የሰሞኑ የጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ካቢኔያቸውን “ከኋላ” አስከትለው ከፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ያካሄዱት የፊት ለፊት ንግግር ያስደሰታቸውና ያስኮረፋቸው ክፍሎች አሉ። “በህወሃት መንደር ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ መድረክ የመወከል ባለጊዜው ህወሃት ነው። ህወሃት የኢትዮጵያ ምልክትና ተምሳሌት ነው” የሚሉት ወገኖች ቀደም ሲል ሲሰማ የነበረውን “የትግሬ ኩራት ተነክቷል” ስሜት በገሃድ ሲያንጸባርቁ ታይቷል።
አስገድደው ከሚመሩት ህዝብ ይልቅ ለውጪው ዓለም በመስገድና በማጎብደድ ወደር እንደሌላቸው የሚነገርረላቸው አቶ መለስ ሰሞኑን አቶ ሃይለማርያም ያገኙትን ዕድል አላገኙም። ከታላቋ አሜሪካ መሪ ጋር በግል የፊት ለፊት ወግ አላደረጉም። በተለያዩ መድረኮች ላይ በጅምላ ተገኝተው ከመጨባበጥና ውስን ቃላቶችን ሲለዋወጡ ከመታየቱ ውጪ ያላገኙትን ይህንን ዕድል አቶ ሃይለማርያም ማግኘታቸው ቅር ያሰኛቸው ክፍሎች “መለስ ከመሬት በታች ሆነው የዲፕሎማሲውን ስራ ሰርተው መድረኩን እንዳመቻቹ አስመስለው በተለያዩ መንገዶች መግለጻቸው የዚሁ የኩራታችን ተነካ ስሜት ነጸብራቅ ነው” የሚሉ ወገኖች አሉ።
ስብሰባው በኋይት ሃውስ እልፍኝ ወይም በተባበሩት መንግስታት ሳሎን ውስጥ አልነበረም የተካሄደው። ዓለምአቀፉ ሒልተን በሚያስተዳድረው የኒውዮርኩ ዋልዶርፍ አስቶሪያ ሆቴል አንድ ክፍል ውስጥ የአሜሪካ “ባንዲራ” እና የኢህአዴግ አርማ እንዲሰቀል ተደርጎ ንግግሩ መደረጉን ያወሱ ክፍሎች፣ ፕሬዚዳንት ኦባማ ምርጫ እየተቃረበ መሆኑንን ጠቁመው “የሲቪል ማኅበረሰቡ እንዴት መንቀሳቀስ እንዳለበት መታየት አለበት” በማለት ያነሱት ሃሳብ ከስብሰባው በላይ ሚዛን አንስቷል። ኢህአዴግ የመያዶች ህግ በሚል በማተም የዘጋውን የሲቪል ማኅበረሰቡን ተሳትፎ አስመልክቶ ኦባማ ማንሳታቸው ውሎ አድሮ የሚመነዘሩ ጉዳዮችን እንደሚያስነሳ አመላክቷል።
ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቴድሮስ አድሃኖም በፌስቡካቸው የለጠፉት የዚሁ የሆቴል ክፍል ስብሰባ በርካታ አስተያየት ተሰንዝሮበታል። “ቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስትር አንተ መሆን አለብህ” ከሚሉት የስጋና የደም አስተያየት ጀምሮ የዚሁ የፊት ለፊት ንግግር የቀድሞው “ባለ ራዕይ” መሪ “ራዕይ” ፍሬ አጎምርቶ የመታየቱ ብስራት ተደርጎ ተወስዷል፤ ታምኗል። ክብሩና ታሪኩም ለመለስ መቃብርና አጽም ህይወት ማላበሻ የአበባ ጉንጉን በረከት ሆኖላቸዋል።
የመለስ ሞት ዱብዳ የሆነበት ህወሃት፣ ከዱብዳው ማግስት ጀምሮ መርዶውን ሚስጥር ያደረገው የርዕሰ መንበሩ ወንበር ለይስሙላም ቢሆን እንዳይወሰድ አስፈላጊውን ዝግጅት ለማድረግ እንደሆነ በወቅቱ ብዙ የተባለበት ጉዳይ ነው። የመለስን የጥድፊያ ሞት “የግፍ ዋጋ፣ የአምላክ ቅጣት” በማለት ጮቤ የረገጡ ቢኖሩም፣ በህወሃት መንደር ግን ዜናው መሬት የተደረመሰ ያህል ስሜታቸውን ያራደ፣ ከሞት ጋር እልህ የተጋቡ የሚመስሉ፣ በዚሁ እሳቤ መለስ ቢሞቱም ያሉ ለማስመሰል የተደረገውና እየተደረገ ያለው ግብ ግብ “አምልኮ መለስ” ማስረጃ እንደሆነ ብዙዎች ተችተዋል።
