ያለሁበት የመን ውስጥ የማይሰማ አይነት ስደተኞች ላይ የሚደርስ ስቃይ የለም፡፡ የስቃይ አይነቱ ተቆጥሮ የማያልቅ ነው፡፡ኢትዮጵያዊን ስደተኞች ከጅቡቲ ቀይ ባህር እና ከሶማሊያ ህንድ ውቅያኖስን ተሻግረው ወደ የመን ይገባሉ፡፡ ግባቸው ግን የመን በመድረስ የሚገታ አይደለም፡፡ ይቀጥላሉ፡፡ አላማቸው የተስፋይቱ ምድር ናት የተባለ ይመስል ሳዑዲ አረቢያን ያነጣጠረ ነው፡፡ ሳዑዲ እጇን ዘርግታ በሳቅ አትቀበላቸውም፡፡ ኮርኩማ ኮርኩማ አንገላታ…ከሞት መንጋ ታግለው፤ ከአጋቾች አምልጠው ወይም ክፈሉ የተባሉትን ብዙ ሺህ የሳዑዲ ሪያል ከፍለው…በጣም ሰቅጣጭ በረሃ በእግር ያቋርጣሉ፡፡ እዚህ በርሃ ላይ በርሃብ ወድቆ መቅረት በውሃ ጥም ነዶ አፈር አልባሽ አጥቶ የትም መውድቅ (የሞተ ሞቶ ማለፍ) የተለመደ ነው፡፡ በየመንገዱም የኢትዮጵያዊን ሬሳ ወድቆ ማየት ለየመናዊያኑ አዲስ አይደለም፡፡
ኢትዮጵያዊያኑ ከየመናዊን ጋር በመቀናጀት ስደተኛውን እያፈኑ በማሰቃየት ከቤተሰብ፣ ወዳጅ ዘመድ ገንዘብ አስልኩ ብለው ጉዳት ያደርሳሉ፡፡ በእሳት ማቃጠል፣ አካል ማጉደል፣ ብልት መቁረጥ…የመሳሰሉትን ይፈጽማሉ፡፡ ስደተኞቹ ይህን ማለፍ በቻሉት መንገድ ካለፉ በኋላ ነው ሳዑዲ አረቢያ ለመሄድ ከ 120 ኪሎ ሜትር በላይ ጭልጥ ያለ ውሃና ምግብ የማይገኝበት በረሃ የሚያቋርጡት፡፡ ድንበር ላይም ሆነ ድንበር ካለፉ በኋላ ሲያዙ ወደ ኢትዮጵያ ይመለሳሉ (ይጠረዛሉ)፡፡ መልሰው ዞረው ይመጣሉ፡፡ ለምን? ሁሌም መልስ ፍለጋ እታትራለሁ፡፡ የቻልኩትንም ያህል ጥናት ለማድረግ ሞክሬያለሁ፡፡ ችግሩ አስቸጋሪ እና ውስብስብ ነው፡፡ ዘርፈ ብዙ ነው፡፡ ድምዳሜ መስጠት ይከብዳል፡፡
ምሳሌ ላንሳ….የዛሬ ሁለት አመት አካባቢ ፈድሉ የተባለ ልጅ ሰነዓ ኢሚግሬሽን እስር ቤት አገኘሁት፡፡ ግንባሩ ተፈንክቷል፡፡ ቀላል የሚባል አይነት አይደለም፡፡ ግምስ ነው ያደረጉት፡፡ ‹‹ምን ሆነህ ነው?..›› ስል ጥያቄዬን እንደዋዛ አቀረብኩለት፡፡ እንደዋዛ ልጠይቀው እንጂ መልሱን በጉጉት እየጠበኩ ነበር፡፡
‹‹…ሀረድ የአብዱል ገዊ ሰዎች ናቸው እንደዚህ ያደረጉኝ፡፡ ወንድሜን ደግሞ አይኔ እያየ ገደሉት፡፡..›› አይኑን ጨመቅ አደረገው፡፡ ማዘኑን ለመግለጽ ነው፡፡ መከራና ስቃይ አደድሮታል ከየት ይምጣ እንባው..የእኔ ግን ውድድር ይመስል ቀድሞ ጠብ አለ፡፡ አብረውኝ የነበሩት ምግብና ልባሽ አልባሳት እንዲያድሉልኝ ይዣቸው የሄድኩት እነ ካልድ ለገሰ እና ሄኖክ በእንባዬ ተደናገጡ፡፡ የከፋ ነገር እንደሰማሁ ገምተው ሊያጽናኑኝ መጡ፡፡ እነሱ የያዝነውን እቃ ማደሉን እንዲቀጥሉ አድርጌ ሞባይል ስልኬን አወጣሁ፡፡ ፈድሉ ለካ እንባው ይድረቅ እንጂ ውስጡ ትክን ብሎ አሮ ነበር፡፡ ‹‹እህ!…›› ብሎ ቃጠሎውን ሲተነፍሰው እንባው ተንዠቀዠቀ፡፡ ‹‹አለመታደል አልኩ በውስጤ፡፡ ሙሉውን ታሪክ እንዲነግረኝ ለመንኩት፡፡ በተንቀሳቃሽ ስልክ መቀዳቱን ባይፈቅድም በህሊናዬ ማህደር ሊረሳ የማይችል በሀዘን የሚያርመጠምጥ ታሪክ አወጋኝ፡፡
