Tuesday, September 9, 2014

እስር ቤቶቻችን በሕገ-መንግሥት ወይንስ በ‹‹ሕገ-አራዊት››?

በጌታቸው ሺፈራው
---------------------
የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትን እንዲጸድቅ በበላይነት የመሩት አቶ መለስና አቶ ሌንጮ ለታ መሆናቸው ይነገርላቸዋል፡፡ ይህ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ጉዳይ ቀጥተኛ ተሳታፊ ባልሆኑት የተገንጣይ መሪዎች ጠንሳሽነት የጸደቀው ሕገ መንግሥት ለአገር ሉኣላዊነት፣ አንድነትና ታሪክ ክብር የሌለው ቢሆንም ዓለማቀፋዊ የሰብኣዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን አጠቃልሏል፡፡ ሆኖም እነዚህ ሰብኣዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ለእርዳታ ማሰባሰቢያ የተቀመጡ እንጂ ወደመሬት ወርደው ተግባራዊ መሆና ባለመቻላቸው የይስሙላህ ሕግ ሆኗል፡፡ ከሕገ መንግሥቱ ይልቅ የገዥዎች ጊዜያዊ ሥልጣን ጥቅም ለማስጠበቅ በየጊዜው ትርጉሙ የሚቀያየረው የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ‹‹መርሕ›› ሕዝብ ላይ የተጫነ ገዥ ሕግ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ ይህን ስርዓት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም ‹‹ሕገ አራዊት›› ሲሉ ይገልጹታል፡፡ በዚህ ስርዓት ሕዝብ በሕግ ስም እንጂ በሕግ የሚዳኝበት አጋጣሚ አይታይም፡፡ ብዙዎቹ በዚህ ስርዓት ያለውን የኢትዮጵያን ሕዝብም የታሰረ፣ ታስሮ የተፈታና ለወደፊት የሚታሰር እያሉ በቀልድ መልክ በሦስት የእስራት ምድብ ያስቀምጡታል፡፡ እንደ እኔ ሌላ አራተኛ ምድብም ሊካተት ይገባዋል፡፡ ይኸኛው እንደ ሦስቱ ምድቦች የአካል ጉዳትና ሰብኣዊ መብት ጥሰት የማይደርስበት ሕገመንግሥቱን አጽድቆ ራሱ የሚጥሰው አሳሪው ክፍል ነው፡፡ ይህ አሳሪው የኅብረተሰብ ክፍል በአካል ያልታሰረና ስርዓቱ እስካለ ድረስ በአካል ሊታሰርበት የሚችለው አጋጣሚ ጠባብ ቢሆንም የአዕምሮ እስረኛ ነው፡፡


ኢሕአዴግ እየዘመረለት የሚገኘው አቶ መለስና በእኩል ደረጃ የሚያወግዘው ‹‹አሸባሪው›› አቶ ሌንጮ ያጸደቁት ሕገ-መንግሥት ኢትዮጵያውያን ታሳሪዎች ምቹ ሁኔታ እንዲመቻችላቸው በርካታ አንቀጾችን አስቀምጧል፡፡ ለአብነት ያህል አንቀጽ 19 (2) የተያዙ ሰዎች ላለመናገር መብት እንዳላቸው ይደነግጋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (5) ‹‹የተያዙ ሰዎች