ከዩኒቨርሲቲ የዲንነት በርጩማቸው ጀምሮ የሚያውቋቸው ሃይለማርያምን “የቆረጣ አካሄድን የተካነ” ሲሉ ይገልጹዋቸዋል። የሲዳማን ብሄረሰብ ለማስደሰት ከክልል ፕሬዚዳንትነታቸው ተነስተው አቶ መለስ ኢህአዴግ ቢሮ የተዛወሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም፣ በብሄር ውክልና ማመጣጠን ሰበብ ምክትል ጠ/ሚ ከመባላቸው ሌላ መለስ ቢሮ ለመጠጋት የሳቸው ሚና የለበትም። እንዳው አጋጣሚ ነው በሚል የሚከራከሩ ሃይለማርያም በኦባማ አስተዳደር ጫና ወንበሩን እንዲይዙ ከተደረገበት ጊዜ አንስቶ ህወሃቶች ውሳኔው “የትግሬዎችን ኩራት የነካ” መሆኑንን በመግለጻቸው በተደጋጋሚ መመከራቸውን ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ዲፕሎማቶች ይገልጻሉ።
ለጎልጉል ቅርብ የሆኑ የአሜሪካ ዲፕሎማት ሰሞኑን እንደጠቆሙት ህወሃቶች “በኩራታችን ተወሰደ” ስሜት ሃይለማርያም ደሳለኝን በቀጣዩ ምርጫ በራሳቸው ሰው ለመተካት እየሰሩ መሆናቸውን አመልክተዋል። በተለያዩ ሚዲያዎች ቴድሮስ አድሃኖም ቀጣዩ ጠ/ሚ/ር ይሆናሉ ስለመባሉ ለተጠየቁት “ቴድሮስ የግራውን መስመር የማያውቁ በመሆናቸው አምባገነን፣ ፈላጭ ቆራጭ መሪ ሊሆኑ አይችሉም፤ መስፈርቱን አያሟሉም በሚል ፈተናውን ሊያልፉ የማይችሉ ተደርገው ስለመወሰዳቸው መረጃው አለኝ” ብለዋል።
“የህወሃት የስለላው ማሽን” የሚባሉትና በፈላጭ ቆራጭነቱ አግባብ ግንባር ቀደም እንደሆኑ የሚነገርላቸው “ዶ/ር” ደብረጽዮን ሌላው እጩ ናቸው። ለመጀመሪያ ጊዜ ጎልጉል ስማቸውን ጠቅሶ ለጠ/ሚኒስትርነት ህወሃት ወደ ግንባር እያቀረባቸው መሆኑንን መግለጹ አይዘነጋም። የመረጃችን ምንጭ የሆኑት እኚሁ ዲፕሎማት፣ “ዶ/ር” ደብረጽዮን አምባገነንና ፈላጭ ቆራጭ በመሆን መስፈርቱን የሚያሟሉ ቢሆኑም ዓለምአቀፍ እውቅና የሌላቸውና ለዚያ የሚበቁ እንደማይሆኑ በራሳቸው በህወሃት ሰዎች መታመኑን ጠቁመዋል።
በቀጣዩ ምርጫ ህወሃቶች ዋናውን “የኢትዮጵያ ውክልና” የሚባለውን ወንበር መልሶ የመያዝ እቅድ እንዳላቸው በቂ መረጃ አሜሪካ እንዳላት የጠቆሙት ዲፕሎማት፣ ከህወሃት ቁልፍ ሰዎች መካከል ሃይለማርያም ደሳለኝ ምክንያት ተፈጥሮ በቀጣዩ ምርጫ እንዳይወዳደሩ የማድረግ ዕቅድ ስለመኖሩ መስማታቸውን ጠቁመዋል። “ለጊዜው መረጃው ጥሬ ነው” ሲሉም ዝርዝር ውስጥ ለመግባት እንደማይችሉ አመልክተዋል።
የመለስ ሞት ይፋ በሆነበት ቅጽበት አቶ ሃይለማርያምን ከህወሃት እውቅና ውጪ ያነገሱት በረከት ስምዖን “የወንበሩ የወቅቱ ባለንብረት ህወሃት ነው” በሚሉት ክፍሎች ጥርስ ተነክሶባቸው እንደነበር ምንጭ እየጠቀሱ በርካታ ሚዲያዎች መዘገባቸው አይዘነጋም። በመተካካት ከኢህአዴግ መንበር ይወገዳሉ ወይም ተወግደዋል የሚባሉት አንጋፋ የድርጅቱ መሪዎች ጥላቸውና እጃቸው መዋቅሩን ነክሶ በመያዙ አሁንም በቀጣዩ ምርጫ የሃይለማርያም ጉዳይ በነዚሁ ሰዎች እጅ እንደሆነ የሚጠቁሙ አሉ።
No comments:
Post a Comment