እንደምን አመሻችሁ!
በዚህች መላዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከቤተሰቦቹና ከወዳጆቹ ጋር ሆኖ አዲሱን አመት ለመቀበል በሚዘጋጅባት ምሽት በግንቦት 7 የፍትህ፤ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ስም እንኳን ለአዲሱ አመት በሠላም አደረሳችሁ ስል ከፍተኛ ክብርና ትልቅ ደስታ ይሰማኛል። መቼም በባህላችን ለሠላም ያለን ቦታ ከፍተኛ ስለሆነ አዲስ አመት በመጣ ቁጥር እንኳን በሠላም አደረሳችሁ እንባባላለን እንጂ ኢትዮጵያ ዉስጥ ሠላም ከጠፋ ብዙ አመታት ተቆጥረዋል።
ዉድ የአገሬ የኢትዮጵያ ሕዝብ-
እኛን ለመሰለ ከሁለት አስርተ አመታት በላይ በዘረኛ አምባገነኖች ለተረገጠ ሕዝብ የአዲስ አመት ዋዜማ አሮጌዉን አመት ሸኝተን አዲሱን የምንቀበልበት የሆታና የጭፈራ ምሽት ሆኖ ማለፍ የሚገባዉ አይመስለኝም። ይልቁንም በዚህ አሮጌዉን 2006ትን ተሰናብተን አዲሱን 2007ትን በምንቀበልበት ምሽት ባሳለፍነዉ የትግል አመት የገጠሙንን ችግሮችና መሰናክሎች መርምረንና ከድክመታችን ተምረን በ2007 ዓም ለምናደርገዉ ወሳኝ ትግል እራሳችንን ማዘጋጀት ያለብን ይመስለኛል።
እኛ ኢትዮጵያዉያን ረጂም የነጻነት ታሪክና በየዘመኑ የዘመቱብንን ወራሪዎች በተከታታይ ያሸነፍን የጥቁር ሕዝብ የነጻነትና የአልበገር ባይነት ተምሳሌቶች ነን። ያለፉት ሃያ ሦስት አመታት ታሪካችንን ስንመለከት ግን እነዚህ አመታት እፍኝ በማይሞሉ የአገር ዉስጥ ጠላቶቻችን ተሸንፈን ክብራችንንና ፈጣሪ ያደለንን ነጻነታችንን ተቀምተን የኖርንባቸዉ አሳፋሪ አመታት ናቸዉ። በ1983 ዓም አምባገነኑን ደርግ በትጥቅ ትግል ያስወገዱት የወያኔ መሪዎች እነሱ እራሳቸዉ ከደርግ የከፉ አምባገነኖች ሆነዉ አሁንም ድረስ አገራችን ኢትዮጵያን እየገዙ ይገኛሉ።
የወያኔ ስርዐት በየቀኑ በአገርና በሕዝብ ላይ የሚፈጽመዉን ግፍ፣ በደልና ሰቆቃ ስርዐቱን አምባገነን ነዉ ብሎ በመጥራት ብቻ መግለጽ የሚቻል አይመስለኝም። አገራችን ኢትዮጵያን ጨምሮ አለማችን ብዙ አምባገነን መንግስታትን አስተናግዳለች ዛሬም እያስተናገደች ነዉ። ወያኔ ግን እመራዋለሁ የሚለዉን ሕዝብና የሚመራዉን አገር በግልጽ የሚጠላ ከሌሎች አምባገኖች ለየት ያለ አምባገነን ነዉ። ወያኔ ሥልጣን ይዞ በቆየባቸዉ አመታት ሁሉ ኢትዮጵያዊነትን ሽንጡን ገትሮ ተዋግቷል፤ የኢትዮጵያን ደሃ ገበሬ አፈናቅሎ መሬቱን የኔ ለሚላቸዉ ታማኞቹና ለዉጭ አገር ቱጃሮች በርካሽ ዋጋ ሽጧል።ደቡብ ኢትዮጵያ ዉስጥ ለረጂም አመታት ከአካባቢዉ ሕዝብ ጋር ተግባብteዉ ይኖሩ የነበሩትን የአማራ ተወላጆች ይህ የእናንተ አገር አይደለም ብሎ ከገዛ አገራቸዉ ተፈናቅለዉ እንዲወጡ አድርጓል። በ 2005ና በ2006 ዓም በኦሮሚያ፤ በአማራ፤ በአፋርና በሶማሌ ክልሎች ከመሬታችን አታፈናቅሉን ብለዉ የመብት ጥያቄ ያነሱ አያሌ ሠላማዊ ዜጎችን በግፍ ጨፍጭፎ ገድሏል። ባጠቃላይ ወያኔ በዘር የተደራጀ፤ ሕዝብን በዘር የሚከፋፍልና የሚቃወመዉን ሁሉ በጅምላ እያሰረ በጅምላ የሚገድል ድርጅት ነዉ።