ከሀገር ሲነሱ ሁለት ወንድማማቾች ሆነው ነበር፡፡ ማንኛውም ስደተኛ እንደሚሆነው ማየት ያለባቸውን ስቃይ ሁሉ እያዩ ጅቡቲ ደረሱ፡፡ የባህሩን ጉዞ በአራት ሰዓት ውስጥ አጠናቀው የየመንን መሬት ሲረግጡ መኪና የያዙ አጋቾች ናቸው የተቀበሏቸው፡፡ ሌሎች አፋኝ ግሩፖችም ስለነበሩ እነዚህን ለእኛ እነዚህን ለእኛ በመባባል ባለቤት እንደሌለው ከብት ተሻምተው ወሰዷቸው፡፡
ከዚህ በኋላ ያለውን ነው ፈድሉ በእንባ እየታጀበ ምንም ያህል ሊነግረኝ ያልቻለው፡፡ ለበርካታ ጊዜ በእንባ ያቋርጥ ነበር፡፡ቢሆንም አቆራርጦ በነገረኝ ታሪክ… በመኪና ጭነው ወደ 4 ኪሎ ሜትር አካባቢ እንደወሰዷቸው ከአንድ የሞት ክልል ከሚመስል የሚያስፈራ ጊቢ ውስጥ ከተቷቸው፡፡ አጋቾቹ ሁሉም መሳሪያ የታጠቁ ናቸው፡፡ ሁሉም ልብሳቸውን እንዲያወልቁ ታዘዙ፡፡ ፍተሻው ተጀመረ፡፡ አፈታተሻቸው ቅጥ ያጣ እና ብልግና የታከለበት ነበር፡፡
‹‹…42 ነበርን ሶስቱ ሴቶች ናቸው፡፡ ሁላችንንም ራቁታችንን አስደረጉን፡፡ ፊታችሁን ወደ ግድግዳው አዙሩ ብለው ከኋላ እያዩን ራሳቸውን በራሳቸው ያረካሉ፡፡ አንደኛው መጥቶ መቀመጫችንን በእጁ ጨበጥ ጨበጥ እያደረገ ይለካ ይሁን ራሱን እያረካ እንጃ ብቻ ወንድሜ ጅላሎ መቀመጫውን ዳሰስ ሲያደርገው ፍንጥር ብሎ አትንካኝ አለ፡፡
‹‹ሳቁበት ተሳለቁበት፡፡
‹‹እሱ ደግሞ አረቢኛ በደንብ ይሰማል፡፡ ጎትተው ከመካከላችን ወሰዱት፡፡ የተለየ ክፍልም አስገቡት፡፡ የጣር ጩኸቱ ይሰማናል ግን ወንድሜን ም እያደረጉት እንደሆነ ለማወቅ ግራ ተጋባሁ፤ ተጨነኩም፡፡ እደበደቡትም መሰለኝ፡፡ ከብዙ የጣር ጩኸት በኋላ ጎትተው አውጥተው ጣሉት፡፡ ነፍሱን አያውቅም ሮጬ ላነሳው ስል እኔን በዱላ መታኝ፡፡ ወደኩ ከዛ በኋላ የሆነውን አላውቅም፡፡ ወንድሜን ለካ ደፍረውት ነው፡፡ ስቃዩ በዚህ አላበቃም ስልክ ቁጥር ያላችሁን አምጡ ይደወል እና ገንዘብ ለሚልክላችሁ ሰው መልዕክት አስተላልፉ አሉ፡፡ የምንደውልበት ስልክ ቁጥር የለንም ነበረ፡፡ ከዛ መዐቱ መጣ….በዚህም ጊዜ ለሌሎቹ መቀጣጫ እንዲሁን ብለው በሞት ቋፍ ላይ ያለውን ጅላሎን ሰቀሉት፡፡ ፍርግጥ ፍርግጥ ብሎ ነፍሱ ልትወጣ ሲያጣጥር ገመዱን ፈተው አወረዱት፡፡ እንደታረደ በሬ ተንደፋደፈ ተሰቃይቶ ተሰቃይቶ ህይወቱ አለፈች፡፡ በዛ ላይ በጣር እንኳን እያለ በብልቱ ሲጫወቱበት ነበር፡፡ ከሞተ በኋላ ብልቱን ይዘው……….
