምኞቴ ነው። አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጓደኝነት ከምቀርባቸውና ከማከብራቸው ስዎች ውስጥ አንቺ አንዷ እንደነበርሽ ራስሽምብዙ ሰዎችም ያውቃሉ። ከጊዜ ብዛትና በስልጣንም ርቀት ምክንያት ጓደኝነቴን ብትረሽውም አልፈርድብሽም። እኔ ግን ከሀገሬ ባለስልጣኖች አንዷ በመሆንሽ አልፎ አልፎም ቢሆን ስላንቺ የሚባለውን ከፉም ደግም እሰማለሁ። ብዙ ጊዜ ሰዎች ስላንቺ ክፉ ሲናግሩ ስሰማ የጓደኝነት ነገር እየሆነብኝ ደስ አይለኝም። ተሳክቶልኝ እንደሆን ባላውቅም ስላንቺ የማውቃቸውን በጎ ነገሮች በማንሳትም ልሟገት የሞከርኩበት ጊዜ ጥቂት አይደለም። ብዙ ሰዎች ያኔ 41 መምህራን ከዩኒቨርሲቲ ስንባረር አንቺን እንዳባራሪ እያዩሽ ለምን እንደማልጠላሽ ይገርማቸዋል። እስከዚህ ደቂቃ ድረስ ዉሳኔው ሲቀርብልሽ አትፈርሚም ብዬ ባልከራከርም አንቺ በኔ መባረር ላይ ትወስኛለሽ ብዬ አስቤ አላውቅም። አስተያየት እንድትሰጭ ብትጠየቂም በኔ ላይ ክፉ የምትናገሪም አይመስለኝም። መንግስታችን ላንቺ አይነት ሰዎች ትልቅ ወንበር እንጂ ትልቅ የውሳኔ ሰጭነት ስልጣን አብሮ እንደማይሰጥ እንደ ብዙ ሰው አውቃለሁ። ድሮ ጀምሮ ካንቺ ጋር ውቃቢያችሁ የማይዋደደው ወዳጄ ዶክተር መ
ረራ ጉዲና “ያቺ በተገናኛችሁ ቁጥር ስትሳሳሙ የማያችሁ ጓደኛህ መጨረሻ ላይ እኔን ትታ አንተን ነከሰችህ” እያለ ያሾፍብኛል። በቅርቡ የጻፈው መጽሀፍ ላይም ይህንኑ እንደቁም ነገር ጽፎታል። “ገነት እኔን አላባረረችኝም፣ እሷ እንዳላባረረችኝ ማስረጃዬ ያንተ አለመባረር ነው” እያልኩ መልሼ አሾፍበታለሁ። በዚያ የደርግ የመከራ ዘመን ብዙ ክፉ ነገር ያየሽ ሰው መሆንሽን እንዳወኩ በውስጤ ላንቺ ትልቅ የተቆርቋሪነት ስሜት ነበረኝ። እንደነገርኩሽ እኔ እድለኛም ሆኜ ከዚያ መአት ነፍሴ የተረፈች ሰው ብሆንም የምወዳቸው ደርግ የገደላቸው ጓደኞቼ ሀዘን የነበረብኝ ስው ስለነበርኩ ያን መከራ አቋርጠው ለተረፉ ሰዎች ሁሉ ስስ ልብ ነበረኝ። እንደጥንካሬ ተምሳሊትም (inspiration) እንድቆጥርሽና እንደ እህትም እንድቀርብሽ ያደረገኝ ያ ይመስለኛል።
ዛሬ ካለወትሮዬ ይህን ደብዳቤ የምጽፍልሽ ወድጄ አይደለም። እግዚአብሔር ይይልሽና የረሳሁትን ነገር ቀስቅሰሽ ሕሊና የሚነዝር ነገር ስለሰጠሽኝ ነው። በቅርቡ የሆኑ ወዳጆቼ ጉድህን ስማ ብለው ሸገር ኤፍ ኤም የሚባል ሬዲዮ ላይ የሰጠሽውን ቃለ ምልልስ የያዘ ክሊፕ ላኩልኝ። ረጅም ጊዜ ያልሰማሁትን ድምጽሽን ሳዳምጥ ቆይቼ ጋዜጠኛዋ ስለረሳሁት ስለ 41ችን ከአዲስ አበባ ዩኒበቨርሲቲ መባረር ጉዳይ አነሳችብሽ። እግዜር ይይላትና የተረሳ ነገር ብትተወውስ። እውነቱን ለመናገር አሁን እድሜሽም ብዙ ማይል ስለሄደ ለማሰላሰልም ጊዜ ስላገኘሽ የጸጸት አስተያየት የምትሰጭ መስሎኝ ነበር። በቃለ ምልልስሽ ላይ ስለተናገርሽው ሌላ ብዙ ዕውነት ያልሆነ ነገር እንኳን ብዙም አልተገረምኩም። እኛ ሀገር ውሸት ከስልጣን ፓኬጅ ጋር አብሮ የሚመጣ መሆኑን ስለማውቅ እሱ ብዙ አልደነቀኝም። ዕብሪት የተሞላበት ስድብና ዘለፋሽ ግን አሳዘነኝ። የተባረርነውን መምህራን ያንቺኑ ቃል ልጠቀምና ለማስተማር ፊት (fit) ስላላደረጉ (በአማርኛው ብቃት ስለጎደላቸው ለማለት ፈልገሽ መሰለኝ) ነው የተባረሩት ፥ የኮንትራት ሰራተኞች ስለሆኑ ኮንትራታቸው fit ስላላደረጉ ተቋረጠ፥ ቴኑር(tenure)ስለሌላቸው ነው፥ የተባረሩት 41 ብቻ እኮ ናቸው ያውም ካንድ ዩኒቨርሲቲ ፥ በዚህ የደረሰ ጉዳት የለም ፥ አሁን እኮ የማስተርሱ ብዛት ፣ የፒኤችዲው ብዛት ሕዝብ ይፈርደዋል፣ ተረረም ተረረም. . . .” የሚል ከቅብጥርጥርነቱ ይበልጥ ስድብነቱ የበዛ ነገር ውስጥ ለምን እንደገባሽ በጣም ነው የገረመኝ። አለቃሽ ሟቹ አቶ መለስ እንኳን ነፍሱን ይማረውና ከብዙ ጊዜ በኋላም ቢሆን በዚህ ጥያቄ ላይ የሰራው ስራ ስህተት መሆኑን መቀበሉን ሰምቼ ይቅርታ አድርጌለት ነው የሞተው። እናም ይህን የምጽፈው በፖለቲካ ልዩነት ተገፍቼ አይደለም። ነገርሽ ስለጓጎጠኝ ብቻ ነው። እዚህ ለስድብሽ የምሰጥሽን አስተያየት ላለቆችሽ አቅርበሽ የመንግስት ተቃዋሚ persecute አደረገኝ ብለሽ ለሰማዕትነት እንድትጠቀሚበት አይደለም። “ዮዲት ጉዲት” ተብሎ የወጣልሽን ስም በሿሚዎችሽ ዘንድ እንደሜዳልያ አንግባና እንደሰማዕትነት ተቆጥሮላት እንደ ጥገት ላም አለበችው እያሉ ብዙ ሰዎች ሲያሙሽ ሰምቻለሁ። የምናገረው ስለሀገር ፖለቲካ ሳይሆን ስለ ለከት የለሹ ስድብሽ ነው። ታስታውሽ እንደሆነ የተሾምሽ ሰሞን በርቺ እዚህ ትርምስ ወስጥ ጥሩ ድምጽ ልትሆኚ ትችያለሽ ብዬ አበረታትቼሽ ነበር። እኔ እንዴውም ያንን ማዕከላዊ የሚባለውን የቶርቸር ማዕከል አስፈርሰሽ ትምህርት ቤት ታስደርጊዋለሽ ብዬ አስቤም ነበር። ዛሬ ተሻሽሎ አገልግሎቱን መቀጠሉን እሰማለሁ። አንቺ ያየሽውን መከራ ሌላ ትውልድ እንዳያይ ክሩሴደር ሳትሆኚ ቀርተሽ የራስሽንም መስዋዕትነት ትርጉም ታሳጭዋለሽ ብዬ አላሰብኩም ነበር።
በዚህ ከመንደር ጥጋበኛ አፍ ብቻ ሊወጣ በሚችል ስድብሽ መገረሜን የነገርኳቸው ብዙ ሰዎች አድምጦ ከቁም ነገር የሚወስዳት ብዙ ሰው የለም ስላሉኝ ስቄ ልተወው አስቤ ነበር። ትንሽ ቆይቼ ግን ሁለት ነገሮች ከነከኑኝ። ይህን ደብዳቤ ለመጻፍም ምክንያቶቼ እነዚህ ሁለት ነገሮች ናቸው። አንደኛ ከተባረርናውና ይህን ዘለፋ ከምታወርጂብን 41ዳችን መሀል ሁለቱ በህይወት ስለሌሉ መልስ ሊሰጡሽ እንደማይችሉ ሳስብ ልቤ ብጅጉ ተነካ። እንደምታውቂው ፕሮፌሰር አስራትና ዶክተር መኮንን ቢሻው ዛሬ በህይወት የሉም። ሁለተኛው ምክንያቴ ደግሞ ልጆቼና የልጅ ልጆቼ ናቸው። እዚህ በስደት ሀገር የዘራኋቸውና ወደፊት የምዘራቸው ልጆቼ የልጅ ልጆቼና የነሱ ልጆች በብርቱ ሰራተኛነቱ የሚኮሩበት አባት እንጂ አንቺ እንዳልሽው ለመምህርነት fit ማድረግ ባለመቻሉ የተባረረና የተሰደደ ሰው አድርገው እንዳያዩኝ ፈራሁ። ደግሞስ ከኦባማ በኋላ ማን ያውቃል። እንዱ ወይም አንዷ የልጅ ልጄ ፕሬዚዳንትነት ወይም ሴናተርነት መወዳደር ይችሉና አባታችሁ አገሩ በመምህርነት ሥራ “fit” ማድረግ አቅቶት የተባረረ ሰው ነበረ ብለው አንቺን ጠቅሰው እንዳያሳፍሯቸው ሬከርዴን ማስተካከል አለብኝ ብዬ አሰብኩ። የትምህርት ሀላፊ (Educator in Chief) ከነበረች ሰው አንደበት የወጣ ስለሆነ እውነትነት ይኖረው ይሆን ወይ ብለው ቢያስቡና ቢሸማቀቁስ? የልጅ ልጆቼ ጠንካራና ታታሪ አያታቸው ስደት ሀገር ስራ-አጥ የሚል ፓስፖርት ይዞ መጥቶ ከምንም ተነስቶ የቆመ ፣ ከኛ አልፎ ለብዙ የተረፈ፣ ኢትዮጵያን እኛን ልጆቹንና ስራውን የሚወድ ታታሪ ነበር እያሉ እንዲኮሩ እፈልጋለሁ። ይህን ደብዳቤ የምጽፈው ለነሱም ውለታ ለመስራት ብዬ ነው። እኔና እንቺ በዚህ አስተሳሰብ ብዙ ልዩነት ሳይኖረን አይቀርም። አንቺ ልጆችሽና የልጅ ልጆችሽ “የጉዲት ልጆች” ወይም “የዚያች ድሀ ህዝብ ልጆች ላይ እንደ አይጥ ሙከራ ያካሄደች ሴትዮ ልጆች” እየተባሉ ጣት እየተቀሰረባቸው መኖራቸው ምንም ላይመስለሽ ይችል ይሆናል። እኔ ድግሞ ለራሴ ክብር ያለኝ ሰው ነኝ። እኔ ከሞትኩ በኋላ ሰርዶ አይብቀል ያለች አህያ ብቻ ነች እያሉ ያሳደጉ ቤተሰቦች ነበሩኝ።