ይህም ሁሉ ሆኖ የወያኔ መሪዎች ከሕዝብና ከራሳቸዉ ጋር ታርቀዉ፤ በአገርና በሕዝብ ላይ የፈጸሙት ዝርፊያና ያደረሱት በደል በይቅርታ ታልፎ በኢትዮጵያ ዉስጥ እዉነተኛ ዲሞክራሲያዊ ስርዐት የሚገነባበትን መንገድ እንዲያመቻቹ የኢትዮጵያ ሕዝብ ተደጋጋሚ ዕድል ሰጥቷቸዉ ነበር። ለምሳሌ ከ1997ቱ ምርጫ በኋላ ተቃዋሚ ድርጅቶች የምርጫዉ ዉጤት እንደተጭበረበረ እያወቁ የወያኔ አገዛዝ አገሪቱን ለሚቀጥሉት አምስት አመታት ያለምንም ተቀናቃኝ እንዲመራና እነዚህን አምስት አመታት የተራራቀ ሕዝብን ለማቀራረብ፤ የዲሞክራሲ ተቋሞች መሠረት ለመጣልና አገራችን ዉስጥ መሪዎች በሀቀኛ ህዝባዊ ምርጫ ብቻ ወደ ስልጣን የሚመጡበትን መንገድ ለማመቻቸት እንዲጠቀምበት ዕድል ተሰጥቶት ነበር። ከዚህ በተጨማሪ ተቃዋሚ ድርጅቶች እራሳቸዉም በዚህ አገርን የማዳን ጥረት ዉስጥ ሙሉ በሙሉ ከወያኔ ጎን በአጋርነት እንደሚቆሙና እንደሚተባበሩት ቃል ገብተዉለት ነበር። ሆኖም የወያኔ መሪዎች አስተዋይነትን እንደ በታችነት፤ ትዕግስትን እንደ ፍርሃት መቻቻልን ደግሞ እንደ ሞኝነት በመቁጠር በወዳጅነት ላቀረብንላቸዉ የአገራችንን እናድን ጥሪ ምላሻቸዉ እስር፤ ግድያና ከአገር እንድንሰደድ ማድረግ ብቻ ነበር።
በአገራችን በኢትዮጵያ አንድነትና በህዝባቿ የወደፊት ዕድል ላይ የተደቀነዉ መጠነ ሰፊ አደጋ ከወዲሁ የታያቸዉ የተለያዩ ኢትዮጵያዉያን በተለያየ መልኩ ከወያኔ ጋር ብዙ እልህ አስጨራሽ ድርድሮችን አካሂደዋል። ከዚህም አልፈዉ የኢትዮጵያ አንድነት የሚረጋገጥበትንና ህዝበቿ ሠላም፤ ፍትህና እኩልነት በነገሱበት አገር የሚኖሩበትን መንገድ ለማመቻቸት ከወያኔ መሪዎች ጋር ረጂምና አድካሚ መንገዶችን ተጉዘዋል። ሆኖም አገራችንን ከዉድቀት ለማዳን እነዚህን ሁሉ ተደጋጋሚ ጥረቶች ስናደርግ የወያኔ መሪዎች በግልጽ የነገሩን ነገር ቢኖር ፍላጎታቸዉና የረጂም ግዜ ዕቅዳቸዉ የኢትዮጵያን ሕዝብ አዋርደዉ መግዛት እንጂ ፍትህ፤ ነጻነት፤ ዲሞክራሲና እኩልነት በፍጹም አጀንዳቸዉ እንዳልሆነ ነዉ። የወያኔ መሪዎች ዕብሪትና ማን አለብኝነት በዚህ ብቻም አላበቃም፤ የጫኑብንን የባርነት ቀንበር አሜን ብላችሁ ተቀበሉ፤ አለዚያም ድፍረቱ ካላችሁና እኛ የመጣንበትን መንገድ የምትችሉት ከሆነ “መንገዱን ጨርቅ ያድርግላችሁ” ብለዉ አሹፈዋል።
የወያኔ መሪዎች ከ1997ቱ ምርጫ የተማሩት ትምህርት ቢኖር ኢትዮጵያ ዉስጥ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ቢኖር እነሱና ፓርቲያቸዉ በፍጹም ወደ ሥልጣን እንደማይመጡና ኢትዮጵያንም እንዳሰኛቸዉ መዝረፍ እንደማይችሉ ነዉ። ሰለሆነም ከምርጫ 97 በኋላ በነበሩት ሦስትና አራት አመታት የወሰዷቸዉ እርምጃዎች በሙሉ ነጻ ምርጫ የሚፈልጋቸዉን ተቋሞች የሚያሽመደምዱና ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችን ባሰኛቸዉ ግዜ ሁሉ መወንጀል የሚያስችላቸዉ ህጎች ነበሩ ። ለምሳሌ የሜድያ ህግ፤ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ህግና የሽብርተኝነት ህግ የወያኔ መሪዎች የሚቃወማቸውንና ሀሳቡን በነጻነት የሚገልጸዉን ዜጋ ሁሉ ለመኮነን ያወጧቸዉ ህጎች ናቸዉ። እነዚህ ህጎች ከወጡ በኋላ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፤ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎቹ አንዱአለም አራጌና በቀለ ገርባ፤ ጋዜጠኛና መምህርት ርኢዮት አለሙና ሌሎችም ብዙ ሠላማዊ ዜጎች የግንቦት 7 አባላት ናችሁ በሚል ቃሊቲ ወርደዋል።
