Wednesday, September 17, 2014

የሽዋስ አሰፋ የርሃብ አድማ አደረገ * በእስር ቤት ከቅዳሜ ጀምሮ እህል አልመቀሰም

በማዕከላዊ ምርመራ ታስሮ የሚገኘውና የሰማያዊ ፓርቲ ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢ የሆነው አቶ የሽዋስ አሰፋ የአራት ቀን የርሃብ አድማ አደረገ፡፡ የሸዋስ ማክሰኞ ጱግሜ 4 ጀምሮ አዲሱን አመት በርሃብ አድማ ያሳለፈ ሲሆን ቅዳሜ መስከረም 3/2007 ዓ.ም ምግብ እንደቀመሰ ባለቤቱ ወይዘሮ ሙሉ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጻለች፡፡ አቶ የሽዋስ የርሃብ አድማ ያደረገው ከታሰረበት ሐምሌ 1/2006 ዓ.ም ጀምሮ ከጠበቃው ጋር ከአንድ ጊዜ በላይ መገናኘት ባለመቻሉና ዘመድ አዝናድ እንዲሁም የኃይማኖት አባት እንዳይጎበኘው በመከልከሉ ነው፡፡

የሽዋስ አሰፋ በባለቤቱ ብቻ ከሳምንት አንድ ቀን እንዲጎበኝ የተፈቀደለት ሲሆን የርሃብ አድማ ባደረገባቸው ቀናት ባለቤቱ ምግብ ስታስገባ ለየሸዋስ ምግቡ እንደደረሰው ተደርጎ ባዶ ሳህን ሲደርሳት ቆይቷል፡፡ ባለቤቱ የበዓል ቀን ልትጎበኘው በሄደችበት ወቅት ‹‹ወጥቷል›› ተብላ የተመለሰች ሲሆን በማግስቱ ልጆቹን ይዛ ልትጠይቅ ስትሄድም ‹‹ስብሰባ ላይ ናቸው!›› በሚል እንዳታገኘው በመደረጓ ለ15 ቀናት ሳትጠይቀው ቆይታለች፡፡


አቶ የሽዋስ ‹‹የርሃብ አድማውን ያደረኩት ቤተሰብና ጠበቃዬ እንዳይጠይቁኝ በመከልከላቸው ነው፡፡ ለምን እንዲጠይቁኝ አይደረግም? ብዬ ጥያቄ ሳቀርብ ማንም አልመጣም፡፡ ቢመጣ እንድትጠየቅ እናደርግ ነበር፡፡›› የሚል መልስ እንደሚሰጡት ገልጾአል፡፡ በሌላ በኩል ጠበቃው ተማም አባ ቡልጉ የሽዋስን ለማግኘት በተደጋጋሚ ወደ ማዕከላዊ አቅንቶ የተለያየ ምክንያትና መሰናክል እየፈጠሩ ሳያገናኙት እንደቀሩ ገልጾአል፡፡

ጠበቃ ተማም ‹‹ለበርካታ ቀናት አመላልሰውኛል፡፡ ለምሳሌ አንድ ቀን ረቡዕ ጠዋት ሄድኩኝ፡፡ መብትን መለመን ጥሩ ባይሆንም እንዲያገናኙኝ ብለምናቸውም ሊያገናኙኝ አልቻሉም፡፡ ከሰዓት እንድመለስ ነግረውኝ ከሰዓት ብሄድም አሁንም ሊያገናኙኝ አልቻሉም፡፡ ለቀጣይ ረቡዕ ቀጠሩኝ፡፡ አሁንም ረቡዕ ስሄድ የተለያየ ምክንያት እየፈጠሩ ሊያገናኙኝ አልቻሉም፡፡ እንዲያውም ‹‹ምን ታመጣለህ አናገናኝህም!›› አሉኝ፡፡ ብዙ ጥረት ባደርግም ሊያገናኙን አልቻሉም፡፡ የሚገርመው የዳንኤልና የሃብታሙ ጠበቃ የሆኑ ሌሎች ጓደኞች አሉኝ፡፡ አንድ ሰው ከአንድ ጠበቃ በላይ ሊኖረው እንደሚችል እየታወቀና እኔም ደንበኞቼን ማግኘት እንዳልችል ከልክለውኝ እነሱን ግን ‹‹እኛ የምናውቀው ተማምን ነው›› ይሏቸዋል፡፡ እኔ ስሄድ ደግሞ ደንበኞቼን እንዳላገኝ እደረጋለሁ፡፡›› ሲሉ ሁኔታውን ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡

የሽዋስ ምግብ ሲገባለት ምግቡን የሚያደርሱለት አካላት መልሰው ለሚስቱ እንዲሰጧት ይነግራቸው እንደነበር የተናገረ ሲሆን የርሃብ አድማ ላይ እንደሆነ እንዳይታወቅ ምግቡን የበላ አስመስለው እቃውን ባዶ አድርገው መመለሳቸው አሳፋሪና ቅጥ ያጣ አፋኝነት መሆኑን መግለጹ ታውቋል፡፡ የሽዋስ አሰፋ በርሃብ አድማው ምክንያት ሰውነቱ እንደተዳከመ ባለቤቱ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጻለች፡፡

ምንጭ፡- ነገረ ኢትዮጵያ


No comments:

Post a Comment