በራሳቸው ላይ በማስረጃነት ሊቀርብ የሚችል የእምነት ቃል እንዲሰጡ ወይንም ማንኛውንም ማስረጃ እንዲያምኑ አይገደዱም፡፡ በማስገደድ የተገኘ ማስረጃ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡›› ቢልም በተለያዩ ጊዜያት የተሰሩ የፕሮፖጋንዳ ፊልሞች ላይ ‹‹እማኝነታቸውን›› የሰጡ ታሳሪዎች የሚሰጡት ቃል በኃይል የተደረገ መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡
መጋቢት 8/2005

ይህን እውነታ እሁድ መጋቢት 8/2005 ‹‹ለማርሻል ግራዚያኒ ክብር መሰጠት የአባቶቻችንን መስዋዕትነት ማራከስ ነው›› በሚል የተደረገ ሰላማዊ ሰልፍ ተከትሎ እኔና ጉዋደኞቼ በታሰርንበት ወቅት ለማረጋገጥ ችያለሁ፡፡ አንድ ታሳሪ ከአንድ ጊዜ በላይ ቃል መስጠት እንዳለበት የሚገልጽ የሕግ አሠራር ባይኖርም ከሶስት እስከ አራት ጊዜ ቃል እንድንሰጥ ተደርገናል፡፡

በመጀመሪያው ዙር ሁሉም ሕገ መንግሥቱ ‹‹ሰጥቶኛል›› ያለውን መብት ተጠቅሞ ‹‹ቃል አልሰጥም›› ብሎ ፊርማውን አስቀምጦ ወጣ፡፡ በዚህ የተደናገጡት መርማሪዎች አንዳንዶቹን ቃል እንዲሰጡ ቢያባብሉም ሊሳካላቸው አልቻለም፡፡ በታጎርንበት ጣቢያም ሆነ በሌሎቹ ጣቢያዎች የፖሊስ አባል መሆናቸው ያልታወቀውና ከመጀመሪያው ጀምሮ ሰልፉን የበጠበጡት ‹‹ኮማንደር›› ግን ‹‹ይህ ፒቲሽን በመሆኑ ጥንቃቄ ሊደረግበት ይገባል›› በሚል መርማሪዎች የቻሉትን ሁሉ ተጠቅመው ቃል እንዲቀበሉን ትዕዛዝ አስተላልፈዋል፡፡ ሆኖም ሁሉም ታሳሪዎች ቃል ሳይሰጡ ቀሩ፡፡ ይህን ተከትሎም የይስሙላህ ሕገ መንግሥቱ ተግባር ላይ የዋለው ለተወሰኑ ደቂቃዎች ብቻ ሆነ፡፡
ቃል አንሰጥም ካልንበት ወቅት በኋላ ለጥቂት ጊዜ ጠፍተው የቆዩት ‹‹ኮማንደር›› ታሳሪዎች በእየተራ ፎቶ ግራፍና ቪዲዮ እየተቀረጹ ሌላ ተጨማሪ ቃል እንዲሰጡ አደረጉ፡፡ ይህን ምርመራ የሚያከናውኑት ፖሊሶች ሳይሆኑ ደህንነቶች በመሆናቸው ቃል አልሰጥም የሚለው መብት አይሰራም፡፡ ተመርማሪው ገና ከመግባቱ ስድብና ዘለፋ ይገጥመዋል፡፡ ከእነኮማንደር በሚደርስ ቅድሚያ ፍረጃ አንዳንዶቹ ለቃል ከመግባታቸው ዱላ ጠብቋቸዋል፡፡ አብዛኛዎቹ ወጣቶች ብሄራቸውን ሲጠየቁ ‹‹ኢትዮጵያዊ›› በማለታቸው ዱላና ዱላ ቀረሽ ስድብና ዘለፋ ገጥሟቸዋል፡፡ አንዲት የሰማያዊ ፓርቲ አመራር ወጣት ከደህንነቶቹ በደረሰባት ድብደባና አስጸያፊ ዘለፋ እራት መብላት አልቻለችም፡፡የባሰው ደሞ ቅዳሜ መጋቢት 7 ቅስቀሳ ላይ እያሉ የታሰሩ ወጣቶች የደረሰባቸው ከፍተኛ ድብደባ ነው፡፡ ተክለሀይማኖት አካባቢ ታስረው የነበሩት መካከል አንደኛው ብሔሩን ‹‹ኢትዮጵያዊ›› በማለቱ ይመረምረው የነበረው ደኅንነት ከመደብደብ አልፎ በሽጉጥ አስፈራርቶ መረጃ እንደጠየቀው አውግቶኛል፡፡