የወያኔ እስርና አፈና በአገር ዉስጥ ብቻ ተወስኖ አልቀረም። የወያኔ አገዝዝ ከሱዳን፤ ከኬንያና ከጂቡቲ መንግስታት ጋር በመመሳጠር አያሌ ኢትዮጵያዉያን ስደተኞችን ሽብርተኞች ናቸዉ እያለ አገር ቤት አስመጥቶ ሰቆቃ ፈጽሞባቸዋል። በመጨረሻም ባለፈዉ ሰኔ ወር አጋማሽ ዕብሪተኞቹ የወያኔ መሪዎች የንቅናቄያችንን ዋና ፀሐፊ አቶ አንዳርጋቸዉ ጽጌን ፍጹም ህገወጥ በሆነ መንገድ አግተዉ እስከዛሬ ድረስ እያሰቃዩት ነዉ። እኛ የወያኔን መሪዎች እስሩን፤ ግድያዉን፤ ዝርፊያዉንና የዘረኝነት ፖሊሲያችሁን አቁማችሁ አገራችን ዉስጥ ፍትህ፤ሠላምና እኩልነት የሰፈነበት ስርዐት አንገንባ ብለን ስንወተዉታቸዉ እነሱ ግን አፈናቸዉንና ዉንብድናቸዉን በስደት የምንኖርበት አገር ድረስ ይዘዉ በመምጣት ለሰላም የከፈትነዉን በር ዘግተዋል። በዚህም የወያኔ መሪዎች እነሱ እራሳቸዉ በመረጡልን የትግል ስልት ገጥመናቸዉ ከአገራችን ምድር ጠራርገን ከማስወጣት ዉጭ ሌላ አማራጭ እንዳይኖረን አድርገዋል።
ዉድ ኢትዮጵያዉያን ወገኖቼ!
የወያኔ አገዛዝ እኛን ኢትዮጵያዉያንን ያዋረደዉ አገር ዉስጥ ብቻ አይደለም። በዉጭ አገሮችም ባለቤትና ጠያቂ የሌለዉ ዜጋ አድርጎናል። በባዕድ አገሮች ጥቃት ሲደርስብን የራሱ ፓርቲ አባላት ወይም ደጋፊዎች ካልሆንን በዜግነታችን ምንም ነገር ለማድረግ ፈቃደኛ ሆኖ አያዉቅም። ዛሬ ከወያኔ ግፍና አፈና ለማምለጥ የሚሰደደዉ ኢትዮጵያዊ ከብዛቱ የተነሳ ቁጥሩ በዉል የሚታወቅ አይመስለኝም። የአፍሪካና የአረብ አገሮችን እስር ቤቶች የሞሉት ኢትዮጵያዉያን ስደተኞች ናቸዉ። ሴቶች እህቶቻችን አገር ዉስጥ የስራ ዕድል ስለማያገኙ በየአረብ አገሩ እየተሰደዱ የሚደርስባቸዉን ዉርደት በአፋችን ደፍረን መናገር ያቅተናል። ባለፈዉ አመት ከሳዑዲ አረቢያ ስንትና ስንት መከራና ፍዳ አይተዉ ወደ አገራቸዉ የተመለሱ ወገኖቻችን ሳዑዲ ይሻለናል እያሉ ለሁለተኛ ግዜ እየተሰደዱ ነዉ። ይህ ሁሉ የሚያሳየን ወያኔ የዛሬዋን ብቻ ሳይሆን የነገዋንም ኢትዮጵያ እገደለ መሆኑን ነዉ።
ዉድ የአገሬ የኢትዮጵያ ሕዝብ!
የወያኔ ዘረኞች ባለፉት ሃያ ሦስት አመታት ያደረሰብንን በደል፤ ዉርደት፤ ስደትና ስቃይ ላንተ የችግሩ ገፈት ቀማሽ ለሆንከዉ በዝርዝር መናገሩ የአዋጁን በጆሮ ነዉና አላደርገዉም፤ ሆኖም ይህ ስርዐት ምን ያክል ዘረኛ፤ ጨካኝና አረመኔ መሆኑን ማሳየት ስርዐቱን ንደን ለመጣል ለምናደርገዉ ወሳኝ ትግል ይጠቅማል ብዬ አጥብቄ ስለማምን ወያኔ ዛሬ በምንሰናበተዉ በ2006 ዓም ብቻ በሕዝብና በአገር ላይ የፈጸማቸዉን አንዳንድ ወንጀሎች መጥቀስ እፈልጋለሁ።
የወያኔ የጸጥታ ሃይሎች የእስልምና እምነት ተከታይ ወገኖቻችንን የአምልኮ ቦታቸዉ ድረስ ሰርገዉ በመግባት ለፈጣሪያቸዉ ፀሎት በማድረስ ላይ እንዳሉ በቆመጥ ደብድበዋል፤ አያሌ ምዕመናንን አስረዉ በሽብርተኝነት ከስሰዋle
ዉድ ወገኖቼ! እነዚህ የዘረዘርኳቸዉ ወንጀሎች በሕዝብ ተመረጥኩ የሚለዉ ወያኔ በ2006 ዓም ከፈጸመብን ወንጀሎች በጣም ጥቂቶቹ ናቸዉ። የዛሬዉ ቁም ነገሬ ግን ወያኔ የፈጸማቸዉ ወንጀሎች ብዛትና ማነስ ላይ ማተኮር አይደለም። የዛሬዉ ቁም ነገሬ እንደ ሕዝብና እንደ አገር ለምን በገዛ መሪዎቻችን ወንጀል ይፈጸምብናል – እኛስ እስከመቼ ነዉ ለጆሮ የሚሰቀጥጥ ወንጀል በየቀኑ ሲፈጸምብን ዝም ብለን የምናየዉ? የሚለዉ መሠረታዊ ጥያቄ ላይ ነዉ።