‹‹በቃ!!!!!!!!!!!…›› ብዬ አስቆምኩት፡፡
ህሊናዬን ልስት የደረስኩ ነው የመሰለኝ፡፡ አዞረኝና ከአንዱ እስረኛ የያዘውን ውሃ ተቀብዬ ተጎነጨሁ፣ አናቴ ላይም አፈሰስኩ፡፡….የሁለታችንም አይኖች እንባ ማዝነባቸውን ስለተያያዙት የእስር ቤቱ ፖሊስ ጠጋ ብሎ ‹‹ኤሽ ፊ!›› ብሎ ችግር መኖሩን እና አለመኖሩን ጠየቀን፡፡ ምን ልበለው ‹‹ማፊ ሙሽክላ..›› ብዬ መለስኩለት፡፡ ለካ በቃ!… ስለው ሳላስበው ጮኬ ነበርና ነው ፖሊሱ የመጣው፡፡ ነጠብጣብ አድርጌ ያለፍኩትና ራሴን አስቶ ያስጮኸኝን ታሪክ ማንም እንዲሰማው አልፈለኩም እኔው እንደታመምኩበት እኔው ጋር ይቅር ብዬ ነው የዘለልኩት፡፡
ወንድሙን ደፍረው አንገቱን ገመድ ውስጥ ከተው የገደሉበት ልጅ ምን ሊሰማው እንደሚችል አስቡት፡፡ ይሄና አሁን እዚህ ጋር ያልጠቀስኩት በጣም ሰቅጣጭ ድርጊት ሲፈጸም በአይኑ ያየ ልጅ ሀገሩ ሲገባ የስነ ልቦና ዶክተር ሊያየው ይገባል ብዬ ነበር ያሰብኩት፡፡ ግን ምን አይነት ችግር እንደተቆራኘው፣ እንደገፋው አላውቅም ከስድስት ወር በኋላ ተመልሶ መጥቶ ድጋሚ ታስሮ አገኘሁት፡፡
‹‹ግሩሜ..›› ብሎ ወደ እኔ ሲመጣ ንዴት እንዴት እንደለወጠኝ ሳላውቅ ‹‹ቱ!..ደደብ›› ብዬ በጥፊ ልለው ስል ልጆች ያዙኝ፡፡ ‹‹..ለምን ዳግም ወንድምህን ወዳጣህበት የሞት ቀጣና መጣህ አንተ ውሻ….››አለኩት፡፡ ንዴቴን መቆጣጠር አልቻለኩም፡፡ የባህሩን ጉዞ አውቀዋለሁ፡፡ እንደነሱ አይነት ሰቅጣጭ ግፍ በይፈጸምብኝም በሶስት ጀልባ እየሞላን ተጭነን ስንጓዝ አንዱ ጀልባ ሲሰምጥ አይቼ ራሴን ስቼ ታምሜያለሁ፡፡ እሱ ወንድሙን ገለውበት ያን ሁሉ ስቃይ አይቶ እንዴት ይመለሳል ብዬ ነው መናደዴ፡፡ ሞትም ቢሆን በሀገር አይሞትም ነበር ሀሳቤ….
‹‹ምን ላድርግ ብለህ ነው አማራጭ አጣሁ…ምንም ማድረግ አልቻልኩም፡፡….መልሶ እንባው ቀደመው…………………… ወደ ዋናው ታሪክ አልገባሁም እመለሳለሁ፡፡
No comments:
Post a Comment