እኔ በግሌ ከዚያ ዩኒቨርሲቲ መባረሬ በጅጉ ጠቀመኝ እንጂ አልጎዳኝም። የተሰደድኩ ሰሞን ኑሮ ትንሽ ቢያንገዳግደኝም አሁን የምወደውን ስራ እየሰራሁ እኖራለሁ። ያባረሩኝን ሰዎች እንደባለውለታ ነው የምቆጥራቸው። እንቃቸዋለሁ እንጂ አልጠላቸውም። በዓለም ላይ ትልቁ የጤና ምረምር ተቋም ውስጥ ነው የምሰራው። አንድ ኮሌጅ ውስጥም መምህር ነበርኩ። ከኛ በጅጉ በሚበልጠው የስደት ሀገሬ ውስጥ እንዳንቺ “fit” አታደርግም ብሎኝ የሚያውቅ የለም። ለነገሩ እዚህ አገር ሰው fit አታደርግም አይባልም። ቃሉን ለጫማ ፥ ለልብስና ለመለዋወጫ ዕቃ እንጂ ለሰው አይጠቀሙበትም። የመደዴ አነጋገር ነው። የምኖርበት ሀገር ከባለስልጣን እስከተራ ያገሬ ሰዎች በሎተሪ የሚመጡበት አሜሪካ ነው። መንግስታችሁ ሀብታም አደረኳቸው እያለ የሚኮራባቸው ብዙ ሰዎችም ሚስታቸው ስታረግዝ አሜሪካዊ ልጅ እንዲኖራቸው እዚህ እያመጡ ነው የሚያስወልዱት። ሀገሬ ሀብት ያላቸው ሰዎች እንኳን ለልጆቻቸው የማይመኟት ሀገር መሆኗ አንጀቴን ይበላኛል እንጂ ለኔስ አልከፋኝም።። ሟቹ መለስንም ሌሎቹንም እባራሪዎቼን እዚህ እግኝቻቸው አውቃለሁ። ሀገራችን ጦርነት ገባች ቢባል ሁሉንም ነገር ረስቼ ሰው እስኪገርመው ድረስ ዋሺንግተን ዋና ድጋፍ አስተባባሪ ነበርኩ። አባቶቻችን ከመንግስት ተቀያይመውም ጠላት ሲመጣ የራሳቸውን ስንቅ ይዘው ጦርሜዳ የሚሄዱበትን ወግ አድርሻለሁ። በጥላቻ አላየኋቸውም። እንቺንም ባገኝሽ ከድሮው ባልተናነሰ ክብርና ፍቅር አስተናግድሽ እንደሆን እንጂ የጥላቻ ስሜት አታገኝብኝም። ጥላቻ የበለጠ የሚጎዳው ጠዪውን መሆኑን አውቃለሁ።
ያሁኖቹ ሹዋሚዎችሽ ስልጣን ላይ ከመውጣታቸው በፊትና እንደወጡ ሰሞንም እኔና እንቺ ስለነሱ ብዙ አውርተን እናውቃለን። ካንቺ በበለጠ ለነሱ ገራገር አመለካከት የነበረኝ እኔ እንደነበርኩ የምትረሺ አይመስለኝም። ብዙዎቹን በተማሪነታችን ጊዜ እንደማውቃቸውና ዲሞክራሲያውያን ሊሆኑ እንደሚችሉ ስነግረሽ እንደነበር ታስታውሻለሽ። ሰለነሱ ቀና ነገር በተናገርኩ ቁጥር ሰውነትሽ እንዴት ይለዋወጥ እንደነበርም አስታውሳለሁ። አንድ ጊዜ እንዴውም ስለህወሀቶች እንደዚህ ማውራት ከቀጠልን ልጠላህ እችላለሁና እናቁም ብለሽ ማቆማችንንም የምታስታውሽ ይመስለኛል። እሁን ሰዎችን ትምክህተኛ እያልሽ ታሸማቅቂያለሽ ብለው ሰዎች ነግረውኝ የግርምት ሳቅ ስቄ ነበር። ይህን በዝርዝር ማውራት ከወዳጆችሽ ማቀያየም ይሆንብኛል እንጂ ስለህወሀቶች በተለይ ስለትግሬዎች ባጠቃላይ ከነበሩሽ እመለካከቶች ውስጥ ብዙ ነገሮች ጠቅሼ አስታውስሽ ነበር። ብዙዎቹን ቃል በቃል አስታውሳቸዋለሁ። ወደ ተራ ሰባቂነት መውረድ ስለማልፈልግ በዚሁ ይቅር። አንድ ጉብዝናሽን ግን አደንቃለሁ። ቢያንስ እኔን በዚህ በጣም ትበልጭኛለሽ። ስለወያኔዎች እንቺ በአወንታውም በአሉታውም በኩል ሁለት ጊዜ ልክ ሆንሽ። እኔ ሰዎች ሲመስሉኝ ላንቺ ጭራቅ ነበሩ ፥ ለኔ ክፋታቸው ሲገለጥልኝ ደግሞ ላንቺ መላዕክት ሆኑ። እንቺ ሁለት እኔ ዜሮ ወጣን ማለት ነው። በቡጢ ቋንቋ በዝረራ ነው ያሸነፍሽኝ። ይቺ ድንቅ ችሎታ ነች። ከሁሉ በላይ ደግሞ ከዚህ ሁሉ ጂምናስቲክ በኋላ ከህሊናሽ ጋር አብሮ የመኖር ችሎታሽ ሊደነቅልሽ ይገባል።
እስኪ ስለዋናው ስለተነሳሁበት ስላወረድሽብን ስድብ ጉዳይ እንነጋገር። ለመሆኑ እንዴት አይነት የኮሌጅ ኮንትራክት ነው እባክሽ ሴሚስተር መሀል በመጋቢት ወር መምህር fit አላደረገም ተብሎ ሲቋረጥ ያየሽው? አንቺ እንደምትዪው ተራ የኮንትራት ማቋረጥ ጉዳይ ከሆነ ታዲያ በዩኒቨርሲቲው ግቢ ዙሪያ እንዳንደርስ ለምን በወታደር ከለከላችሁን? ጎዳና ላይ እየተከተሉ ማስፈራራትንና ማዋከብንስ ምን አመጣው። ዩኒቨርሲቲ መምህር ቀጣሪም ኮንትራት ሰራዥም የሙያ ዲፓርትሜንቱ እንደነበረ ረስተሽው ነው ወይስ ሸገር ሬዲዮ የሚሰማው ሰው በሙሉ ደንቆሮ መሰሎሽ ነው? ለመሆኑ ኮንትራት የሚቋረጠው ቁራጭ ወረቀት አባዝቶ አንድ ቀን ጠዋት ተነስቶ ለሰራተኛው ያውልህ ብሎ አፍንጫ ላይ በመወርወር ነው? ትልቁ መመለስ ያለብሽ ጥያቄ ደግሞ ይህ ነው። እንዴው ለመሆኑ ማነው የት ቁጭ ብሎ የማስተማርና የምርምር ችሎታችንን የመዘነውና አንቺ እንዳልሽው fit አለማድረጋችንን ያረጋገጠው? ርግጠኛ ነኝ ለነዚህ ጥያቄዎች መልስ የለሽም። ነገሩ አፍ እንዳመጣ ለመናገር የሚገፋፋ የጥጋብ አነጋገር ነው ያልኩሽም ለዚህ ነው። መልስሽ ሁሉ የሚያደምጡሽን ሰዎች በመናቅ ላይ የተመሰረተ ነው።
