Monday, December 1, 2014

አንገት የሚያስደፋ እውነታ! 200 ገደማ ኢትዮጵያውያን የሕክምና ባለሙያዎች ውደ ምዕራብ አፍሪካ ሊሄዱ እየተዘጋጁ ነው፡፡

አንድ ወዳጄ ትላንት አመሻሽ አከባቢ ተደዋውለን ሻይ ቡና እያልን በወሬ መኸል ኢቦላ ሕመምተኞችን ለማከም ወደ ምዕራብ አፍሪካ ለመሄድ “እነዳለፈ” ነገረኝ::

በድንጋጤ “ምን ማለትህ ነው ‘አለፍኩ’ ስትል?” አልኩት:

“እንዴ፡ የቀረ ሐኪም እኮ የለም፡፡ እዚሁ ትግራይ ከሚሰሩ ጠቅላላ ሓኪሞች ከግማሽ በላይ ተመዝግበው ነበር፡፡ ጥቂቶች በዋናነት በግልጋሎት ግዜ ብዛት ተመረጥን” አለኝ፡፡

“እንዴት እንዲህ ሰው ሊበዛ ቻለ?”

“እንዴ፡ የወር ክፍያው እኮ እዚህ ኢትዮጵያ በሶስት ዐመት የምታገኘው አይደለም፡፡ 250 ዶላር አበል በቀን፣ ሙሉ የምግብና የመጠልያ ወጪ፤ አበሉን ብቻ ብታሰላው 250 ዶላር በቀን 7500 ዶላር በወር ነው፡፡ ይህ በኛ 150 ሺህ ብር ነው፡፡ እዚህ ኢትዮጵያ 150 ሺህ ብር ሴቭ ለማድረግ እኮ 5 ዐመትም አይበቃህም፡፡ ለ3 ወር ስለሆነ 450 ሺህ ብር አገኝህ ማለት ነው፡፡ ያ አበል ብቻ ነው፤ ተጨማሪ ሌላ ክፍያም አይጠፋውም፡፡ ምናልባት ይህ ገንዘብ አሁን ባለችው ሀብቷ በባለስልጣናትና ጥቂት ተባባሪዎቻቸው ደንቆሮ ነጋዴዎች የተያዘው ኢትዮጵያ 10፣ 15 ዐመት ለፍተህም የምታገኘው አይደለም፡፡ ታድያ ለዚህ የሐገሪቷ ሐኪሞች ቢጋደሉ ምን ይገርምሀል የኔም የሌላ ተመዝጋቢዎችም ምክንያት በዋናነት ይህ ነው፡፡”

ስለክፍያውና ሌላሌላው እኔም ሰምቼ ነበር፡፡ ገንዘቡ ትንሽ እንዳልሆነ እኔም እስማማለሁ፡፡ እዚህ ሀገሬ ውስጥ ያለውን መራር ሐቅም በደምብ አውቀዋለሁ፡፡ ቢሆንም ጓደኛየ እንዲህ በሚያም መልክ ሲገልፀው ግን እንደአዲስ የሆነ ውጋት ነገር ተሰማኝ፡፡
ጓደኛየ ዘንድሮ የሆነ ትምህርት ለመማር እየተዘጋጀ ነበር፡፡ ያንን ጭምር መስዋእት አድርጎ ነው እየሄደ ያለው፡፡ ከጥቁር አምበሳና ዐይደር ሪፈራል ሆስፒታልም ትምህርት አቋርጠው ለመሄድ የተዘጋጁ እንዳሉ ይሰማል፡፡
የትውልዴ፣ የምሁሩ፣ የብርቱ ሰራተኛው ክፍል ተስፋ መቁረጥ አንገት የሚያስደፋ ነው፡፡ እኔ ይህ ብሄራዊ ውርደት ይመስለኛል፡፡


No comments:

Post a Comment