በዚህ ምድር ላይ በዳይና ተበዳይ፤ አሸናፊና ተሸናፊ ነበሩ ለወደፊትም ይኖራሉ። ሲበደል በደሉን አሜን ብሎ ተቀብሎና ሁሌም ተሸናፊ ሆኖ የሚኖር አገርና ሕዝብ ግን በፍጹም የለም። በዛሬዉ ምሽት የኛ የኢትዮጵያዉያን ጀግንነት ድንበር ጥሰዉ ሊወርሩን በሚመጡ ጠላቶቻችን ላይ ብቻ ሳይሆን በአገር በቀል ጠላቶችም ላይ መሆኑን በግልጽ ተነጋግረን መግባባት አለብን። ወያኔ ደግሞ አገር በቀል ጠላት ብቻ ሳይሆን ከወጭ ወራሪዎች ባልተናነሰ መንገድ የአገራችንን አንድነት የሚዋጋ ኃይል ነዉ። በ2007 ወጣቱ፤ ገበሬዉ፤ ሰራተኛዉና የመከላከያ ሠራዊቱ አባላት እጅ ለእጅ ተያይዘዉ ይህንን አገር በቀል ጠላት ማስወገድ አለባቸዉ ብሎ ግንቦት ሰባት በጽኑ ያምናል።
ግንቦት 7 የፍትህ፤ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ወያኔንና ወያኔ የገነባዉን ዘረኛ ስርዐት አስወግዶ ፍትህ፤እኩልነትና ዲሞክራሲን ለማስፈን በሚደረገዉ ህዝባዊ ትግል ዉስጥ ወጣቶች፤ ሴቶችና የመከላከያ ሠራዊት አባላት እጅግ በጣም ቁልፍ የሆነ ሚና ይጫወታሉ ብሎ ያምናል። ይህንን ደግሞ ወያኔም ስለሚረዳ ለዘረኝነት አላማዉ ከጎኑ ለማሰለፍ በጥቅማጥቅም የሚደልለዉና አለዚያም በሽብርተኝነት ፈርጆ እያሰረ የሚያንገላታዉ እነዚሁኑ ሦስት የህብረተሰብ ክፍሎች ነዉ።
የአገሬን ዳር ድንበር ከወራሪዎች እጠብቃለሁ ብለህ የመከላያ ሠራዊቱን የተቀላቀልክ የአገር መከላከያ ሠራዊት አባል ሆይ! አንተ የለበስከዉ ዪኒፎርም ጀርባህ ላይ ተቀድዶ ፀሐይና ብርድ ሲፈራረቁብህና የወለድካቸዉ ልጆችህና የወለዱህ እናትና አባትህ ደግሞ የሚላስና የሚቀመስ አጥተዉ በችግር አለንጋ ሲገረፉ፤ በየክልሉ እየሄድክ የገዛ ወገኖችህን እንድትገድል ትዕዛዝ የሚሰጡህ የወያኔ አለቆችህ ግን በኮንትሮባንድና በግልጽ የመሬት ዝርፍያ በዋና ዋና የአገራችን ከተሞች ከገነቧቸዉ ሰማይ ጠቀስ ህንፃዎች ዉጭ ካንተና ከሕዝብ የዘረፉት በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ትላልቆቹን የዉጭ አገር ባንኮች አጨናንቋል። አንተና ቤተሰቦችህ ነገ ምን እንሆናለን የሚል የችግር እንባ ስታነቡ ጥጋበኞቹ አለቆችህ ግን የጥጋብ ግሳት ያገሱብሃል።
ዉድ የአገሬ መካላከያ ሠራዊት አባል ሆይ!
ምትክ የሌላትን አንድ ህይወትህን ልትሰጣት ቃል በገባህላት አገር ዉስጥ እንዲህ አይነቱ የሚዘገንን በደል ባንተና በወገኖችህ ላይ ሲፈጸም ዝም ብለህ የምትመለከትበት ግዜ ማብቃት አለበት። መጪዉ አዲስ አመት ግንቦት 7 ለኢትዮጵያ ሕዝብ የገባዉን ቃል ተግባራዊ ማድረግ የሚጀምርበት አመት ነዉ። ይህንን መከላከያ ሠራዊቱን ጨምሮ መላዉን የኢትዮጵያ ሕዝብ ከወያኔ ባርነት ነጻ የሚያወጣ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ጀምረን ከወያኔ ጋር ትንቅንቅ ዉስጥ ስንገባ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ከታጠቁት መሳሪያ ጋር ወደምንገኝበት ቦታ ሁሉ እየመጡ እንዲላቀሉንና በምንም ሁኔታ የዘረኞችን ትዕዛዝ ተቀብለዉ በገዛ ወገኖቻቸዉ ላይ ክንዳቸዉን እንዳያነሱ በግንቦት 7 ንቅናቄ ስም አገራዊ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ!