አንዳንድ ጊዜ አፍ ሞልቶ ሌሎችን መሳደብ ቀርቶ ለመተቸት እንኳን ራስን ትንሽ ማየት ይጠይቃል። አንቺ ለሹመት በመብራት ተፈልገሽ የተገኘሽ ከባድ ሚዛን ምሁር እንዳይደለሽ ራስሽም ብዙ ሰዎችም እናውቃለን። በየት በኩል ሄደሽ ለሹመት እንደበቃሽ ብዙ ሰዎች ያውቃሉ። ይህ ብቻ ትሁት (humble) ሊያደርግሽ ይገባ ነበር። ስልጣንና ዕውቀትን የሚያደባልቀው ያገራችን ዛር አንቺ ላይ የሚፈልቅ አልመሰለኝም ነበር። ያ የደርጉን ሀምሳ አለቆች ባንድ ሰሞን የማርክሲስት ሶሻል ሳይንስ ሊቅ ያደረገው ዛር። ያ አቶ በረከት ስምኦንን ስልጣን የያዘ ሰሞን ስድስት ኪሎ መኮንን አዳራሽ ውስጥ የዩኒቨርሲቲውን ፕሮፌሰሮች ሰብስቦ ታሪክ እንዲያስተምር ያዘዘውና ሲያንቀዠቅዥ አምጥቶ ያላተመው ዛር። ሳትሳደቡ ታማኝነታችሁን ላለቆቻችሁ ማረጋገጥ አትችሉም? ያ አስገራሚ ያማራ ህዝብ መሪ ነኝ የሚል ጓድሽ እንዲመራቸው መረጡኝ የሚላቸውን ከገዛ ሀገራቸው በግፍ የተፈናቀሉ ዜጎች ለሀጫሞች ብሎ ሲሳደብ ሰምቼ ገርሞኝ ነበር። ውሏችሁ አንድ ላይ ቢሆንም አንቺ ከሱ ብዙ የምትሻይ መስሎኝ ነበር።
ሌላው የገረመኝ ደግሞ 41 ፕሮፌሰሮች ማባረርን ተራ የቁጥር ነገር አድርገሽው የተባረሩት 41 ብቻ በመሆናቸው የሚጎዳ ነገር እንዳልተከተለ አድርገሽ የተናገርሽውና ለዚያም ከዚያ በኋላ የተገኘውን የባለ ማስተርስና ፒኤችዲ ብዛት እንደማስረጃ ያቀረብሽው ገለባ ነገር ነው። 41 ብቻ ስትይ ልክ አንድ ገበሬ ዶሮዎቹን የሚቆጥረው ነገር አስመሰልሺው። ገበሬውም ቢሆን ዶሮዎቹን አንድ ሁለት ሶስት ብሎ ይቁጠራቸው እንጂ ገበያ ላይ ሲወጡ ላባ ብቻ የሆኑትንና ዳጎስ ያሉትን የሚሸጣቸው በተለያየ ዋጋ መሆኑን ያውቃል። ወይዘሮ Educator in Chief ምሁራን የሚቆጠሩት ከአካዳሚክ ልምድና ችሎታቸው ክብደት ጋር መሆኑን ስተሽዋል። ከዚህ ቁጥር ጋር ከኛ መባረር በኋላ በብሽቀት በራሳቸው የለቀቁትን ፥ ሞራላቸው ተነክቶ ተነሳሽነታቸው የተጎዳውን ከቁጥርም አላስገባሽውም። በዚህ ላይ የኛን ሁኔታ ያዩ ብዙ ውጭ ሀገር ትምህርት ላይ የነበሩ ጓደኞቻችን በወጡበት መቅረታቸውንም ደብቀሻል። የኔ እህት በቁጥር መዋሸት ጥንቃቄ ይጠይቃል። አገር የሚያውቀው ነገር ላይ መዋሸት ደግሞ የመሀይም ፈጠጤነት እንጂ እንዳንቺ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ዘመን ካሳለፈ ሰው አይጠበቅም። ያንቺና የአለቆችሽ የቁጥርና ስታቲስቲክስ አጠቃቀም አንድ ያንቺ ብጤ ዝነኛ የሂሳብ ሊቅ ያስታውሰኛል። ሂሳብ አዋቂው ጥቂት ቁመታቸው ረጅም ከሆነ ብዙ አጫጭር ሰዎች ጋር ሲጓዝ የሞላ ወንዝ ያጋጥማቸዋል። ወንዙን በግር ተራምዶ ለመሻገርም ይፈራሉ። የሂሳብ “ሊቁ” አንድ መላ መጣለትና የወንዙን ጥልቀትና የተሻጋሪውን ቁመት በሙሉ ለካ። የሰዎቹን ቁመት አማካይ (Average) አሰላና ከወንዙ ጥልቀት እንደሚበልጥ ካረጋገጠ በኋላ ለተሻጋሪዎቹ በአማካይ(on the average) ሁሉም ሰው መሻገር ይችላል ብሎ አወጀ። ሰዎቹም በሊቅነቱ አምነው ማቋረት ጀመሩ። ምን ያደርጋል። ቁመታቸው ከአማካይ በታች የሆኑትን በሙሉ ውሀው በላቸው። አየሽ እህቴ ቁጥር ትርጉም የሚኖረው በደረቁ ሳይሆን በይዘቱ ሲተረጎም ብቻ ነው። ይህንን ላንቺ መንገር እንዴት ያሳፍራል መሰለሽ። አለማቀፍ ረጅዎቻችሁ ርዳታ ለመጨመር የሰራችሁትን ስራ ውጤት አሀዝ እንደሚጠይቋችሁ በዚያም ተመስርተው እርዳታ እንደሚሰጧችሁ እናውቃለን። ትምህርት ከተጀመረ በኋላ ተንጠባጥበው የሚቀሩትን ሺዎች ሰርዛችሁ መስከረም ላይ በዘመቻ የመዘገባችኋቸውን ተማሪዎች ቁጥር ያህል አስተማርን እያላችሁ ርዳታም እንደምታገኙ አገር ያውቀዋል። ለፈረንጅ መዋሸታችሁ ብዙ ገንዘብም ያስገኛል። ፈረንጆቹ ውሸቱን ቢያውቁትም ግድ የላቸውም። ይህን ውሸት ለኛው ለባለቤቶቹ እውነት ነው ብሎ መንገር ግን ዐይን አውጣነትም ሰው ንቀትም ብልግናም ነው።