ቃል ስንሰጥ ከተጠየቅናቸው ጥያቄዎች በተጨማሪ የኢሜልና የፌስ ቡክ አድራሻና የይለፍ ቃል በግድ ተቀብለውናል፡፡ ‹‹በምርመራው›› በ1997 ዓ/ም ማንን እንደመረጥን ተጠይቀናል፡፡ መልሱን ከመመለሳችን በፊት ደኅንነቶቹ ራሳቸው ቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ መምረጣችንን ያለ ጥርጥር እየነገሩ ‹‹አፍራሽነታችን›› የቆየ መሆኑን ለማስገንዘብ ሞክረዋል፡፡ ይህ ሁሉ የሚደረገው ለሕዝብ ይቆማል በሚባለው ፖሊስ ተቋም ግቢ ውስጥ ሲሆን ፖሊስ በደኅንነቶች የሚሰጠው ክብር ለታሳሪዎች ከሚሰጠው የሚለይ አይደለም፡፡

ተግባር ላይ መዋል ያልቻለው ሕገ መንግሥት አንቀጽ አንቀጽ 17(1) ‹‹ማንኛውም ሰው ጭካኔ ከተሞላበት፣ ኢሰብኣዊ ከሆነ ወይንም ክብሩን ከሚያዋርድ አያያዝ ወይንም ቅጣት የመጠበቅ መብት አለው›› ቢልም የሚፈጸመው ግን በተቃራኒው ነው፡፡ ስርዓቱ ለይስሙላህ ከሚጠቀምበት ሕገ-መንግሥት በተቃራኒ ‹‹በሕገ አራዊቱ›› እንደሚመራ በደንብ የተረዳሁት ለማሰላቸት ተብሎም ይሁን ለሌላ ዓላማ ከፖሊስ ጣቢያ ፖሊስ ጣቢያ ሲያዟዙሩን ካመሹ በኋላ ከለሌቱ አምስት ሰዓት ገደማ ቀጨኔ አካባቢ በሚገኘው ወረዳ 9 ፖሊስ ጣቢያ ከገባን በኋላ ነው፡፡ ከታሰርነንበት ጊዜ ጀምሮ በሆነ ባልሆነው በዚህ የወረዳ 9 ጣቢያ በተደጋጋሚ የታሰሩ የባለራዕይ ወጣት አመራሮች እንደተለመደው ለመቀጣጫ ወደዚሁ ጣቢያ ሊወስዱን እንደሚችሉ በእርግጠኝነት ይናገሩ ነበር፡፡ ማታ ላይ ሁላችንም ወደጣቢያው እንድንሄድ ተፈልጎ የነበረ ቢሆንም ቀድሞ በመሙላቱ የተወሰኑት ጃን ሜዳ አካባቢ ባለው የማዘዣ ጣቢያ እንዲያድሩ ተደርገዋል፡፡
በወረዳ 9 ሦስት በአራት የሆነች ጠባብ ክፍል ውስጥ እድሜያቸው 15 አመት የማይበልጥ ህጻናትን ጨምሮ 37 ሰው እንዲይዝ ተደርጓል፡፡ በእርግጥ ይህ ክፍል እስከ 50 ሰው የሚይዝበት አጋጣሚ እንዳለ ታሳሪዎቹ ነግረውኛል፡፡ በክፍሉ ወስጥ በተነጠፈው ቆሻሻ የወለል ምንጣፍ ላይ ሰው በሰው ላይ ተኝቷል፡፡ ሙቀቱ ከፍተኛ በመሆኑ ብዙዎቹ ራቁታቸውን ናቸው፡፡ አስተባባሪዎቹ ከፖሊስ ቦታ እንዲፈልጉልን በተላለፈላቸው ትዕዛዝ መሠረት በዚህ መተላለፊያ በሌለው ቤት ውስጥ ለመቀመጫ ያህል ቦታ ሰጡን፡፡ ታሳሪ ወጣቶቹም የያዝነውን ገንዘብ እንድናስረክባቸው ጠየቁን፡፡ ተከትሎም ሳንቲም ሳይቀር ያለንን ገንዘብ በሙሉ ተቀብለውናል፡፡ይህ ታዲያ እኛ ወጣቶቹ ላይ ብቻ ሳይሆን ከእድሜ የገፉትም ላይ ተግባራዊ የሆነ ውስጣዊ የታሳሪዎች ህግ መሆኑን ሰምተናል፡፡እንዳስተዋልኩት ከሆነ ይህ ቤት ሰው እንደሰው የማይቆጠርበት ዘግናኝ ቤት ነው፡፡ በዚህ ሰዎች እንደሰው በማይቆጠሩበት ቤት ውስጥ ሰው ሊማር የሚችለው ጭካኔን ብቻ ነው፡፡