ከእያንዳንዱ መቶ የአገራችን ሕዝብ ዉስጥ 64ቱ ዕድሜዉ ከ25 አመት በታች ነዉ፤ወያኔ እርስ በርሱ እንዳይገናኝ፤ አንዳይደራጅና በአገሩ ጉዳዮች ላይ እንዳይወያይ አፍኖ የያዘዉ ይህንኑ የአገራችን የወደፊት ተስፋ የሆነዉን ወጣት ነዉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ በሚገባ በእዉቀት ተኮትኩቶ ካደገ የወደፊቷን ኢትዮጵያ ተረክቦ አገሩን ከድህነትና ከኋላ ቀርነት ያላቅቃል ተብሎ ከፍተኛ ተስፋ የmiጣለበትም ይሄዉ ወጣት ነዉ። ሆኖም ባለፉት ሁለትና ሦስት ሳምንቶች በግልጽ እንዳየነዉ ወያኔ የአገሪቱን ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች የራሱን የከሰረ አስተሳሰብ ማስፋፊያና የፓርቲ አባላት መመልመያ ጣቢያ አድርጓቸዋል። በተለይ በአሁኑ ወቅት በእረፍት ላይ የሚገኙትን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለሥልጠና ካልመጣችሁ ወደ ትምህርት ገበታችሁ መመለስ አትችሉም ብሎ እያስፈራራ የተፈጥሮና የማህበራዊ ሳይንስ መማር ያለባቸዉን ተማሪዎች ተራ የካድሬ ስልጠና እየሰጣቸዉ ነዉ።
በየዘመኑ የተነሳዉ የኢትዮጵያ ወጣት አገሩን ከወራሪዎች በመከላከልም ሆነ የአገር ዉስጥ ፈላጭ ቆራጭ የገዢ መደቦችን ፊት ለፊት በመጋፈጥ የረጂም ዘመን አኩሪ ታሪክ ያለዉ ወጣት ነዉ። እኔ በኢትዮጵያ ወጣቶች ላይ ያለኝ እምነት እጅግ በጣም ከፍተኛ ነዉ፤ የዚህ ትዉልድ ወጣትም የወያኔን ዘረኞች የገቡበት ገብቶ አይቀጡ ቅጣት ቀጥቶ የእናት አገሩን አንድነትና የወገኖቹን ነጻነት ያስከብራል።
ዉድ የአገሬ ወጣቶች – መጪዉ አዲስ አመት እስከዛሬ ያጎነበሰዉን አንገታችንን ቀና አድርገንና ከዳር እስከ ዳር ተደራጅተን ወያኔን በህዝባዊ እምቢተኝነና በህዝባዊ አመጽ ከስልጣን ለማስወገድ ወደ ወሳኙ ፊልሚያ የምንገባበት አመት ነዉ። ወያኔ ስልጣን እንደያዘ በቆየ ቁጥር ከማንኛዉም የህብረተሰብ ክፍል በላይ ተስፋዉ የሚደበዝዘዉና የወደፊት ኑሮዉ የሚጨልመዉ ያንተ የወጣቱ ትዉልድ ነዉና ወያኔ ለራሱ ጥቅም የፈጠረልህን አደረጃጀት በመጠቀም ከምታምናቸዉ ጓደኞችህ ጋር ሆነህ እራስህን አደራጅ፤ የነጻነት ሃይሎች ለሕዝብ የሚያሰራጯቸዉን መረጃዎች በየቀኑ ተከታተል፤ የወያኔን ዕድሜ የሚያሳጥሩ እርምጃዎችንም በያለህበት አካባቢ መዉሰድ ጀምር። በዚህ መራራ ትግል ዉስጥ ያንተ የወጣቱ ትዉልድ ትልቁ ጉልበት መደራጀትህና በድርጅታዊ ዲሲፕሊን መታነጽህ ነዉና እነዚህ ሁለት እሴቶች ምን ግዜም እንዳይለዩህ።
ዉድ የአገሬ ወጣት!