የቁጥር ነገር ከሆነ አሁን እስቲ የተባረረውን የማቲማቲክሱን ፕሮፌሰር አየነው እጅጉንና ራስሽን ለምሳሌ ያህል አወዳድሪ። እውነቱን ከተነጋገርን ለዚያ ዩኒቨርሲቲ ተብሎ ብትቆጠሩ እሱ መቶ አንቺ አንድ የምትሆኑ ነው የሚመስለኝ። ይህንኑም ላንቺ ቸር ሆኜ ነው። እኔን አንድ ቀን አንድ አለማቀፍ ጉባዔ ላይ እንዳጋጠመኝ ምሁራን ስራውን ለምርምር እንደተገለገሉበት እያደነቁ ሲጠቅሱ ብትሰሚ ዝሆን አጠገብ የቆመች እይጥ ሆነሽ ነበር ራስሽን የምታገኝው። የዚህን ለምሳሌ ያህል የጠቀስኩልሽን ምሁር ፕሮፋይል ይህን ማስፈንጠሪያ ጠቅተሽ (http://www.linkedin.com/in/ayenewejigou) ምን እንደሚመስል እስቲ ተመልከች። ትንፋሽ ያሳጥራል አይደል? እሱ ወዲያው ሰው አገር ዩኒቨርሲቲ ሄዶ ያንድ ፋኩልቲ ዲን መሆን ችግር አልነበረበትም። የኛ ሀገር ደፋር ግን አፍሽን ሞልተሽ Fit አያደርግም ትይዋለሽ። የፕሮፌሰር አስራት ወልደየስን የህክምና እውቀትና መምህርነት ሰንት ድንጋይ ቀጥለሽ ተንጠራርተሽ ብቁነታቸውን ለመጠየቅ እንደሞከርሽ ገርሞኛል። ካንቺ ዘለፋና እሳቸው አወጡልሽ ከሚባለው የሙገሳ ስም የትኛው ለዕውነት የሚቀርብ ይመስልሻል? ጊዜ የሰጠው ቅል ድንጋይ ይሰብራል የሚለውን አባባል በጥሬው የተረጎምሽው መሰለ። አሁን ባለስልጣን ሲያረጅ የሚሰጠውን የዲፕሎማትነት ሹመት መሾምሽን ሰምቻለሁ። ይህን ዓይነት የቋንቋ አጠቃቀም ይዘሽ ምን አይነት ዲፕሎማትሲ እንደምትሰሪ ማሰብ ከባድ ነው።
41 ፕሮፌሰሮችን ማባረርና ባንቺ ስልጣን ዘመን የተገኘውን የዲግሪ ብዛት የቁጥር ነገር ብቻ ስታደርጊው የሰራሽው ሌላ ስህተት ምን ያህል ግዙፍ እንደሆነ በቀላል ምሳሌ ላስረዳሽ። ለምሳሌ አንቺ ታስተምሪ የነበረውን ዓይነት የማስተማር ሙያ ካንድ ቢሮ ውስጥ እንድ ሴክሬታሪ ጠርቶ እንድትሸፍነው ማድረግ ይቻላል። ያው እንዳስተማርሻት ታስተምራለች ማለት ነው። ሌላ ልጨምርልሽ። አምና አራተኛ ዓመት የጨረሰ ኮሌጅ ተማሪ ዘንድሮ የአራተኛ ዓመት ተማሪዎችን ገብቶ የተማረውን ደግሞ በተማረበት ዘዴ “ማስተማር” ይችላል። ሁለት ፕሮፌሰሮች በይ ባንቺ አቆጣጠር። ለነገሩ አሁን ዩኒቨርሲቲ እያላችሁ በምትከፍቱዋቸው ቦታዎች ትምህርት የሚሰጠው በዚህ መንገድ መሆኑን ሰምቻለሁ። በዚህ መልክ የተማሩት ተማሪዎች ደግሞ አንቺ እንደዶሮዎችሽ የምትቆጥሪውን ዲግሪ ይይዙና ዞረው አስተማሪ ይሆናሉ። አየሽው የቁልቁለቱን መንገድ? ዛሬ የኢትዮጵያን ትምህርት ጥራት ገፍታችሁ የለቀቃችሁት በዚህ የቁልቁለት ላይ ነው። እንዲህ አይነት ትምህርት አስተምሮ እግዚአብሄርንና ታሪክን ወይም ያለምአቀፍ ስታንዳርድ ችግር ካልፈሩ ዲግሪ መስጠት የሚከለክል የለም። በየስርቻው ዩኒቨርሲቲና የፒኤችዲ ፕሮግራም መክፈትም የሚከለክል ነገር አይኖርም ማለት ነው። ነገሩ እንዲህ ከሆነ ደግሞ በያመቱ ዲግሪ እንደቆሎ እየዘገኑ ለመስጠት የሚያግድ የለም። ይህ ግን ከፍተኛ ትምህርት አይባልም ወይዘሮ Educator in Chief። የከፍተኛ ትምህርት ትርጉም ባጭሩ የዕውቀትን ዳር ድንበር መግፋት (pushing the envelope) ነው ሲባል ስምተሽ እንኳን አታውቂም? የከፍተኛ ትምህርት ማለት የከረመ ነባር ዕውቀት እንዳለ መገልበጥና ማንከባለል ማለት አይደለም። የከፍተኛ ትምህርት ዓላማ የታወቀው ነገር ላይ አዲስ ነገር መጨመር ፣ ያልተገለጠ ነገር እንደሽንኩርት ወደ ውስጥ እየላጡ መግለጥ ፣ ቅቡል (ኮንቬንሽናል) ዕውቀትን መሞገትና መጠየቅ ፣ ኢኖቬት ማድረግና መፍጠር ፣ ህዝብ በዘመናት ያካበታቸውን ጠቃሚ ሀገር በቀል (indigenous) ዕውቀቶች እየፈለፈሉ እያጠኑ ጥቅም ላይ ማዋል ፣ ይህን ሁሉ ደምሮ የሰውን ልጅ ኑሮ ማቅለል ማለት ነው ባጭሩ። የኔ እህት ሰው እኮ ትምህርት ቤት ሳይገባም የሚማራቸው