እንደገባንም የገጠመኝ ይህ ነው፡፡ በግድግዳው ላይ የተጻፉት ጽሑፎችም የሚያሳዩት ጨካኝ በሆኑት ታሳሪዎች ላይ የሚደርስባቸውን በደል ነው፡፡ አብዛኛዎቹ ግድግዳው ላይ የተጻፉ ጽሑፎች እስረኞቹ ያለምንም ጥፋት መታሰራቸውን የሚገልጹ ናቸው፡፡ በተለይ ‹‹አገሬ ሆይ ወንድ አይወለድብሽ››፣ ‹‹በደልን ለማን ይነግሩታል››፣ ‹‹አይ ስቃይ››፣ ‹‹ገሃነብ ከመግባት በምን ይለያል››፣‹‹ሰው እንዴለለኝ›› የሚሉት ግድግዳው ላይ የተጻፉ ጽሑፎች የእስረኞችን ምሬት ቁልጭ አድርገው ያሳያሉ፡፡ በዚህ በደል የተሞላበት እስር ቤት የሚገኙት አብዛኛዎቹ ታሳሪዎች ከጨካኝነታቸው ባሻገር የአእምሮ ችግርና ተስፋ መቁረጥ የሚስተዋልባቸው ናቸው፡፡ በቀጨኔውና በሌሎቹ በተዘዋወርንባቸው ለሰው የማይመቹ እስር ቤቶች ውስጥ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት በተደጋጋሚ እንደሚታሰሩ በየግድግዳው የተጻፉት የተቃዋሚ ፓርቲዎች ስም ዝርዝር ምስክር ነው፡፡
በእነዚህ ጨካኝ ቤቶች የሚገኙ እስረኞች ከስርዓቱ እንደሚሻሉ ግን እየቆዩም ቢሆን አሳይተውናል፡፡ በምን እንደታሰርን በነገርናቸው ወቅት ለእኛ የነበራቸው አመለካከት ተቀየረ፡፡ ቀደም ብለው ተደራርበው ተኝተው የነበሩትን በማስነሳት ሰፋ ብሎ ለማስቀመጥ የሚያስችል ቦታን እንድንተኛበት አመቻቹልን፡፡ እስረኞች ጫማና ልብሳቸውን ጨብጠው ነው የሚተኙት፡፡ አልፎ አልፎ ዘመድ ያመጣላቸውን ምግብም ከልብስና ጫማቸው ጋር መደበቅ የግድ ይላቸዋል፡፡ አንድ እስረኛ ሊቀርብለት የሚገባውን ምግብ ባይቀርብልንም የታሰርንበትን ምክንያት ዘግይተው ያወቁት ያች ጠባብ ቤት ውስጥ የሚገኙ እስረኞች በርህራሄ ከጓደኞቻቸው የደበቁትንና ለራሳቸው የቆጠቡትን ቆሎና ጁስ ለእኛ አቅርበውልናል፡፡ በተለይ እነ ዶክተር ያቆብ በእስረኞች ዘንድ ይታወቁ ስለነበር በሌላኛው ክፍል ውስጥ መታሰራቸውን ስንነግራቸው በስርዓቱ ላይ ያማረሩት ብዙዎቹ ናቸው፡፡
ከአንገቱ በላይ ካለው የሰውነት ክፍሉ ውጭ ቀሪው ሰውነቱ ላይ ጓደኞቹ የተኙበት አንድ ወታደር ዶክተር ያቆብና ኢ/ር ይልቃል በቀጣዩ ክፍል መታሰራቸውን ሲሳማ ‹‹ይች ግፈኛ አገር!›› ብሎ እንደገና ተኛ፡፡ ሌላኛው አዛውንት ‹‹ምሁሮቿን ሞባይል ሰርቀው ከተያዙ ሕጻናት ጋር ወለል ላይ እንደዚህ የምታስር አገር የት ትገኛለች?›› ለሚል ጥያቄያቸው መልስ ሳይጠብቁ ‹‹የኢትዮጵያ ምሁራን ክብር ቦታና ፓስፖርት እንደልባቸው ከሚሰጣቸው የሶማሊያ ስደተኞች ያነሰ ሆነ፡፡ አገራችን የጠላት እንጂ የዜጎቿ መኖሪያ አልሆነችም፡፡›› ብለው ተናገሩ፡፡