ዛሬ ኢትዮጵያ ዉስጥ ስራ የሚያስገኘዉ ትምህርትና ችሎታ ሳይሆን የወያኔ ድርጅቶች አባል መሆን ነዉ፤ እሱ ደግሞ እራስን መሸጥ ነዉና ኢትዮጵያዊ ስለሆንክ ብቻ እንደማታደርገዉ እርግጠኛ ነኝ። ያለ የሌለ ጥሪትህን አፍስሰህ ንግድ ልጀምር ብትልም መንገዱን ይዘጉብሃል ወይም አብዛኛዉን ትርፍህን ለወያኔ ሙሰኞች ካልገበርክ መነገድ አትችልም ይሉሀል። እneዚህን የጠቀስኳቸዉን ሁለት ፍትህ አልባ አሰራሮች ተቃዉመህ አደባባይ ስትወጣ ደግሞ የአግዓዚ አልሞ ተኳሾች ደረት ደረትህን ይሉሀል። ከዚህ ሁሉ ዉጣ ዉረድ በኋለ ያለህ አማራጭ ወይ ለወያኔ ዘረኞች እየሰገድክ መኖር አለዚያም እናት አገርህን ጥለህ መሰደድ ነዉ። እስከዛሬ የተንገላታኸዉ፤ የታሰርከዉ፤ የተገረፍከዉና የጥይት እራት የሆንከዉ ዉድ የአገሬ ወጣት ሆይ – በዚህ አዲስ አመት ዋዜማ ግንቦት 7 ላንተ፤ ለቤተሰቦችህና ለአገርህ የሚበጅ ሦስተኛ አማራጭ ይዞልህ መጥቷል። ከአገርህ አትሰደድም፤ ለወያኔ ዘረኞችም እየሰገድክ አትኖርም ! ወያኔን ፊት ለፊት ተጋፍጠህ አንተንም ወገኖችህንም ነጻ ታወጣለህ። ገና ዋና ዋና ስራዉን ሳይጀምር መኖሩን በማሳወቁ ብቻ ወያኔን ያርበደበደዉ የሕዝባዊ አመጽ ኃይል ዬት እንዳለ ታዉቃለህና በትናንሽ ቡድኖች እራስህን እያደራጀህ ዛሬ ነገ ሳትል ናና ተቀላቀለን። ለግዜዉ ወደ ጫካዉና ወደ ዱሩ መጥተህ መቀላቀል የማትችለዉ ደግሞ ወያኔን በዝቅተኛ ወጪ በፍጥነት ማስወገድ የምንችለዉ ከዉስጥም ከወጭም ስናጣድፈዉ ነዉና የነጻነት ኃይሎች በተከታታይ የሚሰጡህን መረጃ በመከተል እራስህን አደራጅተህ በየአካባቢህ የወያኔ ስርዐት የቆመባቸዉን መሠረቶች አፍርስ።
ውድ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ!
የአዲስ አመት ዋዜማ እንደ ግለሰብ በአሮጌዉ አመት በዕቅድ ይዘን ያላከናወንናቸዉን ቁም ነገሮች በአዲሱ አመት ለማከናወን ለራሳችን ቃል የምንገባበት፤ እንደ መሪ ደግሞ ለሕዝብና ለአገር አዲስ ራዕይና አዲስ ተስፋ የምንፈነጥቅበት፤ ከስህተታችን የምንታረምበትና ጠንካራ ጎናችንን ይበልጥ የምናጎለብትበት መልካም አጋጣሚ ነዉ። በዚህ አዲስ አመት ከሃያ ሦስት አመት ስህተታቸዉ ታርመዉና የበደሉትን የኢትዮጵያ ሕዝብ ይቅርታ ጠይቀዉ የፍትህና የነጻነት ትግላችንን አንዲቀላቀሉ የትግል ጥሪ የምናደርግላቸዉ ብዙ ድርጅቶች አሉ። ከእነዚህ ዉስጥ አንዱና ዋነኛዉ አራት ድርጅቶችን ያቀፈዉ ኢህአዴግ የሚባለዉ ድርጅት ነዉ። ወገናችንን እንጠቅማለን ብላችሁም ሆነ በሌላ ሌላ ምክንያት ከጠላታችሁ ከወያኔ ጋር የተቆራኛችሁ የኦህዴድ፤ የባዕዴንና የደኢህዴግ አባላትና መሪዎች ሁሉ በዚህች የአዲስ አመት ዋዜማ ምሽት የበደላችሁትን የኢትዮጵያን ሕዝብ የምትክሱበት መልካም አጋጣሚ መፈጠሩን ሳብስርላችሁ እጅግ በጣም ደስ እያለኝ ነዉ። ልቦና ያላቸዉ ወገኖች በህወሓትም ዉስጥ ይኖራሉ ብለን እናምናለን። ህወሓትን ለቆ ለመዉጣትም የመጨረሻዉ ሰዐት ደርሷልና አሁኑኑ እየለቀቃችሁ ዉጡ። ለአገራቸዉ አንድነትና ዲሞክራሲያዊ እኩልነት የሚታገሉት የደሚሂት ወንድሞቻችን ከሌሎች ወገኖች ጋር አብረዉ እየታገሉ ነዉ። ለሀቅና ለእኩልነት ብለህ ወያኔን የተቀላቀልክ ታጋይ በሙስና የተጨማለቁ ወራዳ መሪዎች ጀሌ መሆንህ ማብቃት አለበት።