ነገሮች አሉ ዲግሪ አያሰጡም እንጂ። የባለፒኤችዲ መብዛትም የዕውቀት መስፋፋት መለኪያ የማይሆነው ለዚህ ነው። የኮንቴነር ኮሌጅ ከፍተው ዲግሪ ስለሚያንበሸብሿችሁ ሰዎች ጉዳይ እኮ አንድ ጥሏችሁ የመጣ ሚኒስትር ሰሞኑን ነገረን። የዲግሪ ቁጥር ከምትነግሪን በነበረን ዕውቀት ላይ ስንት አዲስ ነገር እንደጨመርን ፣ ምን ያህል ሳይንሳዊ ኢኖቬሽን እንደተገኘ፣ ወይም ባለዲግሪዎቹ በፈጠራ ስራቸው የሰሩትን አዲስ ስራ ብትነግሪን ነበር ነገረሽ ትርጉም የሚኖረው። ድንጋይ ፈላጭነት ስለሚቀጠሩት የኮሌጅ ምሩቃንና ለትምህርታቸው ስለባከነው የህዝብ ገንዘብ ምን ታስቢያለሽ ብላ ጋዜጠኛዋ ሳትጠይቅሽ ቀረች። ለሱ የምትሰጭው መልስ ናፍቆኝ ነበር።
ርግጥ ነው ሁሉንም የተባረርነውን መምህራን መተካት ይቻላል። ቀላል ያልሆነ ጊዜና ንብረት ግን ይወስዳል። ለኢትዮጵያ ደግሞ ጊዜ ከጎኗ አይደለም። የሰው ሀይል መገንባት የተቃጠለ ቤት መልሶ እንደመገንባት ቀላል አይደለም። ለዚህ ነው እህቴ በተባረርነው ሰዎች የተፈጠረውን ጥፋት እንደ ሀገር ኪሳራ ወስዶ ከመሄድ ውጭ በምላስ መድፈን የማይቻለው። ለፖለቲካ ስንል ሀገሪቱን ያስከፈልናት ሂሳብ ነው ብሎ መቀጠል ማን ገደለ? ታዛቢ ቢኖር እንጂ ጠያቂ እንደሆን የለ። የተባረርነውን ብዙ መምህራን ቦታ እንዴት ባጭር ጊዜ መሸፈን እንደማይቻል ልንገርሽ። ራሴን ምሳሌ ልስጥሽ። እኔ ለምሳሌ ካንቺ ባገልግሎት ዘመንም በዕድሜም የማንስ ገና ብዙ ልሰራ ተስፋ የማደርግና ብዙ ያልሰራሁ ጁኒየርና መምህር ነበርኩ። ከብዙዎቹ ከተባረሩት በጣም ያነሰ ደረጃ ላይ ነበርኩ። በምማርበት መስክ ግን በዓይነቱና በዘመኑ አዲስ የሆነ የዕውቀት ዘርፍ ተማሪ ነበርኩ። ያን ጊዜ ገና እየተጀመረ የነበረውን GIS(Geo-information Systems) ቴክኖሎጂ ከህክምና ሳይንስ ጋር አገናኝቶ በመጠቀም ሀገራችን ላይ የሰፈኑና በየጊዜው የሚከሰቱ በሽታዎችን ከባቢያዊ ባህርይ ከተጠቂ ህዝብ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ባህሪ ጋር ቁርኝታቸውን በማግኘት ለመቆጣጠር የሚበጅ ሳይንስ ነበር። ዩኒቨርሲቲው ውስጥ የነበረው ሜዲካል ጂዖግራፈር እኔ ብቻ ነበርኩ። ያ ድሀ ህዝብ ፈረንጅ ፕሮፌሰር በዶላር ቀጥሮ ነው ያስተማረኝ። እስከአሁን እዚያ ብኖር ኖሮ ብዙ ተማሪዎች አስተምርና ፣ ምርምርም እንሰራና፣ ምናልባትም ተላላፊ በሽታ ሰርጭትን አስቀድሞ የማየትና መመከቻ ዘዴና ሞዴል በማበጀት ህይወት አድን ዕውቀትና ዘዴ ከሌሎች ባለሙያዎች ጋር ሆነን እንገነባ ነበር። ይህ ቀዠት ሊመስልሽ ይችላል። ለኔ ህልሜ ነበር። ይህ ለኛ አይነት ደሀ አገር የሚሆን ፕሮግራም በነበርኩበት ዲፓርትመንት እስከዛሬም አለመጀመሩን አውቃለሁ። እኔ ስባረር እንደቀረ ቀረ። ዛሬ ለትምህርቴ ስሙኒ ያልከፈለው የስደት ሀገሬ ይህን ሙያዬን በደንብ ይጠቀምበታል። ጊዜ የለም እንጂ ሌላም ብዙ ምሳሌ እሰጥሽ ነበር። እኔ ትንሹ ይችን ታክል ካጎደልኩ ግዙፎቹ ምሁራን ምን ያህል እንደሚያጎድሉ ብቻ አስቢው።
ደብዳቤዬን ከመዝጋቴ በፊት ትምህርትን አስመልክቶ ስለተናገርሻቸው ሌሎች አሳፋሪ ነገሮች ትንሽ ልንገርሽ። በቃለ ምልልስሽ ላይ ከሰቀጠጡኝ ነገሮች አንዱ እስከ አራተኛ ክፍል ድረስ ተምረው ማንበብና መጻፍ ሳይችሉ ስለቀሩት ተማሪዎች ተጠይቀሽ የሰጠሽው መልስ ነበር። እነዚያን እንደጊኒ ፒግ የተጫወታችሁባቸውን የድህ ህዝብ ልጆች ለዚያ ሁኔታ የበቁበትን ምክንያት ካለምንም ይሉኝታ እንዳለ በመምህራኑ ላይ ደፈደፍሽው። ቆየት ብለሽ ደግሞ ወደፊት ቴሌቪዥን ተክቶን ስራችንን እናጣለን ብለው የፈሩ መምህራን ናቸው ችግሩን የፈጠሩት ስትይ መምህራኑን ምንም የማያውቁ ቂሎች አስመስለሽ ሰደብሻቸው። አነጋገርሽ የጥጋበኛ ይመስላል ያልኩሽ ይህን ሁሉ ታዝቤ ነው። እንዲመክሩበት ያልጋበዛችኋቸውን የፖሊሲ ችግር ተቋቁመው እንደዚያ እንደሻማ እየቀለጡ በድህነት እየተቆራመዱ የሚያስተምሩ መምህራን ካለቃቸው ከስድብ የተሻለ ይገባቸው ነበር። ያንቺንና ያለቆችሽን ጥፋትና ተጠያቂነት ግን “ቻሌንጅ ነበረብን” በምትባል የጮሌዎች የንግሊዝኛ ቃል በኩል አድርገሽ ለመደበቅ ሞከርሽ።