በዚህ ክፍል ውስጥ የተሻለ ጥንቃቄ ሲደረግለት ያየሁት ሽንት የሚሸናበት የጀሪካን ቅዳጅ ብቻ ነው፡፡ ይህ ጀሪካን ማንም እንዳይጫነው ጥንቃቄ የሚደረግለት ብቸኛው ታሳሪ ነው፡፡ ይህንም የሚያደርጉት ተደራርበው የተኙት እስረኞች የሽንት ማጠራቀሚያውን በሀይል ሲገፉት አሊያም በእንቅልፍ ልባቸው ሲወጡበት በተደጋጋሚ እየተደፋ ቤቱ ስለሚበላሽ ነው፡፡ የሰው ትንፋሽ እና በየቦታው የሚጨሰው ሲጋራ የክፍሉ ሌላኛው አስከፊ ገጽታ ነው፡፡ አብዛኛው እስረኛ ቀን የተወሰነች ሰዓት ተኝቶ ለሌቱን ሌሎች እስረኞች እንዳይጫኑት እየተከላከለ ቁጭ ብሎ ያድራል፡፡ አንዱ በአንዱ ላይ ተደራርቦ ያደረው አብዛኛው እስረኛ በጠባቧ ግቢ ውስጥ ‹‹ሊዝናና›› ሲወጣ ቁጭ ብለው ያደሩት መተኛት ይጀምራሉ፡፡ ሆኖም በየደቂቃው በቆጠራና በሌላ ምክንያት እስረኞች ወደክፍል እንዲመለሱ ስለሚደረግ ሌሊት ከሚደርስባቸው ያልተለየ ችግር ያጋጥማቸዋል፡፡ አንድ ሰው ከፍ ያለ ድምጽ በማሰማቱ አሊያም የመውጫ ሰዓት ደርሶ ፖሊስ ውጣ ሳይለው ሊወጣ በመሞከሩ ክፍሉ እንደገና በቅጣት ተቆልፎ ቤቱ ወስጥ ያለው ሁሉም ሰው አብሮ ይቀጣል፡፡
ዝቅተኛ ካድሬዎች ከመቶ በላይ እስረኛ ከሚታጨቅበት የቀጨኔው እስር ቤት የተሻለ ስፋት ያለው የቀበሌ ቤት፣ ኮምዶሚኒየምና ቪላ ባለቤቶች ናቸው፡፡ ከፍ ያለ ስልጣን ያላቸው ፖለቲከኞች፣ ዘመዶቻቸው፣ የደኅንነት ኃላፊዎች፣ ወታደራዊ አመራሮችና የመሳሰሉት ደግሞ ከሚኖሩባቸው ዘመናዊ ቤቶች በተጨማሪ በሽዎች ብር የሚያከራዩትን ቤት በሕዝብ ገንዘብ ገንብተዋል፡፡ ለሥልጣኑ ሲል ሰዎችን ማሰቃየት አንዱ ስልት ነውና በህግ ጥፋተኝነታቸው ያልተረጋገጠ ታሳሪዎች ወለል ላይ እግራቸውን ዘርግተው የሚተኙበት እስር ቤት ለመገንባት ፍላጎት ያለው አይመስልም፡፡ልንቃወመው ወጥተን በስርዓቱ ድጋፍ ያገኘው የፋሽስት ስርዓት እንኳ በሞቃዲሾና ሮም ቁም ስቅል ያሳዩትን ወገኖቻችንን ያጉርበት የነበረው እስር ቤት አሁን አዲስ አበባ ውስጥ ከሚገኙት በተለየ ሰው በቅጡ ሊያስተኛ የሚችል እንደነበር ታሪክ ያስረዳል፡፡

ፖሊሶች ሕግ እንዲያውቁ አይደረግም፡፡ ሰላማዊ ሰልፉ ከመበተኑ ጀምሮ እስከተፈታንበት ጊዜ ድረስ ሰላማዊ ሰልፍ የመውጣት መብት በሕገመንግሥቱ መደንገጉን የሚያውቁ ፖሊሶች አላጋጠሙኝም፡፡ ሁሉም ይህ መብት ከፓርቲው የሚለገስ አድርገው የሚቆጥሩ ናቸው፡፡ ሕግ እንዳያውቁ ተደርገው እንጂ ለአገራቸው ሕዝብ የተለየ ጥላቻ ኖሯቸው እንዳልሆነ ግን ዓላማውና ሕጉ ሲገባቸው ከእኛ ጎን ቆመው አበረታትተውናል፡፡ በተለይ አመራሮቻቸው ከነገሯቸው በተቃራኒ በፖሊሶች ላይ ግርታ የተፈጠረው በአንድ የፖሊስ መኪና እንደ ሽንኩርት ከሰው ላይ ሰው ጭነው ወደ ጣቢያ ሲወስዱን በመደብደባቸው ይሸማቀቃሉ ተብለው የተገመቱት ወጣቶች፡-