በኢህአዴግና በሌሎቹም የወያኔ አጋር ድርጅቶች ዉስጥ የምትገኙ ዉድ ኢትዮጵያዉያን ወገኖቼ – እስከ ዛሬ እራሱን “የትግራይ ሕዝብ ነጸ አዉጭ ግንባር” እያለ የሚጠራዉ ድርጅት ጥቂት ዘራፊ መሪዎች የኢትዮጵያን ሕዝብ ከሃያ አመታት በላይ ረግጦ መግዛት የቻለዉ በቅርጹ ኢትዮጵያዊ በይዘቱ ግን ፍጹም ፀረ ኢትዮጵያ የሆነ ድርጅት ፈጥሮ መንቀሳቀስ በመቻሉ ነዉ። “የአገሩን ሠርዶ በአገሩ በሬ” እንደሚባለዉ ወያኔ “ኢህአዴግ” በሚል ሽፋን የኦሮሚያን፤ የአማራንና የደቡብ ሕዝብ ክልሎችን ተቆጣጥሮ አገራችንን መዝረፍ ባይችል ኖሮ የኢትዮጵያን ሕዝብ እንኳን ሃያ ሦስት አመት አንድ ወርም ተደላድሎ መግዛት አይችልም ነበር። ስለዚህ ከዚህ የሕዝብና የአገር አንድነት ጠላት ከሆነዉ ድርጅት እራሳችሁን እያገለላችሁ ህዝባዊ ትግሉን እንድትቀላቀሉና የኢትዮጵያን ሕዝብ ለማይቀረዉ ድል እንድታበቁት በዚህ ጀግና ሕዝብ ስም እማፀናችኋለሁ።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ! ታታሪ ሠራተኛ ሕዝብና ለሌሎች የሚተርፍ ለምለም አገር ይዘን ዛሬም ስማችን የሚጠቀሰዉ ከድህነት፤ ከኋላ ቀርነትና ከሰብዓዊ መብት ረጋጮች ተርታ ነዉ። ወያኔ ገነባሁ ብሎ የሚነግረን የኃይል ማመንጪያ ግድቦች ብዛት እንኳን ለኛ ለጎረቤቶቻችንም የሚተርፉ ናቸዉ። ነገር ግን አብዛኛዉ የከተማ ነዋሪ በሳምንት ከአንድ ግዜ በላይ መሠረታዊ የመብራት አገልግሎት አያገኝም፤ እራሱን ልማታዊ መንግስት እያለ የሚጠራዉ ወያኔ የአገሪቱ ኤኮኖሚ በድርብ አኀዝ እያደገ ነዉ ማለት ከጀመረ አስር አመታት ተቆጥረዋል፤ ሆኖም የአገራችንና የአፍሪካ መዲና የሆነችዉና ወደ አራት ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ የሚኖርባት አዲስ አበባ የዉኃ ያለህ እያለች መጮህ ከጀመረች አመታት ተቆጥረዋል። የወያኔ መሪዎች ይህንን ግዙፍ ማህበረሰባዊ ችግር እያወቁ ችግሩን ለመቅረፍም ሆነ በየቀኑ እያደገ ለሚሄደዉ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የመጠጥ ዉኃ ዘላቂ ዋስትና ለመስጠት የሰሩት ወይም ያቀዱት ምንም ነገር የለም።
ወያኔ የተከተላቸዉ ብልሹ የኤኮኖሚ ፖሊሲዎች አገራችን ዉስጥ የሸቀጥ ዋጋ በየቀኑ እንዲያድግ አድርጓል። ይህ የዋጋ ንረት የፈጠረዉ የኑሮ ዉድነት ደግሞ ወላጆች ልጆቻቸዉን በፈረቃ እንዲመግቡ ከማስገደዱም በላይ በአዲስ አበባና በሌሎቹም ከተሞቻችን ለወትሮዉ የፍቅርና የመቀራረብ ምልክት የነበረዉ ጉርሻ ዛሬ በችርቻሮ የሚሸጥ ሸቀጥ ሆኗል። ኢትዮጵያ ዉስጥ ዕንቁጣጣሽ የሚከበረዉ ቅርጫዉ፤ በጉና ዶሮዉ ተገዝቶ ከቤተሰብና ከወዳጅ ዘመድ ጋር አንድ ላይ በመሆን ነበር፤ ዛሬ ግን የኑሮ ዉድነቱና የዋጋ ንረቱ የኢትዮጵያ ሕዝብ ትላልቅ አመት በአሎቹን ከባህሉና ከወጉ ዉጭ በባዶ ቤት ለብቻዉ እንዲያከብር አስገድዶታል።
ግብር ከፋዩ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህ ሁሉ ችግርና መከራ እየተፈራረቀበት የወያኔ ሹማምንትና ምስለኔዎቻቸዉ ግን በፎቅ ላይ ፎቅ ይሰራሉ፤ የቅንጦት መኪና በየአመቱ ይቀያይራሉ ወይም ቅምጥል ልጆቻቸዉን በሕዝብ ገንዘብ አዉሮፓና አሜሪካ እየላኩ ያስተምራሉ። የኢትዮጵያ ሕዝብ በቀላሉ ሊወገዱ በሚችሉ በሽታዎች አንደ ቅጠል እየረገፈ እነሱና ቤተሰቦቻቸዉ ግን ጉንፋን በያዛቸዉ ቁጥር በሕዝብና በአገር ገንዘብ አዉሮፓና አሜሪካ እየሄዱ ይታከማሉ። ይህ ሁሉ በሕዝብ ላይ የሚያደርሱት በደል አልበቃ ብሏቸዉ በየከተማዉ ቤቶችን እያፈረሱ መሬቱን እነሱ ለሚፈልጉት ባለኃብት ይሸጣሉ። ዉድ የአገሬ ሕዝብ – ለመሆኑ እስከመቼ ነዉ በገዛ አገራችን እፍኝ በማይሞሉ ሰዎች እንደዚህ እየተዋረድን የምንኖረዉ? እስከመቼ ነዉ እነሱ ልጆቻችንን እየገደሉ እኛ እየቀበርን የምንኖረዉ? እስከመቼ ነዉ ግብር ከፋዩ የኢትዮጵያ ሕዝብ ደሞዝ በሚከፍላቸዉ ሰራተኞቹ እየተናቀ፤ እየተዋረደ፤ እየታሰረ፤ እየተገደለና ከአገሩ እየተሰደደ የሚኖረዉ? ለመሆኑ ኢትዮጵያ የነማን አገር ናት? እኛስ የነማን ልጆች ነን?