ሌላም ሳልነግርሽ ማለፍ የማልፈልገው አለ። ስለነዚያ ከሻሸሜኔ አካባቢ ቢሮሽ ድረስ ላቤቱታ መጥተው የተቃዋሚዎች ፕሮፓጋንዳ ገዝተው ቋንቋችን ወንዝ አያሻግርምና ልጆቻችን ባማርኛ ቋንቋ ይማሩልን አሉ ብለሽ ስለተዛበትሽባቸው ሽማግሌዎች አንድ ነገር ሳልነግርሽ ብቀር ውለታ አጎድልብሻለሁ። ሽማግሌዎቹ ብዙ እንደበለጡሽ የገባሽ አልመስለኝም። ባንቺ ቤት ቋንቋችን ወንዝ አያሻግርም ያሉት ያው የትምክህተኞችን ወሬ ሰምተው ራሳቸውን በመናቃቸው ነው። ቋንቋ ወንዝ አያሻግርም ሲሉ ልጆቻችን አማርኛ ካልቻሉ ባካባቢያችን ስለሚቀሩ በትልቅ ሀገር ውስጥ ተዘዋውረው መስራት አይችሉም ሊሉሽ ፈልገው እንጂ እናንተ ባትከልሉትም የጎሳቸው መኖሪያ የት ድረስ እንደሆነ አጥተውት እንዳይመስልሽ። አማርኛም ባህር ስለማያሻግር ነው እንግሊዝኛ የምንማረው አይደል? አማርኛም ቢሆን በብዙ ያገራችን አካባቢዎች የማያሻግራቸው ወንዞች አሉ። ይህ እውነት እንጂ ምኑ ነው ስድብነቱና ንቀትነቱ ወይም አለማወቅነቱ? እንደ ቋንቋ ወላይትኛ ካማርኛም ከንግሊዝኛም አያንሰም። የሰዎች የኑሮ መሻሻል ዕድል(opportunity) ሰፋት ግን መናገር ከሚችሉት ቋንቋ ጂዖግራፊያዊ ስፋትና በተለይ የሰራ ዕድል ባለባቸው ከተሞች ውስጥ ብዙሃኑ ከሚናገሩት ቋንቋ ችሎታ ጋር የተያያዘ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ አማርኛ በቅጡ አለመቻል ያንድን ሰው የኑሮ ህልምና የማደግ ጣራ ይገድባል። ሽማግሌዎቹ ይህ ገብቷቸዋል። አንቺና አለቆችሽ ቋንቋውን ከአማራ ረጋሚ ፖለቲካችሁ ጋር ስለምታገናኙት ነው የተምታታባችሁ። እነዚያ ሽማግሌዎች ደግሞ ብዙ ልጆች ባካባቢያቸው ባማርኛ ተምረው ከፍ ያለ ዕድል ሲያገኙ አይተዋል። ቋንቋ እንደ አካፋና ዶማ መሳሪያ መሆኑ ገብቷቸዋል። ባለስልጣናቱ ለልጆቻችሁ የማትመኙትን ለነሱ እንደተመኛችሁላቸው አውቀዋል። ለመሆኑ አሁን አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ በወላይትኛ ብቻ እየተናገረና ባስተርጓሚ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆን ነበር ብለሽ ታምኛለሽ? አቶ መለስም ጥሩ አማርኛ ተናጋሪ ባይሆን ኖሮ እንኳን ጠቅላይ ሚኒስትር የህወሀትም መሪ ለመሆን የሚቸገር ይመስለኛል። ሰው በራሱ ቋንቋ ቢማር ጥሩ ነው። ትምህርት ያቀላል። በሁለተኛ ቋንቋ ተምሮ ሰው አዋቂ መሆን የማይችልና ጥቅም የማያገኝ አስመስለሽ ያወራሽው ግን ተራ ድንቁርና ነው። ያማርኛን ቋንቋ ራሱን ካዳበሩት ሰዎች ውስጥ ብዙዎች አማራ ያልሆኑ አማርኛን በሁለተኛ ቋንቋነት የተማሩ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን የምታውቂም አይመስልም። አማርኛ አለመቻል ባለንበት ባሁኑ ዘመንና ለመጭውም ብዙ ዓመታት ይጎዳል። የአዳጊውን ትውልድ ዕድል (opportunity) ይቀንሳል። ይህን የሚጠራጠር መሬት ላይ ያለውን ዕውነት ማየት የማይችል ወይም ኢትዮጵያን የባቢሎን ግንበኞች አገር በማድረግ የማይግባባ ህዝብ ፈጥሬ ትርፍ አገኛለሁ ብሎ ያሰበ ብቻ ነው። እንዴውም ኦሮምኛን አማርኛ ላይ ብትጨምሩት ሀገርነታችንንና ህዝቡን ብዙ ትጠቅሙት ነበር። አማርኛ ከማንም ቋንቋ በልጦ ሳይሆን ታሪክ በሰጠው አጋጣሚ ምክንያት ባብዛኛው ኢትዮጵያ የክተማ (urbanization)ና የሀገሪቱ ዘመናዊ ኢኮኖሚና ኢንዱስትሪያላይዜሽን ቋንቋ ነው። ወደፊትም ለረጅም ጊዜ ሆኖ መቀጠሉ አይቀርም። ታዲያ ሽማግሌዎቹ ምን አጠፉ? ሽማግሌዎቹ ይህን ፊት ለፊት አይተዋል። የምታገለግይው ፖለቲካ ላንቺ ወደ ማጅራትሽ አዙሮ ሰውሮብሻል። ይህ ብጅጉ ሊያሳፍርሽ ይገባል።