‹‹ተከብረሽ የኖርሽው በአባቶቻችን ደም፣ በአባቶቻችን ደም፣
እናት ኢትዮጵያ የደፈረሽ ይውደም፣ ያስደፈረሽ ይውደም!››
እያሉ ሲጨፍሩ ነው፡፡ ሰባራ ባቡር አካባቢ በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ባረፍንበት ወቅት ሁሉም ሰው እስረኛ ሳይሆን ለሌላ ዓላማ የተገናኘ ያህል ልዩ ስሜት ውስጥ ነበር፡፡ ፖሊሶችንና ‹‹ኮማንደሩን›› ስለሕግ ያስረዳል፡፡ ስለአገሩ ድምፁን ከፍ አድርጎ ይዘምራል፡፡ ኢሕአዴግን ይተቻል፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን የታሰርነውን ለማየት ወደጣቢያው ለመግባት ሙከራ ሲያደርጉ ፖሊስ ሲያስመልሳቸው ሁሉም ለእርሳቸው ክብር ከመቆም በጭብጨባ ክብራቸውን ገለጸላቸው፡፡ በወጣቶቹ ላይ መሸማቀቅና የጥፋተኝነት መንፈስ መመልከት ያልቻሉት ፖሊሶች ይበልጡት ተደናገጡ፡፡ ‹‹ኮማንደሩ›› እና አንዳንድ አመራሮች ደግሞ በመናደዳቸው ጩኸታችንን እንድንቀንስ በተደጋጋሚ ወቀሳ ያደርሱብን ነበር፡፡ ይህን ባለመሳካቱም በቪዲዮ ቀረጻ ተጀመረ፡፡ በወቅቱ ግን ለማሸማቀቅ በሞከሩት አካላት ላይ ይበልጥ ያናደደና ፖሊሶቹ ከእኛው ጋር እንዲሆኑ ያደረገ ሁኔታ ተፈጠረ፡፡ በወቅቱ ከወጣቱ ተለይተው ተቀምጠው የነበሩት እነ ዶ/ር ያቆብ፣ ኢ/ር ይልቃል፣ አቶ ታዲዮስና ሌሎችም በመጨመራቸው ድምፃችን ከፍ ብሎ መሰማት ጀምሯል፡፡ ለማሸማቀቂያነት የታሰበው ቪዲዮ መቅረጽ ሲጀመርም፡፡
‹‹ተከብረሽ የኖርሽው በአባቶቻችን ደም፣ በአባቶቻችን ደም፣
እናት ኢትዮጵያ የደፈረሽ ይውደም፣ ያስደፈረሽ ይውደም!›› እንደገና ተዘመረ፡፡
እኛን ለመጠበቅና ለማስቀረጽ ፊት ለፊታችን መሳሪያና ዱላ ይዘው የተኮለኮሉት ፖሊሶች ከመገረም አልፈው በስሜት አብረውን ዘምረዋል፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ፖሊሶቹ የጠየቅናቸውን ነገር ለማቅረብ ቀናኢ ከመሆናቸውም በተጨማሪ ከተነገራቸው ባሻገር ሌላ አዎንታዊ ዓላማ ይዘን መነሳታችንን ማረጋገጥ የሚያስችላቸውን ጥያቄ በጓደኝነት መንፈስ ይጠይቁን ነበር፡፡ በኮማንደሩ ትዕዛዝ ከፖሊስ ጣቢያ ፖሊስ ጣቢያ ሲያንከራትቱንም ጠባቂ ፖሊሶች ያጅቡን የነበረው ያለ መሳሪያ ነበር፡፡ ስልኮቻችን በመያዛቸው ከቤተሰብ ጋር መገናኘት እንደምንችል በማወቃቸውም ባለ አንስተኛ ደሞዝተኞቹ ፖሊሶች በራሳቸው ጥያቄ ብዙ ሰው ወደቤተሰብ እንዲደውል ተባብረዋል፡፡ እንደኛ ጾማቸውን ውለው የእረፍት ጊዜያቸው ሲደርስ የተለዩን በጓደኛና ዘመድ ስሜት ነው፡፡

No comments:

Post a Comment