ዉድ አባቶቼ፤ እናቶቼ፤ እህቶቼና ወንድሞቼ -
እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ለእነዚህ ጥያቄዎች ተገቢዉን ምላሽ የሚሰጥበት ወሳኝ የትግል ምዕራፍ ፊት ለፊታችን ተደቅኗል። 2007 እንደሌሎቹ አመቶች “ዕንቁጣጣሽ በያመቱ ያምጣሽ” ብለን ተቀብለን የምንሸኘዉ አመት አይሆንም፤ መሆንም የለበትም። ነገ የምንቀበለዉ አዲስ አመት ሲገድሉን ዝም ብለን የማንሞት፤ ሲያሳድዱን አገራችንን ትተንላቸዉ የማንሰደድ፤ ሲንቁንና ሲያዋርዱን ደግሞ ክብር፤ ልዕልናና የረጂም ግዜ ታሪክ ያለን ታላቅ ሕዝብ መሆናችንን ለጠላትም ለወዳጅም የምናረጋግጥበት አመት ነዉ። ይህ አመት የአገራችንን የፍትህ፤ የደህንነትና የመከላከያ ተቋሞች እንደ ማጥቂያ መሳሪያ እየተጠቀመ ሲያስረን፤ ሲያዋርደንና ሲገድለን የከረመዉን ዘረኛ አገዛዝ ለማስወገድ ተግባራዊ እርምጃዎችን መዉሰድ የምንጀምርበት የድልና የመስዋዕትነት አመት ነዉ። ይህ አመት እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ከወያኔ ጋር በሚደረገዉ የነጻነት ትግል ዉስጥ የኔ ድርሻ ምንድነዉ የሚለዉን ጥያቄ እራሱን ጠይቆ መልሱንም እሱ እራሱ የሚመልስበት አመት ነዉ። ነጻና ፍትሃዊ በሆነችዉ ኢትዮጵያ የሚጠቀመዉ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደሆነ ሁሉ ኢትዮጵያን ነጻና የእኩሎች አገር ለማድረግ በሚደረገዉ ትግልም እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ አለበት።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ!
ወያኔዎችን በድርድር ሞከርናቸዉ፤ በምርጫ ሞከርናቸዉ በሠላማዊ መንገድም በሁሉም አቅጣጫ ሞከርናቸዉ፤ ለእነዚህ ሁሉ ሙከራዎቻችን የሰጡን ምላሽ አርፋችሁ ተገዙ፤ ትታሰራላችሁ ወይም ኢትዮጵያን ለቅቃችሁ ዉጡ የሚል የዕብሪትና የንቀት መልስ ነዉ። ግንቦት 7 የፍትህ፤ የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ከሎሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን አንገዛም፤ ከህግ ዉጭ አንታሰርም፤ አገራችንንም ለቅቀን አንወጣም የሚል ጽኑ አላማ አንግቦ ታግሎ ሊያታግላችሁ ዝግጅቱን አጠናቅቆ ኑና ተቀላቀሉኝ እያለ ነዉ ። ንቅናቄያችን የኢትዮጵያን አንድነት፤ ሠላምና ብልጽግና ለማረጋገጥ የወያኔ ስርዐት መወገድ አለበት ብሎ ያምናል፤ ይህ እምነታችን፤ ለእናት አገራችን ኢትዮጵያ ያለን ፍቅርና፤ የነጻነት ጥማታችን ወደትግሉ ሜዳ እንድንገባ አድርጎናል። ይህ ትግል ወያኔን ለማስወገድ ብቻ የሚደረግ ትግል ሳይሆን የተረጋጋ፤ ጤናማና በዲሞክራሲ መሠረቶች ላይ የቆመ አስተማማኝ የፖለቲካ ስርዐት ለመፍጠርም ጭምር የሚደረግ ትግል ነዉ።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ!
ማለት የሚገባንን ሁሉ ብለን ጨርሰናል፤ ካሁን በኋላ ማድረግ የሚገባንን ሁሉ ማድረግ አለብን። ሁለገብ ትግሉ ተጀምሯል። ይህ አመት የትግል አመት ነዉ፤ ይህ አመት የመስዋዕትነት አመት ነዉ፤ ይህ አመት ድል የምናሸትበት አመት ነዉ። ይህ ትግል የገበሬዉን፤ የሠራተኛዉን፤ የወጣቱን፤ የሴቶች እህቶቻችንና የመከላከያ ሠራዊቱን የቀን ከቀን ተሳትፎና መስዋዕትነት ይጠይቃል። እኔም የትግሉን ወደ አዲስና ወሳኝ ምዕራፍ መድረስ እያበሰርኩ ኑና ለክብራችንና ለነጻነታችን እንታገል የሚል የትግል ጥሪ ለእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አስተላልፋለሁ።
የጀመርነዉን ትግል በድል እንደምንወጣዉ ጥርጥር የለኝም !!!!
መልካም አዲስ አመት -
ደህና እደሩ
No comments:
Post a Comment