ፖሊሲያችሁ አንድ ትውልድ ስለመጉዳቱ ለተጠየቅሽው ጥያቄም ያሁኑን ኢኮኖሚ እድገት ታዲያ እንዴት ተገኘ? ለመሆኑ ከሀያ አመት በፊት ከነበረችበት አገራችን አልተሻለችም?” ብለሽ በጥያቄ መልሰሻል። እኔ የማየው የኤኮኖሚ እድገት በትምህርት አጋዥነት በተፈጠረ ዕውቀትና ኢኖቬሽን ሳይሆን ከውጭ በሚገኝ ርዳታና በገፍ የተሰደደው ኢትዮጵያዊ በሚልከው ገንዘብ የተገኘ መሆኑን ነው። ለገበያ የምታቀርቡት እንደሆን ያው እንደዱሮው ቡናና ቆዳ ነው አይደል? ከትምህርት በተገኘ አዲስ ግኝት ይህ ተገኘ ሲባል ሰምቼ አላውቅም። እስከ አርባ በመቶ የሚደርስ የገጠር ልማት በጀት በርዳታ እንደሚሸፈንና ከሰሀራ በታች ዋና በርዳታ የምትኖር ሀገር እያስተዳደራችሁ መሆኑ ሚስጥር አይደለም። ብድሩም 20 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል ይባላል። ይህን መጠን በርቀት እንኳን የሚቀርብ ገንዘብ ቢያገኙ በዘመናቸው በነበረው የተማረ ሰው ሀይል ብቻ አሁን ተሰራ የምትሉትን ነገር መስራት ለደርግም ለኃይለስላሴም አያቅታቸውም። እዚያ አገር ውስጥ በትምህርት አዲስ ዘዴ አፍልቃችሁ የፈጠራችሁትን የሀገር ሀብት አንድ ሁለት ብለሽ መቁጠር አትችዪም። ለምሳሌ ገበሬው ከሚያመርተው እህል ከ 30 እስከ 40 በመቶ ያህል በቴክኖሎጂ ችግር ምክንያት ውድማና ርሻው ማሳ ላይ እንደሚባክን ዛሬም ባለሞያዎች ይነግሩናል። ቢከፍቱ ተልባ የትምህርት ፖሊሲያችሁ እህል ተለምኖ በሚኖርበት ሀገር ይችን እንኳን የሚያስወግድ የገጠር ቴክኖሎጂ ዕውቀት ማፍራት አልቻለም። ባቡር መንገድ ሰራን ፣ ህንጻ ገነባን የምትሉት ፕሮፓጋንዳ ዱሮ አጼ ኃይለስላሴን “ውሀ ፎቅ ላይ ያወጣ ንጉስ” ከሚለው ከንቱ ውዳሴና ፕሮፓጋንዳ ብዙም አይለይም። የደብዳቤዬ ትኩረት የትምህርት ስታርቴጃችሁን መተቸት አይደለም እንጂ ብዙ ልነግረሽ የምችለው ነበረኝ። ይህን ደብዳቤ እየጻፍኩ አንድ የህክምና ፕሮፌሰር አአዩ ሜዲካል ፋኩልቲ ውስጥ ሲያስተምር የተመለከተውን አስደንጋጭ አስተያየት አነበብሁ። በቁጥር ልታደልቢው የምትሞክሪው የትምህርት ፖሊሲ ምን ያህል ሀገር አደጋ ላይ የጣለ መሆኑን እንደ አንድ ዜጋ እንድትመለከችው እዚህ ለጥፌልሻለሁ (http://www.ethiomedia.com/11notes/2816)። ቢያንስ በሰው ህይወት ላይ ብዙ ቀጥተኛ እጅ ያላቸውን የሀኪሞች ትምህርት የቁጥር ነገር ባታደርጉት ምን ትሆናላችሁ? ይህ ፕሮፌሰር ሀኪም ድፍረቱን አግኝቶ ይህን ባደባባይ መረጃውን አቅርቦ ስለተቸ ክብር ይገባዋል። ብዙ ጊዜ ለኔ ብጤ ተችዎቻችሁ (critics) እንደምትሰጡት መልስ ከሆነ ወንጀለኛ ብትሉት አይገርመኝም።
የሰዎች መሻሻል የሚገኘው ዝቅተኞቹ ወደ ላይ እንዲያድጉ በማገዝ ሳይሆን የተሻሉትን ዝቅ በማድረግ ነው የሚለውን የመለስ ዜናዊ Reverse Affirmative Action የፖሊሲ መመሪያ ባታደርጉትና ቢያንስ ከነችግሩ በዓለም ተወዳዳሪ ሆኖ የቆየውን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባለበት ብታቆዩትና በላዩ ብትጨምሩ ለሌሎቹ የሚተርፍና ብዙ ቀዳዳ የሚሞላ (Flagship) ተቋም መሆን ይችል ነበር። ዛሬ ይህን ተሳድቦም ፣ ተቆጥቶም ፣ አስፈራርቶም ሰዎች እንዳይጠይቁ ማድረግ ይቻላል። ሁላችንም በማንኖርበት የወደፊቱ ዘመን ግን ታሪክ ይህን ጥይቄ ጮሆ እንዳይጠይቅና ፍርድ እንዳያገኝ ማድረግ አይቻልም።
እህቴ ተናግረሽ ብዙ አናገርሽኝ። ኢትዮጵያ ሰማይ ላይ ከባድ ዝናብ መምጣቱን እንደሚያበስር ደመና የሚያስገመግም ይህዝብ ብሶት ድምጽ ከሩቁ ይሰማኛል። እሱ ከሚያስነሳው ማዕበል ይሰውርሽ።
(Fekadeshewakena@yahoo.com)
No comments:
Post a Comment